>

እኛ ኢትዮጵያውያን ለራሳችን የተለየን ነፃ ሕዝቦች ነን - ስንል ምን ማለታችን እንደሆነ - በድንገቴ ለማወቅ ለሚሻ - ይኸው!

Why we Ethiopians say we are quite unique unto ourselves – here we go, for real!
አሰፋ ሀይሉ
አንደኛው ፎቶግራፍ . . . ከታላቋ ብሪታንያ ንግሥት ቪክቶሪያ ልዩ መልዕክተኛ ተደርጎ ወደ ታላቋ ኢትዮጵያ ንጉሥ አፄ ቴዎድሮስ የመጣው ካፕቴን ደንካን ካሜሩን… በእኛ አቆጣጠር በ1860 ገደማ… የኢትዮጵያውን ንጉሠ-ነገሥት መልዕክት… ለእንግሊዟ ንግሥት በትክክል አላደረስክም በሚል. . . እና በሌሎችም ክፉ የደባ ተግባራት (ወይም አሻጥሮችን)… በሃገሬ ላይ እየጎነጎንክ እንደሆነ ጠርጥሬሃለሁ በሚል… እና ምናልባትም ኋላ ላይ ከሆነው ነገር ሲታይ በወቅቱ ተገቢነትም በነበረው ጥርጣሬ ምክንያት . . . . . እንደማናቸውም እስረኛ እጅና እግሩ በካቴና ታስሮ . . . በአፄ ቴዎድሮስ ዙፋን ችሎት ፊት ቀርቦ እንዲዳኝ ሲደረግ. . . በሃገርኛ የ‹‹በልሃ-ልበልሃ›› የችሎት ሙግት ሥርዓት እና በሃገርኛ ቋንቋ ስለእርሱ ሆኖ የሚሟግትለት… ኢትዮጵያዊ ‹የዙፋን ነገረ-ፈጅ› … በጥብቅና እንዲቆምለት ተደርጎ . . . ነገረ-ፈጁ ቆሞ ሲከራከርለት እርሱ ግን በእግረ-ሙቅ (ካቴናው) እንዳለ ሆኖ… ተቀምጦ ችሎቱን እንዲከታተል እንደተደረገ የሚያሳይ… ድንቅ ፎቶግራፍ ነው፡፡ ይህም የነፃዋ፣ ሥልጡኗ፣ ታላቋ ሉዓላዊት ሃገር ኢትዮጵያ – ከዛሬ 150 ዓመት በፊት – ሰዎችን ሁሉ – የኢትዮጵያ ዜጋም ሆነ አልሆነ – እንደማናቸውም ነፃ ሰው – በእኩልነት መብቶቹንና ግዴታዎችን ጠብቃ – ታስተናግድበት የነበረችውን ፍትሃዊ የዳኝነት ሥርዓት – በግልጽ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ – እጅግ አስገራሚ ፎቶግራፍ ነው፡፡
ሁለተኛው ፎቶግራፍ ደግሞ የሚያሳየው. . . እኛ አድዋ ላይ ፋሺስት ወራሪዎችን ድል ልናደርግ ሁለት ዓመት ሲቀሩት – ማለትም በእኛ አቆጣጠር በ1886 ዓመተ ምህረት ገደማ – ከዛሬ 130 ዓመታት በፊት – የተነሣ ፎቶግራፍ ሲሆን – ቦታውም አሁን አውስትራሊያ ተብላ በምትታወቀው ሃገር ወይም አህጉር – ኪምበርሊ በተባለች ሰሜን ምዕራባዊ ሃገር – ዊንድሃም በተሰኘች ትንሽ ከተማ ላይ – ሀገር ምድሩ ሁሉ ወርቅ ብቻ ነው ብለው በማሰብ . . . እና ያን ግዛትና በቅኝ ግዛት ለመቆጣጠር፣ ሕዝቡንም በባርነት ለመፈንገል በቋመጡ የታላቋ ብሪታንያ የባህር ላይ ነጋዴዎችና ሽፍቶች . . . አማካይነት በተቋቋመ ማጎሪያ ጣቢያ ውስጥ – ከያሉበት ታድነው ተይዘው – በሚቀጥለው መርከብ ወደ አውሮፓና አሜሪካ በባርነት ግዞት እስኪላኩ ድረስ . . . አሊያም ብሪታንያ ለስሙ የባህር ላይ የባርያ ንግድን በመከልከሏ የተነሳ – በድብቅ በሚጓዙ አስከፊ የባርያ መርከቦች ወደ አውሮፓና አሜሪካ የባርያ ገበያዎች እስኪቀርቡ ድረስ – እንዳያመልጡ – ከአንገት እስከ እግራቸው በካቴና የከረቸሙባቸውን – እና በወራሪዎቹ በኃይል ተገደው – ቀደም ሲል በነፃነት ይኖሩበት ብከነበረው ብዙም ያልተደራጀ ነፃ የደሴቲቱ ነዋሪ ሕዝብነት – ወደ ባርነት የተሸጋገሩትን – የአውስትራሌዢያን ቀደምት ነዋሪዎች ከእነ ፈንጋያቸው የሚያሳይ – እጅግ አሳቃቂ ፎቶግራፍ ነው፡፡
እንግዲህ እኛ ኢትዮጵያውያን – የተለየን ነበርን – የተለየን ነፃ ሕዝቦች ነበርን – ብለን ራሳችንን ከሌሎች በባርነት ሥር እንዲማቅቁ ከተደረጉ – እና ሕመማቸው ቆዳችንን ዘልቆ ከሚገባው ሌሎች ጥቁር አፍሪካውያን ወንድሞቻችንና – በመላው ዓለምም በነጭ ቅኝ ገዢዎች በገዛ ምድራቸው ለአሰቃቂ የባርነት ዕጣ-ፈንታ ከተዳረጉት ሌሎች ጠያይም ሕዝቦች – እና ከራሳቸውም በቁሳዊና መንፈሳዊ ሥልጣኔ ደረጃቸው የላቁ ከሚመስሉት እና ግን የቁሳዊ ረሃባቸው ሌሎችን አስፀያፊ በሆነ የባርነት አገዛዝ ሥር ጨፍልቀው እንዲገዙ ካደረጋቸው ከነጭ ቅኝ ገዢዎች ሕዝቦች – እና ከሁሉም – እኛ ኢትዮጵያውያን እንለያለን የምንለበት – እና የምንልበት ሳይሆን – በትክክልም በልህቀታችን እና በፍትሃችን የምንለይበት – ምክንያቱ – ይሄ እና ይሄ ነው፡፡ እንዲህ ነበርን፡፡
አሁን ላይ – ምናልባት – ፍትህ ያጡ እስረኞች ኢትዮጵያ ውስጥ ያለፍርድ እየማቀቁ ነው እያለ – ነጋ ጠባ አምንስቲ ኢንተርናሽናል – ጉዳችንን ለዓለም የሚነዛብን፣ እና አንገታችንን በሃፍረት የሚያሸማቅቅበት ጊዜ ላይ እንሆን ይሆናል፡፡ አሁን ላይ ምናልባት – ጉልበተኛው – አቅመ-ደካማውን በኃይል ረግጦ ከሚገዛበት የጉልበተኝነት አባዜ የሞላበት ሃገር ውስጥ ተነክረን እንገኝ ይሆናል፡፡ ምናልባትም አሁን – ወደቀድሞ ታላቅነታችን ወደሚወስደን መንገድ ለጀመርነው ጉዞ ታላቁን እርምጃችንን – በትክክል በፍትህ መድረክ ፍትህ ተነፍጓቸው የነበሩ – (ያስገርማል ይሄ አሳብ!).. በርካታ ኢትዮጵያውያን ዜጎቻችንን ከጎረቤትም ግዞት ሃገር… ከራሳችንም ግዛት ከርቸሌ … በገፍ እየለቀቅን እና ነፃ እያወጣን… የፍትህን እፍታ… ለዚህ ለታላቅ ሕዝባችን ማዳረስ የጀመርንበት የ‹‹ጥልቅ-ምልሰት›› ዘመን ላይ እንገኝ ይሆናል… ምናልባትም ያልተቸገርንበት እና እጅ ያላጠረን የህይወት መስክ ተፈልጎ ይታጣ ይችል ይሆናል – አሁን ላይ፡፡ ይህ ሁሉ አሁን ላይ በአሁናችን ላይ ተደቅኖ ሊሆን ይችላል፡፡ ወይም ተደቅኗል – እና እኛም በየአሸንዳችን የዚያን ሁሉ መከራ ዝናብ እየጠጣን ሊሆን ይችላል፡፡ ነውም፡፡
