>

"እኛ ቤት ጀግና አለ ከተባለ ጀግናዋ ማን እንደሆነች ዛሬ ተረጋግጧል"  (እስክንድር ነጋ)

አቤል አለማየሁ
ማንኛውም ድርጊት እንዲከወን አጋዥ ኃይል ያስፈልገዋል።  ወደ ሰላማዊ የትግል መድረክ መጥተህ ጎርበጥባጣውን ለማለፍ ደግሞ የአጋር ጠቀሜታ ወሳኝ ነው። እንደ ናትናኤል መኮንን አንዱአለም አራጌ ባለቤት ዓይነት የብረት ማገር ለመሆኗ በአደባባይ የተመሰከረላት አጋር የመኖሯን ያህል በተቃራኒው ደግሞ በእስር ላይ እያሉ ትዳራቸው የፈረሰ፣ ቤተሰባቸው የተበተነ ታዋቂ የፖለቲካ ታጋዮች አሉ።
 ሠርካለም ፋሲል
ይህቺ ሴት ከብረቶቹ ተርታ የምትመደብ እውነተኛ አጋር ናት።  በእስኬው የእስር ዘመን ድምጹ ሆና ብዙዎች ጋር ደርሳለች። በጀግና ባሏ ጥላ ሥር ሆና ራሷን ለማጉላት ሞክራ አታውቅም። ሁሌም ርዕሷ ባሏ እና ኢትዮጵያዊ ጉዳይ ነው። ለልጇ ስትል አካሏ እዚያ ሆነ እንጂ ነፍሷ ያለው እዚህ ነው – እስኬውጋ።
    ሠርኬ ልጅ የማሳደግ ኃላፊነት ከበደኝ ብላ እስኬው አጠገቧ እንዲሆን አትጎተጉተውም። የሕዝብ አደራ እንዳለበት ስለምታውቅ ለዓመታት ያጣችውን ግማሽ አካሏን ሳትጠግበው ወደ አገሩ ለመሸኘት ቃል ገብታለች። ትላንት እስክንድር ዋሽንግተን ዲሲ እንደደረሰ ሠርኬ “ልጃችሁ እዚህ አይቀርም መልሼ እልከዋለሁ።” ስትል ቆፍጣና የዴሞክራሲ አጋር መሆኗን አሳይታለች። በሁላችን ልብ የነገሰው፣ የፖለቲካ አክቲቪስቱ እስክንድር ነጋም “እኛ ቤት ጀግና አለ ከተባለ ጀግናዋ ማን እንደሆነች ዛሬ ተረጋግጧል” አክብሮቱን እና ምስክርነቱን ሰጥቷታል። ጥሩ የቤተሰብ ጊዜ ይሁንላችሁ!
Filed in: Amharic