>

ልቅናው -የአንዳርጋቸው ፅጌ ....!  (በመስከረም አበራ)

 የሃገራችን ፖለቲካ ህማሙ ብዙ ነው፡፡የህማሙ ራስ ደግሞ በፖለቲካው ሰፌድ ወደፊት የሚመጡ ፖለቲከኞች የስብዕና ችግር ነው፡፡ ግብዝነት፣ሴረኝነት፣በግልፅ የማይነገር የስልጣን ጥም፣ልታይ ባይነት፣ የእውቀት እጥረት፣ከንባብ መጣላት፣እብሪት፣የፖለቲካ ግብን ጠንቅቆ አለማወቅ፣ስህተትን ያለመቀበል ካፈርኩ አይመልሰኝ ድርቅና፣ቡድንተኝነት፣አድመኝት፣በግልፅም በስውርም የሚንፀባረቅ ዘረኝነት በተቃውሞውም ሆነ ገዥው ጎራ በተሰለፉ አብዛኞቹ ፖለቲከኞቻችን ልቦና ያደረ ክፉ ነቀርሳ ነው፡፡ ይህ ክፉ ደዌ የፖለቲካችንን ፈውስ አርቆ ቀብሮብን ከዛሬያችን ትናንታችን የሚሻል ተስፋ ቢሶች አድርጎናል፡፡
ሆኖም በፖለቲካችን ፊተኛ መስመር ብቅ ያሉ መሪዎች የስብዕና እንከን ሁሉንም ፖለቲከኞቻንን አንድስ እንኳን ሳያስቀር የሚያጠቃልል አይደለም፡፡ ይህ ነቀፌታ የማይነካካቸው ትቂት ቢሆኑም ለዘር ለፍሬ የተቀመጡ፣በአደባባይ ካወሩት በላይ በፖለቲካው ጓዳ ውብ ሆነው የሚታዩ አንዳርጋቸው ፅጌን የመሰሉ ከማውራት ቆጠብ ከመስራት በርታ ያሉ ሰዎችም ታድለን ነበር፡፡አሳዛኙ ነገር ሴረኛው ፖለቲካችን እንዲህ ያለ ቅን ማንነት ላላቸው ባለ ከባድ ሚዛን ፖለቲከኞች የማይመች፣ምርትን ከግርድ የመለየት አቅም የሚያጥረው፣ከሁሉም በላይ ደግሞ ድጋፍ ተቃውሞው ተወልጄነት የተጫነው መሆኑ ነው፡፡
 ዘመናችን ዘረኝነት እና ስሜታዊነት ምክንያታዊነትን አሳደው አባረው ብቻቸውን የተንሰራፉበት ነው፡፡  ስለሆነም እንደ አንዳርጋቸው ፅጌ አይነት እውነትን ገንዘቡ ያደረገ፣ምክንያት ይዞ የሚመጣ፣ሩቅ የሚወስደውን መንገድ የሚያሳይ፣ባለጥልቅ ግንዛቤ ፖለቲከኛ ጆሮ የሚሰጠው የለም፡፡ከእዛ ይልቅ ምላሱ ላይ ያስቀመጣትን አንዳንድ ጥቅስ ቀራርሞ የሚያነበንብ ካድሬን መድህን ልናደርግ ይቃጣናል፡፡ ይበልጥ የሚያሳዝነው ደግሞ ሰርተፍኬት ሸማች ካድሬዎች ባለ አእምሮዎችን የሚያስሩ፣እባካችሁ ልቀቁልን ተብለው የሚለመኑ መሆናቸው ነው፡፡
ፖለቲካችን እንዳይሆን ሆኖ የተበላሸ ባይሆን ኖሮ አንዳርጋቸው ፅጌን አስሮ አሳር መከራ የሚያሳይ አገዛዝ መሪ የግንዛቤውን ያህል ስለኢትዮጵያዊነት ሲያወራ፣ስለ ሌብነት አስከፊነት ሲተርክ፣ስለ እኩልነት ባማረ ቃል ሲደሰኩር ልባችን ባልቀለጠ ነበር፡፡አንዳርጋቸው ፅጌ ሃገር አፍራሽ ወንበዴ ተደርጎ፣ዓለምን የሚያክል ወጥመድ ተዘርግቶ ሲታደን ኖሮ በስተመጨረሻው የምድር ሲኦል ውስጥ የተወረወረው የኢትዮጵያን መከራ ማብቂያ መንገድ ያገኘ መስሎት በዛው ሲማስን ነው፡፡ አንዳርጋቸው ፅጌ ለኢትዮጵያ ያለውን ፍቅር የሚገልፀው በቀይ ምንጣፍ እየተራመደ፣ቶክሲዶ ለብሶ ሃገር እስኪያልቅ እየዞረ፣ልጆቹን እቅፉ ላይ አድርጎ እየተመፃደቀ፣የገባውም ያልገባውም በሚለቀው የጭብጨባ ጩኽት እየታጀበ አይደለም፡፡ከእባብ ጋር ተኝቶ፣የጉድጓድ ውሃ ጠልቆ ጠጥቶ፣እንጨት ፈልጦ፣በበረሃ ተጠብሶ፣አልባሌ ለብሶ፣እጅ እግሩን እከክ ወርሶት፣የትግል ጓዶቹን ልብስ አጥቦ፣በወንድ ልጅ እጁ እንጀራ ጋግሮ፣ያላደገበትን ተቆራምዶ፣ልጆቹን በትኖ ነው፡፡ይህ ሳያንሰው እሱ ራሱን በጎዳ የተቀማጭ ሰማይ ቅርቡ ለብላቢ ምላስ ችሎ፣ሰምቶ እንዳልሰማ ሆኖ፤አላማውን ብቻ አንግቦ እየተጓዘ ነው፡፡አንዳርጋቸው ተጨብጭቦለት አያውቅም!