>

ልማታዊ ዘገባ (በፍቃዱ ሞረዳ)

በአሜሪካ፣ በሜክስኮና ጃማይካ የኢሕአዴግ መንግሥት ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ካሳ ተክለብርሃን ባለፈዉ ቅዳሜ ሚያዚያ 27/2010 ወይም ሜይ 5/2018 ሂዩስተን/ቴክሳስ ነበሩ፡፡
  ሂዩስተን ስለመምጣታቸዉ በግልጥ ማስታወቂያ ወይም ጥሪ የተነገረ ነገር ባይኖርም፣ ለተልዕኳቸዉ ቅርብ የሆኑ ሰዎች ሲናገሩ አስቀድሞ ተሰምቷል፡፡ ስለአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር  ሕልም / ሐሳብ በከተማዉ ከሚኖሩ የኢትዮጵያና ‹‹ ትዉልደ-ኢትዮጵያ›› ማኅበረሰብ ጋር ለመነጋገር፣ የዲያስፖራዉን ነፃ ሐሳብ ለማዳመጥ፣ ጥያቄዎችንም ተቀብለዉ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ለማስተላለፍ እንደሆነ ነዉ ስለተልዕኳቸዉ የተወራዉ፡፡
 ማንም ሰዉ በነፃ ገብቶ ፣ሐሳቡን በነጻነት ይናገራል ተብሎ ስለነበረ ከአንድ ወዳጄ ጋር በስብሰባዉ ላይ ለመገኘት ተቀጣጠርን፡፡ ቅዳሜ ምሳ ሰዓት ላይ ለወዳጄ ደዉዬ የምንገናኝበትን ሰዓት ስጠይቀዉ መሄድ እንደማይፈልግ ነገረኝ፡፡ምክንያቱም የተጠሩት 120 ሰዎች እንደሆኑና ከዚያ ዉጪ ሌሎች ጫጫታ ፈጣሪዎችን እንደማያስተናግዱ ከአዘጋጆቹ አንዱ ነግሮታል፡፡
እኔ ግን ሄድኩ፡፡ ጉዳቸዉን ልይ ብዬ፡፡ በሶስት የታጠቁ የአሜሪካ ፖሊሶች ይጠበቃል በሩ፡፡ አልፌ ገባሁ፡፡ ‹‹ ማነህ? ምንድነህ?ወዴት ነህ? ››አልነበረም፡፡ ስሜን እንድፅፍ ተጠይቄ ፃፍኩ፡፡ 120 ሰዎች ተጠርተዋል ለተባለዉ ስብስባ ፣በአዳራሹ ዉስጥ የነበረዉ ወንበር ከሰባ አይበልጥም፡፡ ‹‹ ኣዳሜ ዛሬ ቆሞ ዲስኩር ሊኮመኩም ነዉ›› አልኩ ለራሴ፡፡
አምባሳደሩ እንደአምባሳደርነታቸዉ ለሀገራቸዉ ሰዉ ልማድ ታማኝነታቸዉን ለማሳየት ነዉ መሰል ሰላሳ ያህል ደቂቃ ብቻ አሳልፈዉ መጡ፡፡ እርሳቸዉ በአዳራሹ ሲሰየሙ የነበርነዉ ሰዎች ከአርባ በላይ መሆናችንን እንጃ፡፡ ቢያንስ ከሃያ ሺህ በላይ ስደተኛ የሀገር ሰዉ እንደሚገኝበት በሚገመተዉ ከተማ ዉስጥ አምባሳደሩ አርባ ምናምን ሰዉ ገንዘብና ጊዜ ማባከናቸዉ እየደነቀኝ እያለ አቶ መሰለ የተባሉ ሰዉ አምባሳደሩን ለማስተዋወቅና ለመጋበዝ ወደመነጋገሪያዉ ቀረቡ፡፡
   ሰዉዬ ‹‹ የእዳሴ ምክር ቤት›› የሚባለዉና የሕወሃትና የኢሕአዴግ ወዳጆች ያቋቋሙት እንትን መሪ ናቸዉ፡፡ አምባሳደሩንም ‹‹ ይምጡና በከተማችን የሚገኙትን የሀገርዎን ሰዎች ያነጋግሩ ›› ብሎ የጠራቸዉ ይኼዉ የእነመሰለ እንትን ነዉ፡፡ ከዚህ በፊትም ግርማ ብሩን ጋብዞ ነበር፡፡ ፖሊስ ጠርቶም ሰዎችን አሳስሯል፡፡
