>
5:14 pm - Monday April 20, 3040

የዶ/ር አብይ ቀናኢነትና የአንድነት ኃይሉ ማፈግፈግ  (ሞሀመድ አሊ መሀመድ)

– ስለአንዳርጋቸው መጮህና ምፀቱ!

– የአል-በሽር ምላሽና አንደምታው;

“የኢፌድሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድ በሱዳን የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን እስረኞች እንዲለቀቁ ባቀረቡት ጥያቄ መሰረት የሃገሪቱ ፕሬዝዳንት ኦማር ሃሰን አልበሽር ኢትዮጵያዊያኑ እንዲፈቱ ወሰኑ”
ይህ ዜና በሁሉም ብዙሃን መገናኛዎች እየናኘ ሲሆን ድብቅልቅ ያለ ስሜት ፈጥሮብኛል። በአንድ በኩል ከቤተሰብና ከዘመድ ርቀው በሰው አገር እሥር ቤት ሲማቅቁ የነበሩ ወገኖቻችን በመፈታታቸው ተደስቻለሁ። ዶ/ር አብይ አህመድም ከተለመደው ዲፕሎማሲያዊ የቃላት ጨዋታ ባለፈ በእሥር ላይ ለነበሩ ወገኖቻችን ትኩረት ሰጥተው ጥያቄውን ማቅረባቸው; እንዲሁም የሱዳኑ ፕሬዝዴንት ሀሰን ዑመር አልበሽር ጥያቄውን ተቀብለው አፋጣኝ ውሳኔ መስጠታቸው አስደምሞኛል።
በርግጥ የሱዳን መንግሥት ቀደም ብሎ በሀገሩ ያሠራቸውን የፖለቲካ እስረኞች ሙሉ በሙሉ መፍታቱን ሰምተናል። በአንፃሩ የኢትዮጵያው ገዥ ፓርቲ ኢህአዴግ የፖለቲካ እስረኞችን ሙሉ ለሙሉ ለመፍታት መወሰኑን ቢያበስረንም የነፃነት ታጋዩን አቶ አንዳርጋቸው ፅጌን ጨምሮ በርካታ የፖለቲካ እስረኞች እስካሁን ድረስ በእሥር  ቤት እየማቀቁ ነው።
እዚህ ላይ አነጋጋሪው (ironic) ጉዳይ ዶ/ር አብይ የኢትዮጵያ መሪ ሆነው አገራቸው ላይ መፈፀም ያልቻሉትን የጎረቤት አገር መሪ ተማፅነው ማስፈፀም መቻላቸው ነው። ከዚህ ተነስተን ዶ/ር አብይ እንደ አንዳርጋቸው ፅጌ ያሉ አገር ወዳድ ዜጎች የበቀል ፖለቲካ ሰለባ መሆናቸው ሳያሳስባቸው ቀርቶ ነው? ወይስ እንደ ሱዳኑ መሪ የመወሰን ሥልጣን የላቸውም? የሚል ጥያቄ ለማንሳት እንገደዳለን።
ሰሞኑን ከቤተ-መንግሥት አካባቢ እንደተናፈሰው ወሬ ከሆነ ዶ/ር አብይ ራሳቸው የበቀል ፖለቲካው ሰለባ ከመሆን ለትንሽ ነው የተረፉት። ስለሆነም ሀገርን መውደድና ከሥርዓቱ የተለዬ አቋም መያዝ ምን ያህን ዋጋ እንደሚያስከፍል ከዶ/ር አብይ በላይ ማን ምስክር ሊሆን ይችላል? ሀቁ ይኸ ከሆነ የዶ/ር አብይ መንግሥት እነ አንዳርጋቸው ፅጌን የማይፈታው ለምንድነው? ምንስ እስከሚሆን ነው የሚጠበቀው?
ከዚሁ በተጓዳኝ ዶ/ር አብይ ኢትዮጵያዊነትን ለመስበክና በዚህ ዙሪያ ገዥ አስተሳሰብ ለመፍጠር የሚያደርጉትን ጉዞ ቀጥለው አሶሳ ላይ ህዝብን ሲያወያዩ በሌላ በኩል የአማራ ተወላጅ የሆኑ ዜጎች ከቤኒሻንጉል ክልል እንዲወጡ እየተደረገ ነው። ዶ/ር አብይ የኢትዮጵያዊነትን አስተሳሰብ ከላይ ለመደረብ ሲታገሉ ጠባብ ብሔርተኞች ከሥር እርቃኑን እያስቀሩት ነው። የነዶ/ር አብይን ተነሳሽነት አፈር ለማልበስ እርምጃቸውን እየተከተሉ ከሥር ከሥር ጉድጓዳ የሚምሱትና አካፋና ዶማ የሚያቀብሉት እነማን ናቸው?
