>

«መሬቱን ለኦሮሞ ወጣቶች ማከፋፈል ስለምንፈልግ ለቃችሁ ወደ ምትሄዱበት ሂዱ!?!» በኦሮሚያ የወረዳ እና የቀበሌ አመራሮች

በላይ ማናዬ
በ«ኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሸዋ ዞን» ዳኖ ወረዳ ውስጥ በአዋዲ ጉልፋና አጅላ ዳሌ ቀበሌዎች ለዘመናት ሲኖሩ የነበሩ ከ1,200 በላይ አባዎራዎች ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸውን ተጎጂዎች ተናገሩ። ከግንቦት 1፣2010 ዓ/ም ጀምሮ  አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ በወረዳውና ቀበሌው አመራሮች የተገደዱት ተጎጂዎች እንደሚያስረዱት 0 ተብለው በኃይል ስለተገደዱ ቤተሰባቸውን ይዘው አቤት ለማለት አዲስ አበባ ደርሰዋል። የተጎጂ ተወካዮች እንዳስረዱት የወረዳና ቀበሌ አመራሮች የተፈናቃዮችን ቤት ንብረት ጨምሮ የይዞታ መሬታቸውን እየለኩ ለወጣቶች እያከፋፈሉ ነው። ችግራቸውን የሚዲያ አካላት እንዲያደርሱላቸው ለኢትዮጵያ ቴሌቪዥን 30 ተወካዮች አቤት ቢልም ሰሚ አጥተው ተመልሰዋል። በአማራነታቸው ብቻ ለዘመናት ከኖሩበት ቀዬ የተፈናቀሉ ወገኖች አውቶቡስ ተራ ከነቤተሰቦቻቸው መስፈራቸውንም ተወካዮቻቸው ገልፀዋል።
አንድ የኢቢሲ ጋዜጠኛ እሱ ዜናውን ለመስራት ተቋሙ ባይፈቅድለትም ተጎጅዎችን በወፍ በረር ጠይቆ፣ በፎቶ አስደግፎ የሚከተለውን መረጃ ላከልኝ።
“ከኦሮሚያ ክልል አምቦ ዙሪያ የተፈናቀሉ በርካታ አማራ ገበሬዎች አዲስ አበባ ላይ መጥተው ወድቀዋል፡፡ ከተፈናቃዬቹ መካከል የእስልምና እምነት ተከታዮች በፆሙ ስዓት በግፍና በሥቃይ ሀብት ንብረታቸንን ቀምተው ስላፈናቀሉን በደላችን ከእስካሁኑም የባሰ ነው ብለዋል፡፡ ተፈናቃዮቹ በአሁኑ ስዓት ኢቲቪ እና ፋና በር ላይ ሆነው ካገር ከቀያችን በግፍ ተባረናል ድረሱልን ቢሉም እስካሁን የሰማቸው የለም፡፡ በአሁኑ ስዓት ኢቲቪ በር ላይ ተቀምጠው የሚታዩት ቀጥራቸው ከሀምሳ እስከ መቶ የሚጠጉ ሲሆን ሌሎቹም መሰል ቅሬታዎችን ለማሰማት በየሚዲያ ተቋማቱ እየማሰኑ ቢሆኑም እስካሁን ሰሚ አላገኙም።”
መንግስትና ህብረተሰቡ በአፋጣኝ ካልደረሰላቸውም ያሉበት ሁኔታ አስቸጋሪ መሆኑን፤ ሜዳ ላይ ወድቀው አቅመ ደካማና ህፃናት የቤተሰብ አባላትን በዝናብ ጭምር እየተሰቃዩ መሆኑን አስረድተዋል።
Filed in: Amharic