>
5:13 pm - Friday April 19, 7005

ሁሌም ጥላቻ የነገሰ ቢመስለንም እንኳ ፍቅር ያሸንፋል!!! (አለማየሁ ማህተመ ወርቅ)

….ዛሬ ላይ አፋችንን በእጃችን ላይ የሚያስጭነን፣  በሀዘን ልባችንን የሰባበረ ፣ አይናችንን በእንባ፣ አንደበታችንን በኡኡታ ያስከፈተ፣ ጆሮአችንን፣ በወገን ዋይት እና እሪታ ብዛት እንዲደፈን ያደረገ ያ ታላቁ የሰናኦር ግንብ…..።
አዎ.., ይህ ታላቅ የሆነ እስከ ሰማየ ሰማያት ከፍ ከፍ ያለ የሰናኦር ግንብ መሰረቱን የጣለበትን ዘመን እና ሁኔታ ለታሪክ እንተወው እና ለሶስት አስርት አመታት ትንሽ ትልቅ ሳይሉ በየ እዝነ ልቦናችን ሲገነቡት የኖሩትን ያንን የጥላቻ፣ የመለያየት፣ የመከፋፈል፣ የእኔ ብቻ ባይነት የሰፈነበትን፣ “እኛ እና እነርሱ” ያሰኘንን በወዲህኛው የአጥሩ ገጽ የወገን ሞት፣ ስቃይ ሰቆቃ፣ እስከ መንበረ ጸባኦት የደረሰ የወገን ዋይታ እና እሪታ…..
ከግንቡ በወዲያኛው ገጽ የከበሮ ድለቃ፣ ፌሽታ እና እልልታ፣ ግሳቱ ገመገም ዞሮ የሚሰማ ጥጋብ የነገሰበትን….
ያንን የሀጢአት ውጤት የሆነ የዘረኝነት አጥር የመለያየት ግንብ…..
ያንን ተገዥዎችን እያቃጠለ ገዥዎችን እያሞቀ በሚንቀለቀል እሳት የተቀጠረ ቅጥር – የተገነባ ግንብ እጅ ለእጅ ተያይዘን በፍቅር ውሀ እሳቱን ልናጠፋ ፣ በበረታ የአንድነት ክንድ ድንጋዩን ልናነሳ ሲገባን እኛ ግን….. አናሳዝንም ወይ??? አለ ድምጻዊው።
አዎ…. እኛ ግን ያ ታላቅ ግንብ በፊታችን ቆሞ፣ እንደ ተራራ ገዝፎ ፣ እስከ ሰማየ ሰማያት ከፍ ከፍ ብሎ አስጨንቆን ሳለ እንደ ኦሪቱ ዘመን ሥላሴዎች ወርደው ቋንቋቸውን ለዋውጠው እንዲያፈርሱልን በመጠበቅ ይመስላል እርሱን ለመለኮታዊ ሀይል ትተን የየራሳችንን የእኔ ብቻ ባይነት ፣ አንተ ከእኔ ወገን አይደለህም በዘመኑ ቋንቋ “መጤ ነህ ” ሂድልኝ የምንልበት ወገናችንን በጥላቻ የምንመርዝበት አያትህ እንዲህ አድርገው ፣ ቅድመ አያትህ እንዲህ ብለውኝ እያልን ከክፉ ልብ የመነጨ ክፉ ሀሳብን በክፉ ልባችን ጨምረን የምንለያይበት የራሳችንን እያሪኮ ግንብ ገንብተን ቁጭ ብለናል።
ዛሬም ገዳዮች፣ አሳዳጆች ፣ በጥላቻ ጦር የምንወጋ ፣በነገር ምላስ የምናቆስል ሆነናል። ለሁላችን ጥላ መጠጊያ እና መሸሸጊያ ከሚሆነን ትልቁ ዋርካ (ኢትዮጵያዊነት) ይልቅ ገዥዎች እንደ ሰም አቅልጠው እንደ ገል ቀጥቅጠው ለመግዛት አንገታችንን ቀና አድርገን የነጻነት፣ የፍትህ እና የእኩልነት ጥያቄ ባነሳን ጊዜ፣ መብቴን አላስነካም ባልን ሰአት ደማችንን እንደ ውሀ ለማፍሰስ፣ አጥንታችንን ለማድቀቅ፣ የመንፈስ ልእልናችንን (ሞራላችንን ) ለመንካት የተጠቀሙበትን ፋሽስታዊ የከፋፍለህ ግዛ መጋዛቸውን ተመልክተን በቅርጹ እና በአምሳሉ ሰርተን አካላችንን ቆርጠን ለመጣል የማንሣሣ ጉዶች ሆነናል።
አንተ አማራ ነህ ሂድልን ብለን ቆርጠን የጣልነው ቢገባን አማራነቱን ሳይሆን አካላችንን ነው፤ አንቺ ኦሮሞ ነሽ ተለይን ብለን ያሳደድናት ቆርጠን የጣልናት እናት የነበረች ፣ አባት የሆነ፣ ሚስት የሆነች፣ ባልም የነበረ ልጅም የሆኑንን አካላችንን ነው።
አካላችንን ቆርጠን እየጣልን እየለየን እየተለያየን ምድሪቱን አኬልዳማ – የደም መሬት አደረግናት። ይህ እስከ መቼ ይሆን የሚቀጥለው? ማቆምያውስ ምን ይሆን?
