>
5:13 pm - Saturday April 19, 6138

እውን ኢትዮጵያዊነት ተሸንፏል??? (ብርሀኑ ተክለ ያሬድ)

ምስጋና በደማቸው ፍሳሽ በአጥንታቸው ክስካሽ ውዷን ሀገራችንን ላቆዩልን አበው ጀግኖች ይሁንና ከእነሱ አብራክ የተወለድን ልጆቻቸው ይቺ ውዷን ሀገር ዛሬ ከተጫነባት የአምባገነንነት የዘረኝነትና የድህነት አረንቋ ለማውጣት የአባቶቻችንን ተጋድሎ እየጠቀስን በየፊናችን መታተር ከጀመርን ሁለት አስርታትን አስቆጠርን ታዲያ የእኛ ትውልድ ተጋድሎ ስለምን ሁለት አስርታትን ወሰደ? ዛሬስ ትግሉ በጎመራበትና ህዝቡ የትግሉ ባለቤት እየሆነ በመጣበት ሁኔታ ስለምን የልዩነታችን አጀንዳ ከአንድነት አጀንዳችን በላይ ጎልቶ ታየ? የትግላችን መንገድስ የሚወስደን ወደምንናፍቀው ታላቅነት ወይስ ወደ መለያየት? የሚሉ ጥያቄዎች በትውልዱ ልሒቃንና በህዝቡ ውስጥ ይመላለሳሉ በእርግጥ ለእነዚህ ጥያቄዎች ሙሉ በሙሉ መልስ ማግኘት የሚቻል ባይሆንም አሁን እየታዩ ካሉ ምልክቶች በመነሳት ለጥቂቶች ጥያቄዎች ግምቶችን ማስቀመጥ ይቻላል፡፡ የዚህ ጽሁፍ አላማ ለእነዚህ ጥያቄዎች መልስም ግምትም መስጠት ሳይሆን በአሁኑ ወቅት በሩቅ ለምናየው የለውጥ እና የነጻነት ጭላንጭል እንደጎታች ሆኖ እየታየ ላለው ‹‹ትግሉ ህብረ ብሔራዊ መሆን አለበት ወይስ ብሔራዊ?›› ለሚለው ፖለቲካዊ ውርክብ የመፍትሔ ሀሳብ ማቅረብ ነው፡፡
ወቅቱ የተጧጧፈ ትግል እያደረግን ያለንበት ጊዜ ነው በዚህ የትግል መንገድ ውስጥ ደግሞ ህብረ ብሔራዊ/ሀገራዊ ድርጅቶች፣ ግንባሮች፣ ንቅናቄዎች ተሰልፈዋል በሌላው ገጽም እንዲሁ ብሔራዊ/ክልላዊ ፓርቲዎች፣ ንቅናቄዎችና ግንባሮች ይገኛሉ የእነዚህ የጋራ ጠላት የሆነውን አምባገነኑን ኢህአዴግን ስንጨምር ደግሞ አሰላለፉን ወደ 3 ጎራ እንከፍለዋለን ማለት ነው ታዲያ በዚህ የአሰላለፍ ስልት ውስጥ የምናደርገው ትግል ወዴት ይመራናል? የምንናፍቀውን ነጻነትስ እንዴት ማምጣት ይቻለናል? በማለት ቆም ብለን ትግላችንን እንድንመረምር የምንገደድበት ወሳኝ ወቅት ላይ በመሆናችን ትግሉ ኢትዮጵያዊነትን ብቻ ተላብሶ እንዲካሔድ የሚያደርጉንን ጥቂት መግፍኤዎችን ለመመልከት እንሞክራለን፡፡
ኢትዮጵያዊ ትግል ምንድነው?
