>
5:14 pm - Monday April 20, 3311

"የድሮ ፕሬስ ናፋቂው" ፍቃዱ (ቢቢሲ አማርኛ)

ፍቃዱ ማኅተመወርቅ የ4 ኪሎ ልጅ ነው። በጋዜጣ ልክፍት የተመታው ገና ድሮ በብርሃንና ሰላም በኩል ሲያልፍ ነው። ተማሪ ሳለ።

ለነገሩ የመንግሥት መቀመጫ ብቻ አይደለችም፤ አራት ኪሎ። ፕሬሱም እዚያው ነው የከተመው። የጉምቱው ማተሚያ ቤት ማደሪያ፣ የጋዜጣ ቸርቻሪዎች መናኸሪያ…።

በ4 ኪሎ እንኳን አንድ መኝታ፣ ግንጥል ጋዜጣም ይከራያል።

ፍቃዱ ታዲያ የጋዜጣ መንፈስ በአያሌው የተጫናት ሰፈሩን ይወዳታል። ጋዜጦቿንም እንዲሁ።

መጀመርያ በደጃፉ እንደ ጅባ ተነጥፈው የሚሸጡ የኅትመት ውጤቶችን ገርመም አድርጎ ማለፍ ጀመረ። አንስቶ መሸጥ ገቢ እንደሚያመጣ ሲረዳ ከትምህርት ቤት መልስ እንደ ጀብድ ጋዜጣ ማዞር ጀመረ።

ከማንበብ ወደ መሸጥ፣ ከመሸጥ ወደ ማከፋፈል…። የኋላ ኋላ የአገሪቱ ሁነኛው የጋዜጣ አከፋፋይና ወኪል ሆነ። ዛሬም ድረስ የአገሪቱ ዋና ዋና ጋዜጦችና መጽሔቶች በእርሱ በኩል ነው የሚያልፉት።

በዚያ ላይ አሳታሚም ነው።

ለምሳሌ ኅትመቷ ተቋርጦ አዘጋጆቿ የተሰደዱባት “ዕንቁ”፣ የቴዲ አፍሮን አወዛጋቢ የፍርድ ሂደት በማተሟ በፖሊስ የተወረሰችው “ሐምራዊ”፣ አሁን በገበያ ላይ ያለችው “ግዮን” ሁሉም የፍቃዱ መጽሔቶች ናቸው።

“ታስረህ ታውቃለህ፣ ፍቃዱ?”

“ፕሬስ ውስጥ እየሠራ እስር ያልቀመሰ ይኖራል ብለህ ነው?”

ለነገሩ እንኳን እርሱ መጽሔቱም ታስራ ታውቃለች። “የቴዲ አፍሮን የፍርድ ቤት ሙሉ ዘገባ የያዘችው ባለ ሙሉ ቀለሟ “ሐምራዊ” መጽሔት ለ3 ወራት አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ውስጥ ታግታ ቆይታ ነው ኋላ ላይ የተፈታችው።”

ፍቃዱ የክስ ዶሴው ስላልተዘጋ ዛሬም ድረስ እያሰለሰ ፍርድ ቤት መመላለሱን አልተወም።

ለመቶ ሚሊዮን ሕዝብ 3 ጋዜጣ?

ፍቃዱ የቀድሞውን ፕሬስ ናፋቂ ነው። በ80ዎቹ መጨረሻና በ90ዎቹ መጀመሪያ ስለነበረው የኢትዮጰያ ፕሬስ አውርቶ አይጠግብም።

“ያኔ እኮ. . . ከሰኞ እስከ ሰኞ ጋዜጣ ነበረ፤ ከሰኞ እስከ ሰኞ መጽሔት ነበረ። በቀን እስከ 8 ዓይነት ጋዜጣና መጽሔት አማርጠህ ታነባለህ። አዲስ አበባ ብቻ ከሺህ በላይ አዝዋሪዎች በየቀኑ ጋዜጣና መጽሔት ይዘው ይርመሰመሱ ነበር። አሁን እኮ ሁለት መቶ አይሞሉም፣ ይሞላሉ?” ሲል ይጠይቃል።

በፕሬስ ሕይወቱ የማይረሱትን ቀናት ሲያስታውስም እነ ኢትኦጵን፣ እነ አባይን፣ እነ ጦቢያን፣ እነ አሌፍን ያነሳሳል። ድሮና ዘንድሮን እንዲያወዳድር ሲጠየቅ ግን ሳቅ ይቀድመዋል። “ምነካህ!” ብሎ ነው የሚጀምረው፣

“…የታተመ ጋዜጣ እኮ አልቆ በድጋሚ ለማሳተም ከማተሚያ ቤት አቅም ሁሉ በላይ ሆኖ፣ ጋዜጣ ፎቶ ኮፒ እያደረግን የሸጥንበት ዘመን ነበረ። ይሄንን ብዙ ሰው የሚያውቅ አይመስለኝም።”

ፍቃዱ በተለይ 90ዎቹ መጀመሪያ ከአገር ስለሚባረሩ ኤርትራዊያን፣ እንዲሁም ስለ ሕወሓት ክፍፍል ዘገባ ይዘው የወጡ ጋዜጣና መጽሔቶች አይረሱትም።

ኢትኦፕ በቀን ሁለት ጊዜ ማተሚያ ቤት መግባቷን ያስታውሳል። “ለዚያውም 180ሺህ ኮፒ ተጠይቆ፣ ማሽን አልችል ብሎ፣ 130ሺ ብቻ ታትሞ ወጥቶ አከፋፍያለሁ” ይላል።

ቅዳሜ ከሚወጡት ውስጥ ደግሞ አባይ ጋዜጣን አይረሳትም።

“ማተሚያ ቤት ከመጥፋቱ የተነሳ። ይሄን ያህል ማተም አንችልም ብለውን እኮ አንድ ጋዜጣ ሦስት የተለያዩ ማተሚያ ቤቶች እንዲታተም ተደርጓል።”

አሁንስ?