      እናም አቶ መሰለ በስብሰባዉ ላይ የተገኙትን የትግራይ እና የኤርትራ ኮሙኒቲ አባላትን በስም ጠቅሰዉ አመሰገኑ፡፡ በስብሰባዉ ላይ ስለመገኘታቸዉ፡፡ ስለኢትዮጵያ ኮሙኒቲ ተሳስተዉም የተናገሩት ነገር አልነበረም፡፡ ነገሩ ደንቆኝ ( ለምን እንደደነቀኝ እንጃልኝ) ግራና ቀኝ ሳይ ከእኔ ፣ከዶክተሩ ዘመዴና ከአርቲስት ፋንቱ ማንዶዬ ( በከተማችን ይኖራል) በስተቀር ‹‹ፀጉረልዉጥ›› የለም፡፡ ሕወሓታዊያንና የአይተ ኢሳይያስ መንግሥት ተቃዋሚ ኤርትራዊያን ናቸዉ በነቂስ፡፡
   አምባሳደሩ የመንግሥታቸዉን አቋም ከገለፁ በኋላ አስተያየትና ጥያቄ ቀረበ፡፡ አምባሳደሩና መንግሥታቸዉ የተለያዩ ሚዲያዎችን (ከኢሳት በስተቀር) በመጠቀም ስለፖሊሲያቸዉ በስፋት እንዲያስረዱ የመከሩ የጎረቤት ሀገር ኢሳት ጠል ወፈፌዎችን የተናገሩትን ጨምሮ የተለያዩ አስተያየቶች ተሰጡ፡፡
    አንድ  ኤርትራዊ-አሜሪካዊ እንደሆነ ተናግሮ በእንግሊዝ አፍ የሚያወራ ሰዉዬም ፣ የኢሕአዴግ መንግሥት ተቃዋሚ ፓርቲዎችን፣ ‹‹ ተቃዋሚ ተብዬዎች›› (the so-called) ብሎ ሲያብጠለጥል የሰማን ጊዜ፣ ሥርዓቱ ቀለብ ከሚሰፍርላቸዉ ንክ ደላሎች አንዱ ሊሆን እንደሚችል ገምተን ዝም አልን፡፡ይህ ሰዉ ከሃያ ሰባት ዓመታት በፊት የሚበላዉን የሌለዉ የኢትዮጵያ ሕዝብ ጠግቦ ማደር መጀመሩን፣ ኢኮኖሚዉ ወደሰማይ መተኮሱንም ሲነግረን፣‹‹shame on you›› አልነዉ በልባችን፡፡
   የአድዋ ተወላጁ አቶ መሐመድ አንድ ቆንጣጭ ነጥብ አነሱ፡፡ እንደ አቶ መሐመድ አገላለፅ በዛሬይቱ አክሱም ፣አንድ ዉሻና አንድ ሙስሊም ቢሞቱ ፣ዉሻዉ መቀበሪያ ቦታ ሲያገኝ ሙስሊሙ ግን በተወለደበት አፈር ዉስጥ የመቀበር መብት የለዉም፡፡
‹‹እዉነት የጋራ ሀገር ነዉ ያለን? ›› አሉ አቶ መሐመድ፡፡ እንኳን እኔ አምባሳደሩም ለዚህ ጥያቄ ቀጥተኛ መልስ አልነበራቸዉም፡፡ ‹‹ ከአጠቃላይ ችግሮቻችን ጋር አብሮ ሊፈታ የሚችልበት ሁኔታ ነዉ ያለዉ ›› ብለዉ በዲፕሎማት ሞሳ አጠቃቅሰዉ አለፉ፡፡
‹‹ ስድስት ሰዉ ገድሎ…›› እያሉ በኮሎኔል ደመቀ ላይ ጣት የቀሰሩ ሰዎችም ከአንድ በላይ ናቸዉ፡፡ ሌሎች ዝባዝንኬዎችም ነበሩ፡፡
አምባሳደሩ ተፈታታኝ ጥያቄ ስላልቀረበላቸዉ ምላሻቸዉ ቤተሰባዊና ዲፕሎማሲያዊ ነበር፡፡ጥቂት ካድሬያዊም ጭምር፡፡ በማንኛዉም ምክንያት ከሀገር ወጥተዉ በስደት ያሉ ሁሉ ዜጎች ያለምንም ስጋት ወደሀገራቸዉ እንዲገቡ አምባሳደሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ‹‹ በእኔ ይሁንባችሁ›› ብለዉ፡፡
ጥሪዉ ልቤን ቢያሞቀዉም፣ የፀረ ሽብርና የሚዲያ ሕጉን፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን፣ ኮፒዉ በእጄ የሚገኘዉን ግማሽ ደርዘን የፍርድ ቤት የመያዣና የእስር ትዕዛዝን አስቤ ተረጋጋሁ፡፡
     በአጠቃላይ አምባሳደሩ ለስላሳ ነበሩ፡፡ ‹‹ዲፕሎማት የሴትን የልደት ቀን እያስታወሰ፣ ዕድሜዋን የሚረሳ ነዉ›› ያለዉ ያ ያልታወቀ ሰዉ ማነዉ?
አሪፍ አይደል?
Filed in: Amharic