አልተጨበጨበልኝም ብሎም ከመስራት ለግሞ አያውቅም፡፡ ስራ ሰራሁ ብሎ በማንም ላይ አፉን አላቆ አያውቅም፤አንደበቱ ምጥን እና  ጨዋ ነው፡፡ እንደ ክርስቶስ ተሰቅየ መድህን ልሆንላችሁ ይህን እና ያንን ሆንኩላችሁ ብሎ ውለታ ማስቆጠርም አይነካካውም፡፡ የሚያደርገውን ሁሉ የእሱ ትውልድ ፖለቲካ ያበላሸውን ለመካስ የተደረገ የእዳ መክፈል ስራ አድርጎ ይቆጥራል እንጅ፡፡ ብዙ ሰርቶ ትንሽ በማውራቱ፣ብዙ ተሸክሞ ግን እዩኝ እዩኝ ባለማለቱ ፣ፊት ፊት ሁን የሚለው የስልጣን ጥም ስለሌለበት ከመታሰሩ በፊት በብዛት አይታወቅም ነበር፡፡
አንዳርጋቸው ሌብነትን፣የሰብአዊ መብት ረገጣን፣አድልኦን ተጠየፍኩ የሚለው በባለጠመንጃ ቤት ሩብ ምዕተ አመት ሲያጋፍር ኖሮ አይደለም፤ሁለት አመት ከመጫኛ ረዝሞበት እንጅ! በዛው የሁለት አመት ቆይታው ታጋይ ነን ባይ ባለስልጣናት በየቤታቸው ሰርክ የሚደግሱት የሆድ ድግስ ሳይቀር ሃገር ይጎዳል ብሎ የሚያስብ፣ ፊት ለፊት የሚሞግት የኢትዮጵያዊ ሁሉ ጠበቃ ነው፡፡ ቅባት የበዛበት የሆድ ድግሳቸው ቢያቅለሸልሸው “የተዋጋችሁት ህዝብ ቀምተው ግብር ያበሉ በነበሩ የፊውዳሉ ዘመን  መሳፍንት ቀንታችሁ ነው እውነት ለህዝብ አስባችሁ ነው?” እስከማለት ደርሷል፡፡ አንዳርጋቸው አይልመጠመጥም! እንዲህ እውነትን ለስልጣን የመናገር አቅም እና ድፍረት ያለው ሰው ነው፡፡
የሰው ልጅን ክቡርነት ጠንቅቆ በማወቅ ብቻ ሳይሆን ለመተግበር በመፋተር  አንዳርጋቸው ፅጌ ጓደኛ የለውም፡፡ ለዚህ አንድ ቀላል ማሳያ ማሳያ ላንሳ፡፡ስለጀግንነቱ በወንዙ ልጆች ሰርክ የሚወራለት ሜጄር ጀነራል ሃየሎም አርዓያ ከደደቢት ገስግሶ አዲስ አበባን በረገጠ ሰሞን ዘመናዊ መኪናውን በቦሌ ጎዳና እያሽከረከረ ሲያልፉ አህያ የሚነዳ የሃገርቤት ሰው በስፔኪዮ ይመታል፡፡ ምስኪኑ ባለ አህያ በባለጊዜው ታጋይ ነኝ ባይ ጥፋት መመታቱ ሳያንስ፣አቶ የነፃነት ታጋይ ከመኪናው ወርዶ የሃገርቤቱን ሰውየ በጥፊ ይማታና መኪናውን አስነስቶ ይከንፋል፡፡ይህን አንዳርጋቸው የሆነ ካፌ ውስጥ ሆኖ ያያል፤ይበሳጫል! ሃየሎምን አግኝቶ ያደረገውን እንዳየ ነግሮ፣በራሱ ጥፋት ሰውየውን በጥፊ መምታቱ ጥፋት ስለሆነ ሃየሎም በመገናኛ ብዙሃን ቀርቦ ላደረገው ነገር ይቅርታ እንዲጠይቅ ይሞግታል፤ ሳይሳቅበት አይቀርም፡፡ አንዳርጋቸው እንዲህ ነው! የመርህ ሰው፣ ያወራውን የሚኖር፣ሊበድል ቀርቶ ሲበደል ማየት የማይፈልግ የፍትህ ሰው፣የሰው ክብር እስከነካ ድረስ ጥፊን እንኳን የማይንቅ ሰብአዊነት ከዳር እስከዳር የገባው አዋቂ፣ በአሮጌ ልብስ ውስጥ ያለ ስብዕናን ማክበር የሚችል ጨዋ!
