>

የሰሞኑ የዳኛ እያሱ ፈንቴ ነገር አዋጁን በጆሮ ሆነብኝ!!! (ኢ/ር ይልቃል ጌትነት)

ዳኛ እያሱ ፈንቴ ሜዳ ላይ በዳኝነት ስራ ላይ እያሉ ድብደባ እንደተፈፀመባቸውና አማራነታቸው ላይ ያተኮረ ፀያፍ ስድብ ተሰድበዋል በሚል በዚሁ ሚዲያ መነጋገሪያ ሆነዋል።
በእኔ እምነት እንዲህ ያለው ነገር በአማራ ላይ ሲሰነዘር  አዲስ ነገር አይመስለኝም። ለምሳሌ ብጠቅስ ቀኑን በውል ባላስታውሰውም በመፈንቅለ መንግስት ሙከራ በእስር ከነበሩት ጀነራሎች ጀነራል አሳምነው ፅጌ ይመስሉኛል በዘሬ እና በማንነቴ እየተሰደብኩ ተደብድቤያለሁ ፤በድብደባ ብዛት ስጋዬ ከአንገት ሃብሌ ጋር አብሮ ተቆርጡዋል ብለው ለፍርድ ቤት ተናገሩ ተብሎ በVoa ሰምቻለሁ። በተለያዩ ጊዚያት ፍርድ ቤት በተገኘሁባቸው ቀናት በምርመራ ወቅት በድብደባ የቆሰለውን አካላቸውን እያሳዩ በአማራነታቸው ፀያፍ ስድብ እንደተሰደቡ በግንቦት ሰባት ተጠርጥረው የታሰሩ ሲናገሩ ሰምቻለሁ። የሶሻል ሚዲያ ዘጋቢዎችም እንዲህ አይነቱን ተመሳሳይ ዜና ዘግበው አንብቢያለሁ።
 ታዲያ ይህ ከሆነ ስድብ በቃላት የሚገለፅ የአስተሳሰብ ነፀብራቅ መሆኑ ቢታመንም የአማራ ጉዳይ ግን ከሃሳብ አልፎ ወደ ተግባር ተለውጦ እስከ በሰሞኑ ዜና ድረስ  ስለተገደሉ ሰዎች፣ቤታቸው ስለተቃጠለ መድረሻ አጥተው ቤተ ክርስቲያን የተጠለሉ ሰዎችን በአይናችን እያየን ነው። እኔ እንደሚመስለኝ ይህ ከላይ የገለፅኩት በአማራ ላይ በአስተሳሰብና በድርጊት የተገለፀው ነገር በመንግስት እውቅና የተሰጠውና ህገ መንግስታዊም ይመስለኛል።
በኢህአዴግ ህገ መንግስት መግቢያ ላይ አንድ ይህንኑ ተግባር ለመግለፅ የተቀመጠ ሃሳብ አለ። ይህውም “እኛ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ባለፉት ጊዚያት የነበረንን የተዛባ ግንኙነት በማረም……..” ። ይህ የተዛባ ግንኙነት የሚለው አገላለፅ አማራ ጨቁዋኝ ሌላው ተጨቁዋኝ  አይነት ግንኙነት ለመግለፅ የገባ ይመስለኛል።
በመሆኑም “በህገ መንግስቱ” መሰረት የተዛባውን ግንኙነት ለማረም “ጨቁዋኝ”በነበረው አማራ ላይ የሚወሰድ የሂሳብ ማወራረድ ነው።
ስለሆነም የዳኛ እያሱ ጉዳይ ህገ መንግስታዊ የሆነው ችግር ከብዙዎቹ መገለጫ ምልክቶች አንዱ እንጅ የተለየና እንግዳ ነገር አይደለም (አዋጁን በጆሮ ነው)  ያልኩት ለዚህ ነው። ይህ በየቦታው የሚታየው ያፈጠጠና ያገጠጠ ችግር ከመሰረቱ እንዲፈታ ከተፈለገና ኢትዮጵያም ይጎዝላቪያ ፣አማራም እንደ ሰርቭ ከመሆኑ በፊት ይህ አማራን ጨቁዋኝ ሌላውን ተጨቁዋኝ የሚያደርገው የህወሃት/ኢህአዴግ ህገ መንግስት ከመሰረቱ መቀየር አለበት። ማድበስበስና መሸፋፈን ችግርን ያፋፋና ያባብሳል እንጅ ለአንዣበበብን አደጋ መፍትሔ አይሆንም።
Filed in: Amharic