ይህን ጥያቄ ማንሳት ያስፈለገው ብዙ ሊቃውንት ዘርዝረው ሊዘልቁት ያልቻሉትን ኢትዮጵያዊነት በዚህ አጭር ጽሁፍ ለመግለጽ አይደ ለም ይልቁኑ ወቅቱ የሚጠይቀውን ትግል በኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነት ውስጥ በማካተት ከብሔር ድርጅቶች ግንባሮችና ንቅናቄዎች ይልቅ ህብረ ብሔራዊ ተቋማት በሰፊው ትከሻቸውና በሁሉን አቀፍ ተደራሽነታቸው የለውጡን መንገድ ይመሩት ዘንድና ሀገር የማዳን ተልእኮአቸውን ይወጡ ዘንድ ጥቁምታ ለመስጠት ያህል ነው፡፡
 ኢትዮጵያዊው ፈላስፋ አለቃ ዘነብ‹‹ አንድ አይንና አንድ አይን ያላቸው ተጋብተው ሁለት አይን ያለው ልጅ ወለድ ይህ ነገር ምንድነው አንዱ ከእናቱ አንዱ ከአባቱ ነዋ› እንዳለው ምሉዕ የሆነ ታሪክ፣ ባህል፣ እሳቤ፣ ወ.ዘ.ተ. ያለው ህዝብ የለም ይህን ሁሉ የሚያሟላውና ብቁ ትውልድ መፍጠር የሚችለው አንዱ ከአንዱ ጋር በአብሮ መኖር ውስጥ በሚወርሳቸው መልካም እሳቤዎች፣ ወጎችና ልማዶች ነው፡፡ የምንኖርባት አለም አሁን ባለችበት ደረጃ የተገኘችውም ይህንኑ ማህበራዊ ቅልቅልና መስተጋብር መሰረት በማድረግ ነው፡፡ ስለሆነም ኢትዮጵያዊነትን ባጭሩ ስንገልፀው “በረጅም የታሪክ ሂደት ውስጥ በህዝቦች ልቦና ውስጥ ታምቆና ተዳፍኖ የሚኖር ጊዜያዊ ወጀቦች የማያጠፉት መንፈስ›› ነው፡፡ ይህም ማለት እንደ አባይ በአሸዋ ውስጥ የሰረገ እየመሰለ ብቅ የሚል፣ እንደ አልአዛር ሞቶ የሚነሳ፣ ይህ ነው ብለው ሊገልጹትና ሊያሳዩት የማይችሉት ግን በሁሉ ልቦና ውስጥ የሚመላለስ ማለት ነው፡፡ ዛሬ ዜጎች ከዚህ እንደ እሳተ ጎሞራ ከሚፍለቀለቅ የኢትዮጵያዊነት ሰልፍ በተቃራኒ ለምን ይሰለፋሉ? ለምንስ ብሔራዊ ድርጅቶች የለውጡን መሪ የጨበጡ መስለው ታዩ? ብለን ስንጠይቅም ከዚህ በታች የምናያቸው ጥቂት ምክንያቶችን እናገኛለን፡፡
የብሔር ድርጅቶች መፈጠርምክንያቱ ምንድነው? 
ዛሬ በሀገራችን ነጻ አውጪ የሌለው ብሔር የሌለ እስከሚሆን ድረስ የብሔር ድርጅቶች ለብዛት እየተመሰረቱና እንዲያም ሲል  ራሳቸውን እያባዙ መሆኑን ሁሉም ኢትዮጵያዊ በአጽንኦት የተገነዘበው ነው፡፡ ታዲያ እነዚህ ድርጅቶች በተለያዩ አጋጣሚዎች መሪዎቻቸው በሚሰጧቸው መግለጫዎች፣ ከድርጅታቸው ሰነድ፣ ከሚዲያዎቻቸውና ከአባልና ደጋፊዎቻቸው ጽኁፎች በመነሳት የተመሰረቱበትንና እየታገሉ ያሉበትን አመክንዮ በጥቂቱ እንዳስሳለን፡፡ (የዚህ ጽሁፍ ጸሀፊ የብሔር ድርጅቶች መመስረት የለባቸውም የሚል አቋም የለውም ይህን ከታች እንመለከታዋለን)
ምክንያት1 ‹‹ታሪክ ገፍቶናል›› 