አንዳርጋቸው ሰውን የበደለ ይቅርታ መጠየቅ እንዳለበት ሲሞግት ራሱ የራሱን ጥፋት ለማመን እየተቸገረ አይደለም፡፡ የስልሳዎቹ ትውልድ አባል እንደመሆኑ መጠን ይህ ትውልድ ያኛውን ትውልድ የሚወቅስበትን ጥፋት አምኖ ይቅርታ ለመጠየቅ የሚያስቸግር ትዕቢት የለበትም፡፡ እንደሚታወቀው አንዳርጋቸው በዛ ዘመን እንደማንኛውም ተራ ወጣት ድንጋይ ወርውሮ ይሆናል እንጅ ቀይ ሽብርን ለመመከት ነጭ ሽብርን በማርቀቅ የወንድማማቾችን ደም በማፋሰሱ ፊት አውራሪነት ላይ የተቀመጠ አልነበረም፡፡ ሆኖም መንግስቱ ኃ/ማርያምን ጨምሮ ዋናዎቹ ‘ያደረግነውን ያደረግነው ለሃገር ብለን ነው’ ሲሉ ይቅርታን ይሸሻሉ:: አንድአርጋቸው ግን “አጥፍተናል፤ በማረፊያችን ዘመን ለትግል የምናደርገውን ጥረት እንደ ይቅርታ እጅ መንሻ ቁጠሩል” ብሎ እንደመለሰ በ1997 አካባቢ በአካል ያገኘው የዚህ ዘመን ትውልድ ፅፎ አንብቤያለሁ፡፡
አንዳርጋቸው ልቆ እንዲታየኝ የሚያደርገው ሌላው ስብዕናው የነገሮችን አዝማሚያ ተረድቶ ሚያዋጣውን መንገድ አውቆ ለማሳወቅ የሚለፋ ሰው መሆኑ ነው፡፡አንዳርጋቸው ቆቅ ፖለቲከኛ ነው፡፡ መነሻ እና መድረሻውን፣የፖለቲካ ግቡን፣የትግል መከራከሪያዎቹን ዋና እና ንዑስ ጉዳዮች አሳምሮ የሚያውቅ እንጅ ግማሽ መንገድ ሳይደርስ የደረሰ መስሎት በየመንገዱ ቆሞ የሚነሆልል ተላላ አይደለም፡፡ ወያኔ መራሹ መንግስት ከአባት ገዳይ አምርሮ የሚጠላው ለዚህ ይመስለኛል፡፡የንባቡ ስፋት ለዚህ ሳይረዳው አልቀረም፡፡ከጥልቅ እውቀቱ ቀድቶ ሊያካፍል፣ቀናውን መንገድ ሊመራ ሲያስብ ለማውራት ወደ መድረክ ሳይሆን ለመፃፍ ወደ ወረቀት ያመራል፡፡ከግንዛቤው ጥልቀት የተነሳ ትንታኔዎቹ ሁሉ እንደ ትንቢት የሚቃጣቸው ናቸው፡፡
የፖለቲካ ንፋስን አኳኋዋን አይቶ ቀድሞ መፍትሄ በመጠቆም በኩል በግሌ እንደ አንዳርጋቸው ያለ ፖለቲከኛ አላውቅም፡፡ ሁሌ የሚገርመኝ ይህ ችሎታው በርካታ ቢሆንም ለአሁኑ አንድ ሁለቱን ላንሳ፡፡ የወያኔን ስልጣን ላይ መውጣት ተከትሎ በአማራው ህዝብ ላይ ሊመጣ ያለውን የመከራ ዳመና ተገንዝቦ ስለ አማራ ህዝብ የመደራጀት አስፈላጊነት በወተወተበት በ1985 ዓም የፃፈው “የአማራ ህዝብ ከየት ወደየት?” በሚለው መፅሃፉ ያስቀመጠው ሁሉ (የፊውዳል ዘመን የአማራ መኳንንትን ለብሄርተኝት የነበራቸውን ግንዛቤ ካቀረበበት ነጥብ ላይ ካለኝ ልዩነት በቀር) እየተደመምኩ ያነበብኩት፣አሁን ካለው ሁኔታ ጋር ሳመሳክረው ደግሞ ትንቢት የሚመስለኝ ነው፤የአንዳርጋቸው ስብዕና ገዝፎ እንዲታየኝ ጥልቀቱ  እንዲገርመኝ ካደረጉኝ ብዙ ምክንያቶችም አንዱ ነው፡፡
