>

የተፈናቃይ አባወራዎች ጥፋት አማራ መሆናቸው ብቻ ነው!  (አቻምየለህ ታምሩ)

የሕወሓቱ ነውረኛ ድርጅት ብአዴን ላለፉት 27 አመታት አማራ ባገሩ ስደተኛ ሆኖ ሲፈናቀልና ሲገደል ለይምሰል እንኳ መግለጫ አውጥቶ አያውቅም። ነውረኞቹ ብአዴዎች ውክልናቸው የትግራይ እንጂ የአማራ ስላልሆነ የአማራ ጉዳይ አይመለከታቸውም።
ባለፈው ጥር ወር ላይ ግን  በወልድያ፣ በቆቦና በመርሳ የትግራይ ነፍሰ በላ ወታደሮች አማራ ሲጨፈጭፉና አማራ ራሱን የመከላከያ ርምጃ ሲወስድ ሁሉም የብአዴን ድርጅታዊ መዋቅሮች መግለጫ አወጡ።  የብአዴን ቃል አቀባዩ Nigussu Tilahun፣ እንደራሴው ገዱ አንዳርጋቸው፣ የአማራ ክልል ምክር ቤት ተብዮው፣ የነውረኛው ብአዴን ስራ አስፈጻሚና የማዕከላዊ ኮምቴ አባላት  በሙሉ የትግራይ ተወላጆች ተጠቁ ብለው የተጨፈጨፈውን አማራ የሚያወግዝ መግለጫ በሬዲዮ፣ በጋዜጣና በቴሌቭዥን አስተላለፉ።
አማራ ሲፈናቀልና ሲሰደድ፣ ሲገደልና ሜዳ ላይ ሲጣል ግን ባለፈው ጥር ወር  ለገዳይ የትግራይ ወታደሮች አዝነው  መግለጫ ያዥጎደጎዱት  እነ ንጉሱ ጥላሁን፣ ገዱ አንዳርጋቸው፣ የአማራ ክልል ምክር ቤት ተብዮው፣ የነውረኛው ብአዴን ስራ አስፈጻሚና የማዕከላዊ ኮምቴ ትንፋሻቸው የለም። እንዴውም በተቃራኒው በክህደት ተሰማርተው ከጎጃም መተከል የተፈናቀሉትን አማሮች   የመለስ ዜናዊን አገላለጽ በመጠቀም  «ሕገ ሰፋሪዎች» በማድረግ እየወነጀሏቸው ነው።
ከታች የታተሙት  ፎቶዎች «ሕገ ወጦች» ተብለው  የተፈናቀሉት  አማሮች የተፈናቀሉበት ምድር  «የመሬት ይዞታ  ማረጋገጫ» ደብተሮች ናቸው።  እነዚህ ደብተሮች አገርና መንግሥት አልባ ሆነው ባህር ዳር አባይ ማዶ  ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ቅጥር ግቢ ውስጥ ተጠልለው የሚገኙ ተባራሪ  አርሷደሮች  የተባረሩበት መሬት «የመሬት ይዞታ  ማረጋገጫ» ደብተሮች ናቸው። ይህ በግልጽ የሚያሳየው አባወራዎቹ የተባረሩት አማራ ብቻ በመሆናቸው ብቻ እንደሆነ ነው።
በተያያዘ – ጌታቸው ሽፈራው
ኮማንድ ፖስቱ ተፈናቃዮች ቤተክርስትያን ግቢ ውስጥ እንዳያድሩ ከልክሏል ተብሏል
~”የተቸገረ ሰው ከእግዚያብሔር ቤት ውጣ አይባልም” አቡነ አብርሃም
ባህርዳር የሚገኙት ተፈናቃዮችን ወደ አማራ ክልል የመጡት ከታህሳስ ወር 2010 ዓም ጀምሮ ነው!
~ለሶስት ቀን ያህል የኦሮሚያ ክልል መንግስት እገዛ አድርጎላቸዋል። የአማራ ክልል መንግስት ያደረገላቸው እገዛ እንዳልነበር ገልፀዋል። የተወሰኑ ሟቾችን አስከሬን ወደ ቤተሰቦቻቸው የላከው የኦሮሚያ ክልል መንግስት ነው።
~ወደ ቤንሻንጉል ተመልሰው ለአንድ ወር ቆይተዋል። ለአንድ ወር ያህል ቀይ መስቀል እገዛ አድርጓል። በዚህ ወቅት ወደቀያቸው ይመለሳሉ ተብሎ ቢታሰብም የቤንሻንጉል ክልል መንግስት “ለቅቃችሁ ካልወጣችሁ ለህይወታችሁ ተጠያቂ አልሆንም” የሚል ማስፈራሪያ አደረሳቸው። ቀይ መስቀልም እገዛውን አቆመ
~ወደ ባህርዳር እንደመጡ መግቢያ ሲያጡ ወደ ገብርኤል ቤተ ክርስትያን ነበር ያቀኑት። ሆኖም አንድ ቀን እንዳደሩ ኮማንድ ፖስቱ ቤተ ክርስትያን ውስጥ እንዳያድሩ ከልክሏል ተብለው ከቤተ ክርስትያን ተባርረዋል
~ከገብርኤል ቤተ ክርስትያን ሲባረሩ ወደ ሚካኤል ቤተ ክርስትያን አቀኑ። ሁለት ቀን እንዳደሩ በተመሳሳይ ምክንያት ተባረሩ
~አሁንም ወደ ሌላ ቤተ ክርስትያን ከመሄድ ውጭ አማራጭ አልነበራቸውም። ወደ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስትያን ሄደው አቡነ  አብርሃም እግር ተደፉ። አቡነ አብርሃም እንዲነሱ ጠየቋቸው። ከየ ቤተክርስትያኑም “ውጡ” ሲባሉ የሰነበቱት ምስክኖች፣ አቡነ አብርሃምን ከጊዮርጊስ ቤተ ክርስትያን እንዲያስጠልሏቸው፣ “አስወጡ” ከተባሉም እንዳያስወጧቸውም ለመኗቸው። አቡነ አብርሃምም “ክፉ ሰርታችሁ መጥታችሁ ከሆነ እንዳታሳፍሩኝ፣ ተገፍታችሁ ከመጣችሁ ግን ቤተ ክርስትያን ለተገፉት መጠለያ ነች” ብለው አስገቧቸው። እራትም እንዲበሉ አደረጉ።
~አንድ ቀን አድረው ግን ተመሳሳይ ጫና መጥቷል። አቡኑ ግን አላስወጧቸውም። “እኛ ከመንግስት አንበልጥም። ግን ይህ ቤተ ክርስትያን ነው። የእግዚያብሔር ቤት ነው። የተቸገረ ሰው ከእግዚያብሔር ቤት ውጣ አይባልም። ……” ብለው እንዳይወጡ እንዳደረጉ ተፈናቃዮቹ ገልፀውልኛል። አሁን በጊዮርጊስ ቤተ ክርስትያን  ግቢ ውስጥ ተጠልለው ይገኛሉ!
ከቀያቸውም ተባርረው፣ ከእግዚያብሔር ቤትም እየተባረሩ ይገኛሉ! የቀጣይ እጣቸውም አስጊ ነው!
Filed in: Amharic