ያ ቆርጠን የጣልነው አካላችን ህመሙ እስከ ልባችን ዘልቆ ካላመመን፣ ዋይታ እና እሪታው ካልተሰማን እኛ አልሰማም ያልነውን የወገን ጩህት የሰማይ አምላክ የሰማ እለት ያ የታበይንበት አካላችንን ቆርጠን ከቅጥር ውጭ ወርውረን የዘጋነው ቅጥር፣ በወገን እንባ እና ደም አላቁጠን የገነባነው የኢያሪኮ ግንብ በላያችን ላይ ይፈርሳል፣ ይደረመሳል።
አዎ ዛሬ በየልቦናችን ከገነባነው የጥላቻ፣ የመለያየት የቂም በቀል ግንብ እንውጣ። እስከ ሰማየ ሰማያት ከፍ ከፍ ወዳለው በተአምር ይፈርሳል ብለን ወደምንጠብቀው ወደ ሰናኦር ግንብ እንሂድ፤ “እኛ እና እነሱ” ያሰኘንን ፤ያንን በእኔ ብቻ ልብላ አንተ ድሮ በልተሀል፤ እኔ ብቻ ልግዛ አንተ ድሮ ገዝተሀል የሚያሰኘውን፤ የወገን አጥንት ድንጋይ ሆኖ ደሙም ውሀ ሆኖ ተለውሶ እና ተላቁጦ የተሰራ፣ የጥላቻ መንፈስ እሳት ሆኖ የሚንቀለቀልበትን አላስጠጋ ያለንን የዘረኞች ግንብ ለማፍረስ እንነሳ።
የሁሉም ነገር መጀመሪያና የሚበልጠውም ፍቅር ነው እና የፍቅር ጉባኤ (ሱባኤ) እንግባ። በፍቅር ውሀ እሳቱን እናጥፋ ፤ በበረታ የአንድነት ክንድ ድንጋዩን (አጥንታችንን) እናንሳ።
ያኔ ዋይታን የተሞላች ምድር በእልልታ ትደምቃለች፤ ያኔ በሀዘን ከተሰበረ የእናቶች የአባቶች ልብ ፈልቆ የሚወጣው እንደ ፍል ውሀ የሚለብልብ የሰቀቀን እንባ ሳይሆን በፍቅር ከተሞላ ንጹህ ልብ ፈልቆ የሚፈስ ነፍስን በሀሴት የሚያወራጭ ቀዝቃዛ የፍቅር እንባ ይፈልቃል…
አዎ ያኔ…..የቆሰለ ልብ ይጠግጋል ፣  የተቆረጠ አካል ይጠገናል፣ የተደፋ አንገት ቀና ይላል…
ያኔ…. አካሉን ሊቆርጥ ከአፎቱ የተመዘዘ ጎራዴ የጨበጡ እጆች የተራበ ወገንን ለማጉረስ ይዘረጋሉ
፣ ምላጭ የሳቡ እጆች ደጅ የወደቀውን ወገን ለማንሳት፣ የጦር መሳሪያ የተሸከመ ትከሻም ወገኑን ለመሸከም አይዝልም።
አዎ ያኔ….የፍቅር አምላክ ፊቱን ይመልስልናል፣ ምድሪቱም የወዛችንን ፍሬ ያለ ስስት አትረፍርፋ ትሰጠናለች…. እዝች ጋር “… ፍቅር አጥተንእንጂ በርሀብ የተቀጣን…” የታላቁን የፍቅር ሰው የቴዲ አፍሮን ዘፈን በጆሮ አችሁ ሳይሆን በእዝነ ልቦናችሁ አድምጡልኝ።
ሁሌም ጥላቻ የነገሰ ቢመስለንም እንኳ ፍቅር ያሸንፋል!!!
ይህች ጽሁፍ መታሰቢያነትዋ ፡- 
“ላንች ነው ኢትዮጵያ 
ላንች ነው ሀገሬ…” እያለ በፍቅር ተስቦ በረሀ ለገባው በማይረቡ ሰዎች እጅ ወድቆ የማይረባ ቦታ ለተጣለው አንዳርጋቸው ጽጌ
* የዘመናቸውን እኩሌታ መንግስት እያፈረሳት ያለችን አገር ለመግንባት ሲታትሩ ዋጋም ሲከፍሉ ለኖሩ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ እና ጋዜጠኝ ሲሳይ አጌና። እንዲሁም ዛሬም ድረስ ዋጋ እየከፈሉ ፕሬሱ ከመጥፋት ለታደጉ መላው የኢትዮጵያ ነጻ ፕሬስ አባላት ትሁንልኝ።
Filed in: Amharic