>
5:13 pm - Saturday April 18, 2392

የአማራ ሕዝብ የህልውና ትግልና  የኢትዮጵያ አንድነት የገጠመው ፈተና ፦ (ጥሩነህ ይርጋ)

አሁን ከቤኔሻንጉል መተከል ግሙዝ ቆዳው በካራ እየተገፈፈ፣ አይኑ በጦር እየፈረጠ የሚገደለው አማራ ህዝብና በጅማ ማጅ እንደ ግልገል ፍየል በገጀራ የሚቆራረጠው አማራ ወገናችን የሚያልፍበት ስቃይ አዲስ አይደለም።
ከወልቃይት ጀምሮ፥ በሰሜን ጎንደር ዋልድባ ገዳም፣ ዛሬማና ጠለምት ፣ ጠገዴ፣ አርማጭሆ፣ መተማና ቋራ እስከ መተከል ቤኔሻንጉል ግሙዝና ማጅ ዛሬ እየተፈፀመ ያለው የዘር ማፍለስ ዘመቻ፥ ትግራይን ወጣጥሮ እስከ ጋምቤላ በማድረስ፥ የአባይን ግድብ ከስሩ ለመቆጣጠር እየተሰራ ያለ መንግሥታዊ ደባ ሲሆን፤
እሄውም የታሪካዊት ኢትዮጵያን መዋቅር ለማፍረስ በእነ ሌንጮ ለታ ተባባሪነት ፖሊሲ ሆኖ የፀደቀ የቅኝ ገዥዎች እቅድና፥ ከአርባ ጉጉ በደኖ ጭፍጨፋ የቀጠለ አማራን የማጥፋት ዘመቻ ነው።
በነገራችን ላይ ቤኔሻንጉል ግሙዝ ከጎጃምና ከጎንደር አማራ መሬት ተነጥቆ ሆን ተብሎ በወያኔ ፕላን የተመሰረተች፥ የተለየ ህገመንግስት ያላት ትንሽ አገር ናት።
እንደ ፋሺስት የትግራይ ገዥዎች ሃሳብ በኢትዮጵያ ከአማራ ህዝብ የፀዱ አናሳ መንደሮችን በተለያየ አካባቢ ፈጥሮ፤  በአማራ መቃብር ላይ የታለመችው የታላቋ ትግራይ ምስረታ ቅዠት ለማሳካት፥ ለቅማንት ዞን፣ ለወይጦ ዞን እያለ እንደሚዳክረው መሆኑ ነው።
አማራን ማዳከም ታላቋን ኢትዮጵያ ለማጥፋት ወሳኝ መሆኑን የተረዱት የትግራይ ፋሽስት ገዥዎች በአማራ ሕዝብ ላይ ከአመታት በፊት የጀመሩትን ሁለንተናዊ ጥቃት ዛሬም እንደቀጠሉ ናቸው።
ጥቃቱ መልኩን ሲቀያየር አዲስ ይመስለናል እንጂ ቀድሞ አጎፍረው ጫካ የገቡበት የህወሓት ዋና አላማ አሁንም በወያኔ መንደር ሕያው ነው።
ሆኖም ግን ከመታኝ ጠበኛየ ይልቅ ይዞ ያስደበደበኝ ቆጨኝ እንደሚሉት፥
በአንድነት ስም ተሰባስበው ኢትዮጵያዊነትን የሚዘምሩ ድርጅቶች፥ በውጭም በውስጥም የሚገኙ የኢትዮጵያ ሚዲያዎች በተለየ ሁኔታ በአማራ ላይ የተከሰተውን እውነት በግልጽ ለመዘገብ ትኩረት እስካልሰጡ፥ በዳዮችን በድፍረት ለመሞገትና አማራው የሚያደርገውን የህልውና ትግል ለመደገፍ ቁርጠኝነት እስካላሳዩ ድረስ አንድነት እያሉ የሚዘምሩላት ኢትዮጵያ ያለ አማራው ሕዝብ ከምኞት የዘለለ እንደማይሆን መረዳት አለባቸው።
አማራ በኢትዮጵያ በማንነቱ ምክንያት ሁለንተናዊ ጥቃት እየተፈጨመበት የሚገኝ ህዝብ ነው። ኢትዮጵያን በሙሉ አገሬ ብሎ ስለሚያውቃት በሄደበት ሁሉ ቤት ሰርቶና ካገኘው ጋር ተዋህዶ የሚኖር ህዝብ በመሆኑ ለጥቃት የተጋለጠ ሆኗል፥ ከላይና ከታች እንደፈርኔሎ በመከራ እሳት ውስጥ ተጥዶ ይገኛል፥
አሁን በመኖርና ባለመኖር መካከል ሲፍጨረጨር እየታየ እሄን ህዝብ ያገለለ፣ ለአማራ ሕዝብ የህይወት ዋስትና ያልሰጠ ምንም አይነት የአንድነት ዝማሬ ዋጋ ቢስ እንደሚሆን ከእለት ወደ እለት በሚከሰቱት የትግል ሂደቶች መረዳት ይቻላል።
እዚህ ላይ የዛሬ 5 አመት አካባቢ አዲስ አበባ ከተማ በአንድነት ፓርቲ ጉባኤ ላይ የተደረገ ንግግር ላስታውስ፥
አንድ የአርማጭሆ ወጣት ከሰሜን ጎንደር አብርሀጅራ መጣሁ ብሎ፤ አገራችን ኢትዮጵያን ከሱዳን ጋር የሚያዋስነው መሬታችን ህዝብ ሳያውቅ ለሱዳን ተሰጥቶ አልቋል፥ ገበሬዎቻችን እርስታቸውን ለማስመለስና የአገር ድንበር ለማስከበር ብቻቸውን እየታገሉ ነው።