ነገር ግን – ነገር ግን – ይህ ሁሉ ጉድለት … ይህ ሁሉ ኩስምና… ይህ ሁሉ አጀብ… ይህ ሁሉ እርም…. ወይም በምንም ውስጥ ተገኘን … አሊያም በማንም እጅ ውስጥ ወደቅን – እኛ ኢትዮጵያውያን – ከጥንት ጀምሮ እስከ ዛሬዋም ቅፅበት ድረስ – የታደልነውን ሥልጡንነት፣ እና ነፃነት፣ እና ፍትህን፣ እኩልነትን፣ ልካችንን … ለራሳችን በራሳችን ልክ የሰፋነውን የራሳችንን ጥበብ … እና ያን ሁሉ ያለን ነፃ የምድሪቱ ነዋሪዎች የመሆናችንን እና እንዲያም ሆነን በጽናት ዘመናትን የዘለቅን የመሆናችንን እውነታ … ይህን አኩሪ የጥቁር አልማዞች አብረቅራቂ ታሪክ … እና ይህን አኩሪ ማንነት . .. እና ይህን ታላቅ አኩሪ ሰብዕና … እና አኩሪ የዘመናት ማንነት … እና አኩሪ ያን አኩሪ ገናናነት … እና ያን ድንቅ አኩሪ ባህል … እና ይሄን አኩሪ ኢ ት ዮ ጵ ያ ዊ ነ ት . . .  ማንም ቢሆን … ምንም ቢሆን… ሰማይ ዝቅ … ምድር ከፍ ብትል … ማ ን ም . . . ከቶውኑም ከውስጣችን ሊፍቀው.. ሊያጠፋው.. ሊያከስመው አይችልም፡፡ ማንም ቢሆን ያን ታላቅ ኢትዮጵያዊ ማንነት . . . !!!
ያን ታላቅ ኢትዮጵያዊ ማንነት . . . ምንም ዓይነት ምድራዊ ኃይል ይምጣ. . . ለጊዜው ሊያዳፍነው.. ለጊዜው ሊያደበዝዘው.. ለጊዜው ሊያኮሰምነው ይችል ይሆን ይሆናል፡፡ ምናልባት ነው እሱም፡፡ ነገር ግን . . . ያን በፅኑ አልማዝ የተጻፈ … እኛን ልዩ የሚያደርገን… አሁን አፋችንን ሞልተን እኛ እኮ ኢትዮጵያውያን ነን የምንልበትን… ከባርነት ነፃ የወጣንበትን የዘመናት አኩሪ ኢትዮጵያዊ ታሪክ.. እና አፍሪካዊ ገናናነት . . . ከቶውኑም… ማንም… ከልባችን፣ ከአዕምችን፣ ከውስጣችን፣ ከዕንቁ ኢትዮጵያዊ ማንነታችን ፈልቅቆ ሊያወጣው፣ ሊፍቀው፣ ሊደልዘው፣ ሊያጠፋው፣ ሊያከስመው፣ ከቶውኑም  አ ይ ቻ ለ ው ም ! !  ምክንያቱምይህ — የ ተ ቀ ደ ሰ ፡ ክ ቡ ር ፡ የ ኢ ት ዮ ጵ ያ ዊ ነ ት ፡  አ ይ በ ገ ሬ ፡  መ ን ፈ ስ — በሁላችን ውስጥ አለና፡፡ 
አምላክ ኢትዮጵያን እና ኢትዮጵያውያንን እና የከበረውን የኢትዮጵያዊነት መንፈስ – በቅድስና፣ ለበጎ፣ ለመልካም፣ ለበረከት አድርጎ አስተካክሎ፣ መርቆ፣ አብዝቶ፣ ይባርከው፡፡ ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር፡፡ እኔ አበቃሁ፡፡ የሃገሬ ታሪክ ግን ይቀጥላል፡፡ ቻው፡፡
ፎቶግራፎቹ (ለየባለቤቶቹ እጅግ ከከበረ ምስጋና ጋር)፡-
1ኛው) Captain Charles Duncan Cameron the British diplomat who carried a message from Queen Victoria of Great Britain but who was later arrested and jailed by Ethiopian Emperor Thewodros’s order around the year 1868;
2ኛው) Australian Aborigine slaves in chains at Wyndham prison, 1902.
Filed in: Amharic