በዚህ ፅሁፉ ትንታኔው ውስጥ የአንዳርጋቸውን እውነተኛነት፣አንባቢን አክባሪነት ያየሁበት ነው፡፡ በክርክሩ ላይ አንባቢን አላዋቂ አድርጎ አይነሳም፤ይልቅስ አንባቢ ሊያነሳው ይችላል የሚለውን ጠበቅ ያለ ጥያቄ ሁሉ እየመለሰ፣ እንደ እኔ በተወሰኑ ቦታዎች ላይ ልዩነት ያለው አንባቢ ካለም ለእምነቱ እየተወ ብዙ ያስተምራል፡፡ በነገራችን ላይ በዚህ መፀሃፉ ምክንያት ብዙ የአማራ ብሄርተኝነት አቀንቃኞች ከወያኔ እኩል እንደሚጠሉት አውቃለሁ፤ጭራሽ የአማራ ህዝብ ጠላት አድርገውት ቁጭ ይላሉ(በዚህ ጉዳይ ላይ መፅሃፉን ዳስሼ የታየኝን ለማሳየት ከሶስት ቀን ባልበለጠ ጊዜ የምመለስ ይሆናል)፡፡
ሁለተኛው ትዝብቴ ወያኔ መራሹ መንግስት በምርጫ ስልጣን ለማስረከብ የሚያስችል ቅንነትም ፣ዝግጁነትም፣ተፈጥሮም እንደሌለው ተገንዝቦ ለዲሞክራሲ የሚደረገው ትግል ሌላ መልክ መያዝ እንዳለበት መርምሮ የተረዳበት ወቅት ነው፡፡ያኔ ለ1997 ምርጫ የኢትዮጵያ ህዝብ ሁሉ የወያኔ መንግስት በምርጫ እንደሚወገድ ተስፋ አድርጎ ለዚሁ በሚለፋበት ሰዓት አንዳርጋቸው በመሃል አዲስ አበባ ሁለገብ ትግሉን ለማድረግ የሚያስችል ጥንስስ እየጠነሰሰ እንደ ነበረ “ሰባት ኪሎ” የተባለች መፅሄት “አንዳርጋቸው ያችን ሰዓት”በሚል ርዕስ ስር አስነብባ ነበር፡፡ ይህንኑ ያወቀው የወያኔ መንግስት አንዳርጋቸውን አስሮ ራሱን እስኪስት አስደብድቧል፣በቅንጅቱ ዋና የምርጫ አስተባባሪ የነበሩት ፕ/ሮ ብርሃኑ ነጋንም ‘አንተ የማታውቀው ተንኮል እየተሰራ ነው’ እያሉ ግራ ያጋቡት እንደነበር “የነፃነት ጎህ ሲቀድ” በሚለው መፅሃፋቸው ገልፀዋል፡፡ አንተ የማታውቀው ተንኮል ማለት እንግዲህ ክሱቱ የአንዳርጋቸው ነገሩ ገብቶት አማራጭ የትግል መንገድ ለማፈላለግ ዳርዳር ማለቱ ነበር፡፡ አንዳርጋቸው ይህን አማራጭ የትግል መስመር ለትግል ጓዶቹ (ፕ/ሮ ብርሃኑን ጨምሮ) ለማስረዳት እና ለማሳመን ብዙ እንደተቸገረ ይህችው ሰባት ኪሎ መፅሄት በጥሩ አቀራረብ አትታ ነበር፡፡ አንዳርጋቸው እንዲህ ቀስ ብሎ የሚገባን ጥልቅ ፣አንብበን ያልጨረስነው ነገር ግን በአልባሌዎች እጅ አልባሌ ቦታ የተጣለ ሃብታችን  ነው፡፡ የዚህን ውድ ሃብታችንን መፈታት የሚጠይቅ ከቀጣዩ ሰኞ ጀምሮ እስከ ሮብ የሚቆይ የማህበራዊ ድህረ-ገፅ ዘመቻ ስላለ አንባቢ ዘመቻውን እንዲቀላቀል በኢትዮጵያ አምላክ ስም እጠይቃለሁ !
Filed in: Amharic