ዛሬ በመካከላችሁ የተገኘሁት መሬታችን ሲወሰድ የነገረን የለም እንዳትሉ በተሰበሰባችሁበት እሄን ትልቅ ጉዳይ ለኢትዮጵያ ህዝብ ለማሳወቅ ነው። ከዚህ በኋላ እኔ ምን እንደሚደርስብኝ አላውቅም፤ የሚመጣውን እቀበላለሁ ህሊናዬ ግን ንፁህ ነው ብሎ ተመለሰ።
እንዳለውም ከጥቂት ከሳምንታት በኋላ በቤቱ ባለበት እንደ ሽፍታ በጦር ታፍኖ እጅና እግሩ በሰንሰለት ታስሮ፥ በማእከላዊና በኢትዮጵያ አሉ በተባሉት ማሰቃያ ቦታዎች ከባህዳር እስከ ሸዋሮቢት ከዝዋይ እስከ ቃሊቲና ቂሊንጦ ተንከራቶ ለብዙ አመታት ብዙ መከራን ተቀብሎ በቅርቡ ተፈትቷል።
ይህ ጀግና ሰሜን ጎንደር አርማጭሆ ያበቀለው፥ ወጣት ጋዜጠኛ ፣ ፖለቲከኛና የሰብአዊ መብት ተሟጋች ሲሆን በሰሜን ጎንደር የቀድሞው የአንድነት ፓርቲ አመራር ነበር፥ ስሙ አባይ ዘውዱ ይባላል።
አባይ በኢትዮጵያ የሱዳን ድንበር እና በትግራይ ተስፋፊዎች ሴራ በሰሜን ጎንደር አማራው ህዝብ እየተፈፀመ ያለውን የዘር ማጥፋት መሰሪ እንቅስቃሴ በመረዳት ገዥውን መንግስት በአደባባይ የሞገተ፤
በሰፊው የፃፈ፣ ገበሬ ወገኑን ከጥፋት ለመታደግ ቀድሞ ድምጽ የሆነና በዚህም ምክንያት ታስሮ ብዙ ስቃይ የተቀበለ የፍትህ አርበኛ ነው። እናከብረዋለን።
አባይ ተወልዶ ያደገበት አካባቢ ለእኔም የትውልድ መንደሬ ነው፥ እሱ ተገደሉ የሚላቸውን ወገኖች እኔም አውቃቸዋለሁ፥ ብዙ ዘመዶቼ ጉድጓድ ውስጥ ታስረው በዛው ሞተው ተቀብረው ቀርተዋል፣ በርሃ ላይ በወያኔ ጥይት ተገድለው ለአውሬ እራት ሆነዋል፥ ወያኔ ከሱዳን መንግስት ጋር ተመሳጥሮ ሳይቀር ያስጨፈጨፋቸውን በስም መዘርዘር እንችላለን።
ከሱዳን ጠረፍ እስከ ወልቃይት ጠገዴ፣ አርማጭሆ መተማና ቋራ፣ ከሰቀልትና ደንቢያ እስከ በለሳ ድረስ፥
በአማራነታቸው ሲሳደዱ ጠላትን መክተው በአርማጭሆ ተራሮች ከትግራይ ወራሪ ሃይል ጋር የተናነቁ፥ በጠገዴ በቆላ ወገራ በዛሪማ፥ ከዋልድባ ገዳም እስከ የሰሜን ተራሮች ድረስ እንቢ እያሉ በጀግንነት የተዋደቁ፥ አንድ መስመር ዜና ሳይጻፍላቸው በግፍ ጥይት የተደበደቡ ብዙ ጀግኖች ወድቀው ቀርተዋል።
ምክንያቱ አንድ ነው፥ በአማራ መቃብር ላይ ታላቋን ትግራይ መስራት።
የአማራ በተገኘበት መገደል እንዳሁኑ በገጀራና በጦር አለመሆኑ ነው እንጂ አዲስ አይደለም። እሄ የጎንደር ችግር ነው በሚል አይነት ችላ ስለተባለ ነው እንጂ፥ በአማራ ላይ ያንዣበበው አደጋ ለሙሁራኑና ለፖለቲከኞች በማሳወቅ ሚዲያ ላይ በማዋላቸው ከፍተኛ ዋጋ የከፈሉ ብዙ ወንድሞቻችን አሉ፥ ባሻ ጥጋቡ፣ ሻለቃ ይላቅን ጨምሮ ሌሎቹ ሞተዋል፥ በሰሜን ጎንደር አርማጭሆ በመተማና አካባቢው ከተነሱ የአገርና የወገን ተቆርቋሪ ወጣቶች፤
ለናሙና ያክል እነሆ፥
አባይ ዘውዱ
አግባው ሰጠኝ
እንግዳው ዋኘው
አስቴር ስዩም
ተገኘ ሲሳይና
ከሌሎች ወጣቶች ጋር በመተባበር በአገሩ የተከሰተውን አደጋ ለማስገንዘብ ብዙ ሰርተው፥
በአገር ጉዳይ፤ የታሰሩ፣ የተሰቃዩ ፣ የተደበደቡ ከፍተኛ በደል ደርሶባቸው በመጨረሻም ሰሞኑን የተፈቱ ጀግና የህዝብ ባለውለታዎች ናቸው።
ሌላው ጀግና አንጋው ተገኝም የታሰረው እሄን ግፍ በጽሁፍ ስላጋለጠ ነው፥ አሁንም ቂሊንጦና ዝዋይ እያመላለሱ ገና በስቃይ ላይ ይገኛል።
ክብርና ሞገስ ይገባቸዋል።
Filed in: Amharic