ከብዙ ብሔር ድርጅቶች  በሰፊውና ተደጋግሞ የሚጠቀሰው በታሪክ ውስጥ ተገፍተናል፣ ቋንቋችን፣ ባህላችን አልታከበረም ለዘመናት በተጻፉና በትምህርት ስርአቱ ውስጥ በገቡ የታሪክ ጽሁፎች ላይ የእኛ ሚና አልተካተተም የሚለው ግዙፍ አመክንዮ ነው በእርግጥም ኢትዮጵያን እስከ አሀን ድረስ እያስተዳደሯት ያሉ ግዢዎች በየትኛውም ህዝብ ላይ ጭቆና አላደረሱም ማለት አይቻልም አሁን የመለያያ ምክንያት እየሆነን ያለው ታሪካችንም ከወገንተኝነት በጸዳ መልኩ ተጽፏል ለማለትም አንደፍርም ነገር ግን ከላይ የተነሳው የትግል ምክንያት መፍትሔው ከሌለው ብሔር ተነጥሎና የራሱን ባህል፣ ቋንቋ፣ መብት ብቻ ማስከበር ወይስ ከሌሎች ጭቁን ማህበረሰቦች ጋር በጋራ  ሆኖ የሁሉም ቋንቋ ባህል ማንነት እንዲከበርና እንዲዳብር ማድረግ? የሚል ጥያቄ ብናነሳ መልሱ ለትግሉ ለውጥ አምጪነትም ሆነ ለብሔሩ  አባላት ጠቃሚ የሚሆነው ከሌሎች ጋር በሀገራዊነት ጥላ ውስጥ ለማንነትና ለመብት መታገል የሚለው ይሆናል፡፡
ምክንያት2 ወካይ የለንም 
ይህ ምክንያትም ሌሎች የብሔር ድርጅቶች በተመሰረቱበት ወቅት ኢትዮጵያዊ ነኝ ብሔራዊ ድርጅት አያስፈልገኝም የማንነት መብቴን በኢትዮጵያዊነት ጥላ ስር እንዲረጋገጥ እታገላለሁ በማለት የብሔር ድርጅት ያልመሰረቱ ብሔሮች አባላት አሁን የመሰረቱት ድርጅታቸው ተቀባይነት ያገኝ ዘንድ የሚሰጡት ምክንያት ነው፡፡ ዘርዘር ስናደርገውም እከሌ፣ እከሌ የሚባሉ ብሔሮች እከሌ የተባለ ድርጅት መስርተው እየታገሉ ነው እኛ ኢትዮጵያ ብቻ ብለን በምናደርገው ትግል ህዝባችን እየተጎዳ ነው የህዝቡ ትግል አብቦ ወደ ለውጥ ሲሄድ ኢትዮጵያ በምትመሰርተው የሽግግር ጉባኤም ሆነ የመንግስት ስርአት ውስጥ ብሔራችን ወካይ ድርጅት ሊኖረው ይገባል በማለት መከራከሪያቸውን ያቀርባሉ በመሰረቱ ማንኛውም ብሔር በራሱ ልጆች የመወከል መብት ያለው መሆኑን ማንም አሌ ሊለው አይችልም ይሁን እንጂ አሁን እየታገልነው ያለው አምባገነን አገዛዝ እንዳደረገው ሀገሪቷ ከእያንዳንዱ ብሔር በመዋጮ መልክ በሚመጡ ግለሰቦች በኋላም አንድ ፈርጣማ ክንድ /Iron hand/ ያለው ብሔር ጎልቶ ወጥቶ በሚዘውራቸው አሻንጉሊት የብሔር ድርጅቶች ስምምነት የሚፈጠር የሽግግር ጉባኤም ሆነ የመንግስት ስርአት ከለውጥ በኋላም ይኖራል ብሎ ማሰብ ከዚህ አልፎም ለዚያ መዋጮ መዘጋጀት እንታገልለታለን የሚሉትን የ‹‹ዲሞክራሲ ለሁሉም›› መርህ መጣስ ብሎም የአሁኑን ገዢ  ፓርቲ የዘረኝነት ፖሊሲ ለማስቀጠል እንደመሞከር የሚቆጠር ነው፡፡
ምክንያት3 እሾህን በሾህ 