ፍቃዱ የዘንድሮን የአንድ ጋዜጣ አማካይ የኅትመት መጠን ሲጠየቅ ቁጥሩን ከመናገር ይልቅ ዝምታን ይመርጣል።

“ለመቶ ሚሊዮን ሕዝብ በሳምንት ሦስት ጋዜጣ እየታተመ. . . ምኑን ትጠይቀኛለህ?”

አራት ኪሎ

ግማሽ ተስፋ

ጠቅላይ ሚኒስትሩን ሰምቷቸዋል፥ ፍቃዱ። ለዚያውም በጥሞና። ውጭ ያሉ ሚዲያዎች አገር ቤት ቢሯቸውን እንዲከፍቱ እንፈልጋለን ማለታቸውን በግማሽ ተስፋ ነው የሚመለከተው።

“…ሰውየው ከኢህአዴግ ውስጥም የወጡ አይመስሉም። 27 ዓመት ስለ አንድነት ተወርቶልን አያውቅም፣ 27 ዓመት ስለ ፍቅር ተወርቶ አያውቅም፤ ስለ አንድነት ተወርቶ አያውቅም። ዶክተር ዐብይ ይለያሉ፤ የሰጡት ተስፋ ጥሩ ነው፤ ወደ መሬት ከወረደ…።”

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግር የምር እንደሆነ ለማረጋገጥ ግን ፍቃዱ ቢያንስ ቢያንስ በጋዜጠኞች ላይ የተከፈቱ ክሶች ሲዘጉ፣ መንግሥታቸው ለግል ፕሬሱ መረጃ መስጠት ሲጀምር ማየትን ይሻል።

“ፕሬሱ ከድሮም ለአገሩ ይቆረቆራል። አገርን ይወዳል። ግን ለፕሬሱ አንድም ቀን ከጎንህ ነኝ የሚል መንግሥት አልመጣም። እንደ ጠላት ነው የሚታየው። እስኪ ብቻ የሚሆነውን ማየት ነው…” ይላል በግማሽ ተስፋ እየዋለለ።

እነ ሚሊዮን ሹሩቤ፣ እነ ኢብራሂም ሻፊ

ፍቃዱ የቀድሞ የፕሬስ ጓደኞቹን ሲያስታውስ ድምጹ ቀስ በቀስ ሐዘን እየተጫነው ይመጣል። ደልቶት የኖረ አንድም የነጻው ፕሬስ አባል እንደሌለ ሲያስብ፥ ለሞያው ሲሉ ቁም ስቅል ያዩ ስፍር ቁጥር የሌላቸው ወዳጆቹን ሲያስታውስ ትካዜ ይገባዋል።

“…ተደጋጋሚ ክስ ተመስርቶባቸው ራሳቸውን ያጠፉ ልጆችም አሉ። ‘ዘውግ’ የሚባል መጽሔት ውስጥ የሚሠራ ልጅ፣ መኮንን የሚባል ማዕበል ጋዜጣ ላይ የሚሠራ ልጅ፣ ሞተዋል። በስደት እያሉ የሞቱም አሉ። እነ ሚሊዮን ሹሩቤ፣ እነ ኢብራሂም ሻፊን ማንሳት ትችላለህ። እዚሁ ሳይሰደዱ ተቸግረው የሞቱ ብዙ የማውቃቸው ልጆች አሉ። ብቻ ያሳዝናል…”

ያም ሆኖ ፍቃዱ ተስፋ ያደርጋል። ከአዝዋሪነት እስከ አሳታሚነት ግማሽ ሕይወቱን ያሳለፈበትን ፕሬስ፤ እነ አስክንድር ነጋን የፈጠረ ፕሬስ፣ ዛሬ እያጣጣረ ያለ የሚመስለው ፕሬስ ወደፊት ቀን እንደሚወጣለት ተስፋ ያደርጋል። የከሰመው ፕሬስ እየተፋፋመ እንጂ እየከሰመ እንደማይቀጥልም ይናገራል።

“የኢትዮጵያ ፕሬስ እንደ ድሮው አብቦ ማየት ነው ምኞቴ፣ ገብቶሀል? እንደድሮው ያልኩህ፤ እንደ አዲስ ማበብ ስለማይጠበቅበት ነው። ወደ ድሮው ዕድገቱ እንዲመለስ ነው ምኞቴ።”

“ከዚህ ሁሉ ዓመት በኋላ እንዴት ተስፋ ታደርጋለህ?” ሲባል፣ “…ምክንያቱም ጋዜጠኝነት ልክፍት ነው፤ የነጻነት ልክፍት፣ ተስፋ የማድረግ ልክፍት…።”

Filed in: Amharic