በዚህ ሁኔታ TeamLemaና ዶ/ር አብይ የሚያቀነቅኑት ኢትዮጵያዊነት ዕጣ ፈንታው ምን ይሆናል? በተለምዶ የአንድነት ኃይል ሲባል የነበረው የማህበረሰብ ክፍል የነለማን ቅን ተነሳሽነትና ገንቢ ትርክት (constructive rhetoric) በወጉ ማስተጋባትና ማበረታታት ለምንና እንዴት አቃተው? ወይስ አጥብቆ ያልያዘውን የአንድነት አስተሳሰብ እንደዋዛ ተነጠቀ?
በሌላ በኩል የትግራዩ ጠባብ ብሔርተኛና መሰሎቹ ይዘውት የተነሱት አስተሳሰብ አሸናፊ ሆኖ እየወጣ ይሆን? የሚል ጥያቄ ማንሳትም ምክንያታዊ ነው። ሁሉም የየራሱን ሰበብ (excuse) በማበጀት ጠባብ ብሔርተኞች በቀደዱት ቦይ የሚፈስ ከሆነ ወደፊት ህወሓትንና የአስተሳሰቡን አቀንቃኞች መክሰስና መውቀስ የሚቻልበት መነሻ (ground) አይኖርም።
በዚህ መሐል የአያት ቅድመ-አያቶቻችንን ውለታ አፈር በላው። ወይም ደግሞ ትውልዱ የአያት ቅድመ-አያቶቹን “አደራ እየበላ ነው” ማለት ይቻላል። ይህች ሀገርኮ በጀግኖች አያት ቅድመ-አያቶቻችን አጥንትና ደም የተገነባች ናት። ለዚች አገር አንድነትና ነፃነት ሲባልኮ ብዙ ደም ፈስሷል; አጥንት ተከስክሷል። ዛሬ ላይ በጠባብ ብሔርተኝነት ስሜት ተሸብበን በአያት ቅድመ-አያቶቻችን መቃብር ላይ ሽምጥ እየጋለብን ነው። ግን የጆግኖቻችንን አፅም እየረገጥን እንዴት ነው የምንዘክራቸው?
ባይሰማን እንጅ ደማቸው ይጮህ; ነፍሶቻቸው ይጣሩና አጥንታቸውም ይወቅሰን ይሆናል። ለእኛ ግን ዛሬ ላይ ይኸ ሁላ ምናችንም አይደል! እነሱ የገነቡትን  ማፍረስና ህልምና ራዕያቸውን ማጨንገፍ የቁልቁለት መንገድ ነው። እስቲ የሩቁን እንተወውና ኢትዮጵያን አንድ ለማድረግ የተነሳው ቴወድሮስ ህልሙ ምን ነበር? ዮሃንስ መተማ ላይ አንገቱን የሰጠው ለምን ነበር? እምዬ ምኒልክ ዕድሜውን ሙሉ የኳተነው ለምን ነበር? የነራስ አሉላ; ባልቻ አባነፍሶ; በላይ ዘለቀ. .. ህልምና ምኞት ምን ነበር?
ከዚያስ ወዲህ ስንቱ ጀግና ጎበዝ “ኢትዮጵያ ወይም ሞት” ብሎ; ፎክሮና አንጎራጉሮ ክንዱን ተንተራሰ? ስንቱ ቤቱን ዘግቶ እንደወጣ ቀረ?  በምሥራቅ; በምዕራብ; በደቡብ; በሰሜን ስንት ደም ፈሰሰ? ዛሬም ቢሆን ብዙዎች የሀገር ፍቅር ዋጋ እየከፈሉ ነው።
እስቲ አንዳርጋቸው ፅጌን እናስበው? አንዳርጋቸው ዕድሉን ቢያገኝ “አደራው” ምን ሊሆን ይችላል? ለምንድነው ይህን ሁሉ መከራና ስቃይ የሚቀበለው? ጊዜው ሲደርስ ራሱ ይነግረናል።
“ላንች ነው ኢትዮጵያ” እያለ ይዘምርልናል።
አንዳርጋቸውን ከቆመለት ክቡር ዓላማ ለይቶ መውደድ አይቻልም። የአንዳርጋቸውን አደራ ደጋግመን ብንጠይቀው “ኢትዮጵያን. ..” የሚል ይመስለኛል። የአንዳርጋቸውን አደራ ቅርጥፍ አድርጎ በልቶ ስለአንዳርጋቸው መጮህ አጉል ምፀት ነው።
ይሁንና አንዳርጋቸውን ፍቱት!!!
Filed in: Amharic