የአንዳንድ የብሔር ድርጅቶች መሪዎችና አክቲቪስቶች ለድርጅቶቻቸው መመስረት ምክንያታቸውን ሲያስቀምጡ ህወሐት መራሹ ኢህአዴግ አሁን እያደረገ ላለው ቅጥ ያጣ ብሔሮችን የመጨቆን ድርጊት መፍትሔው በሱ መንገድ ተጎዞና የሱን ማሊያ ለብሶ መምጣት ነው ይላሉ ይህም ማለት ኦህዴድ፣ ብአዴን፣ ህወሓት፣ ደኢህዴን፣ አብዴፓ፣ ወ.ዘ.ተ. እስካሉ ድረስ የብሔር ድርጅቶችን ታርጋ ሳንለጥፍና ማልያውን ሳንለብስ ወደ ህዝቡ መድረስ አንችልም በሚል የ ሳይጀምሩ ተሸናፊነት መንፈስ መጓዝ ማለት ነው ይህም አመክንዮ ከፍ እያለ ሲሔድ ኢህአዴግ በአማራ፣ ኦሮሞ፣ ደቡብ፣ ወዘተ.. ብሔሮች ላይ ለፈጸመው ግፍ እኛም በሌላው ህዝብ ላይ የአጸፋ መልስ መስጠት አለብን ወደሚል የገደለ ያሸንፍ አይነት አገር አጥፊ ጫፍ ይገፋል፡፡
የውጭ ሀይሎች ሴራ 
ብሔርተኝነት በኢትዮጵያ እንዲጎለብት እርሱ ከአውሮፓ የመጣ ጃኬትና ሱሪውን ለብሶ ‹‹እከሌና እከሌ የሚባሉ ብሔሮች እከሌ የሚባለውን ብሔር ልብስ እንዲሰብሱ ተገደዋል ስለዚህም ኢትዮጵያ የብሔር ብሄረሰቦች እስር ቤት ናት” ብሎ ከደሰኮረው ዋለልኝ መኮንን ጀምሮ ሁሉም ባይባልም አብዛኞቹ የብሔር ፖለቲካ አቀንቃኞች በውጪ ሀይሎች እየተደገፉ ኢትዮጵያ የምትባል ሀገርን ለመበታተን ሰፊ ርቀት ሄደዋል፡፡ ዛሬ ብዙ ወንድሞቻችንን እየገበርን የምንታገለው ሕወሓት ኢህአዴግም የዚሁ የውጪ ሀይሎች እቅድ ውጤት ነው፡፡ ዛሬ በትግል ላይ ከሚገኙ ድርጅቶችም ምእራባውያኑ አይናቸውን እየጣሉባቸውና ለእቅዶቻቸው እያዘጋጇቸው ያሉ ድርጅቶች የሉም ማለት አይቻልም (በእርግጥ ከምእራባውያን ድጋፍ ማግኘትና ተመራጭ መሆን ብቻውን የሀገር አፍራሽነት መገለጫ ሊሆን አይችልም ከቀድሞው ጉዞ የበለጠ አሁን ያሉ ድርጅቶች ሀገር በቀልና ህዝባዊ አጀንዳ ያላቸው መሆናቸውም ሊሰመርበት ይገባል)እነዚህ ከላይ የጠቀስናቸውንና ያልጠቀስናቸውን ሌሎች አመክንዮዎችን በማቅረብ የብሔር ድርጅቶች በትግሉ ሜዳ ላይ ቀላል የማይባል አዎንታዊም ሆነ አሉታዊ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ይገኛሉ፡፡ ከላይ እንደገለጽኩት የብሔር ድርጅትን መመስረት በራሱ ነውርም ወንጀልም ሀገር አለመውደድም አይደለም ሌሎችን በመጥላት የማይነሳ፣ በሀገራዊ ጥላ ስር የተጠለለ፣ መነጣጠልን ሳይሆን አንድነትን የሚያበረታታ አላማው በህዝቦች ላይ የሚደርስ ጥቃትን ለማስቆምና በየትኛውም ብሄር ላይ እንዲህ አይነት ጥቃት እንዳይፈጸም ለማድረግ ያለመ እስከሆነ ድረስ በብሄር ስም መመስረቱ በራሱ ዘረኛ አያስብለውም በአንጻሩ በኢትዮጵያዊነት ስም የተመሰረቱ አንዳንድ ፓርቲ ተከታዮችም ከብሔር ድርጅቶች እሳቤ በጣም በባሰ መልኩ ዘረኝነት የሚንጸባረቅባቸው መሆኑንም መርሳት አይገባንም፡፡
ኢትዮጵያዊነት ተሸንፏል? 
ዛሬ ዛሬ አምባገነኑ ህውሓት/ኢህአዴግ ለከፋፍሎ መግዛት እቅድ ያመቸው ዘንድ በአኩይ እርሾው ያቦካው ብሔርተኝነት ገፍቷቸውም ይሁን በሌላም ምክንያት ኢትዮጵያዊ የሚባል ህብረ ብሔራዊ ድርጅት ስም አያsማን የሚሉ ልሒቃን እየተበራከቱ መጥተዋል በተለይም በቅርብ ጊዜ በሀገራችን እየተከናወኑ በሚገኙ የህዝባዊ እምቢተኝነት ንቅናቄዎች ውስጥ ክልል ተኮር የሆኑ ተቋማት ትግሉን ለማስተባበር መሞከራቸውና ትግሉንም ወደ መሬት ለማውረድ የተሻለው መንገድ ይህ በመሆኑ ኢትዮጵያዊነትን አታንሱብን አይነት አስተሳሰቦች በበርካታ ልሒቃን ዘንድ እንዲበራከቱ አስተዋጽኦ አድርጓል፡፡ ታዲያ ይህን ወቅታዊ እንቅስቃሴና ስሜት በመመልከት አንዳንዶች ኢትዮጵያዊነት ተሸንፏል ትግሉም ለውጥ ማምጣት የሚችለው ሁሉም በየብሔሩ ድርጅቶች ውስጥ በመግባት መታገል ሲችል ነው በማለት ይሞግታሉ፡፡ በእርግጥ ኢትዮጵያዊነት ተሸንፏል? የወቅቱ ትግልስ ህብረ ብሔራዊ አስተሳሰቦችንና ድርጅቶችን የሚሸከም ትከሻና የሚያጫውትበት ሜዳ የለውም? በማለት ቆም ብለን ስናስብ ነገሩ ‹‹እሳት ቢያንቀላፉ ገለባ ጎበኘው›› አይነት ሆኖ እናገኘዋለን፡፡
  ይህም ማለት የኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነት አቀንቃኝ ምሁራን ኢትዮጵያዊነት ተሰርቶ ያበቃ ነው ከህዝቡ ልቦና ማንም ሊያጠፋው አይችልም በሚል ምኞታዊ ሀሳብ በመዘናጋት ይህንኑ መንፈስ ከትግሉ የፍጥነት ሩጫ እኩል ባለማስኬዳቸው አልፎተርፎም ህብረ ብሔራዊ ትግሉ በሁሉም ክልሎችና ማህበረሰቦች ተደራሽ በመሆን ላይ ክፍተቶች የሚታዩባቸው በመሆኑ ከዚህም በተጨማሪ የኢትዮጵያዊነትን ሀሳብ የሚደግፈው ህዝብ አሁን እየተደረገ ባለው የብሔር ድርጅቶች እንቅስቃሴ ተደናግሮና ዳር ተመልካች ሆኖ በድብታ ውስጥ የሚገኝ በመሆኑ ኢትዮጵያዊነት የጠፋ/የተሸነፈ/ መስሎ ይታያል፡፡
  ይሁንና አሁን እየተደረገ ባለው ትግል ውስጥ እንኳን ኢትዮጵያዊነት እንዳልተሸነፈ የሚያሳዩ ብዙ ምልክቶችን መመልከት ችለናል፡፡ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒሰትር (ለሽንገላም ቢሆን)ስለ ኢትዮጵያዊነት በተናገራቸው አዎንታዊ ንግግሮች ከዳር እስከዳር ተቀባይነት እያገኘ የመጣ መምሰሉ፣ አድዋን የመሰሉ ታሪካዊና ብሔራዊ በአላትን መላው ህዝቡ በንቅናቄና ባልተለመደ ድምቀት ማክበሩ፣ ጽንፍ ለጽንፍ ሆነው በመተቻቸትና በመጠላላት ይታወቁ የነበሩ የብሄር ፖለቲካው ልሂቃን ስለ ኢትዮጵያ ሊባል መነጋገር መጀመራቸው ጥቂቶች ማሳያዎች  ናቸው፡፡ ታዲያ እነዚህንና ሌሎችንም ስንመለከት ለጊዜው የብሔራዊ ትግል አጀንዳ እያበበ የመጣ ይምሰል አንጂ የቱንም ያህል እድገት ቢኖረው  ለ3ሺ አመታት ሲሰበክ፣ ሲተገበርና ሲኖርበት የነበረውን ኢትዮጵያዊነት በዛ ቢባል ላለፉት 40 አመታት ብቻ በተሰበከው የብሔርተኝነት ፖለቲካ ሊጠፋና ሊሸነፍ እንደማይችል ማሳያ ነው፡፡
       ይሁንና ይህን ጭላንጭል ወደሚንቦገቦግ ነበልባል ለመቀየርና የለውጡን መንገድ ለማፋጠን ብሎም ቀጣይዋን የተስተካከለች ኢትዮጵያን ለመፍጠር በሚደረገው ጉዞ ውስጥ ሰፊ ትከሻ ያለው ቆራጥ ድርጅት፣ ምሁር፣ ልሒቅ ወዘተ. ያስፈልጋል እነዚህም አካላት በማህበረሰቡ ውስጥ ዘርፈ ብዙ የሆኑ ተግባራትን ሊያከናውኑ ይገባቸዋል፡፡ ድርጅቶች ዴሞክራሲያዊ መሆን ይገባቸዋል ዴሞክራሲው ደግሞ ሁሉንም ማህበረሰብ ያካተተ መሆን አለበት አንድ ሓገራዊ ድርጅት ሃገራዊነቱን የሚያስመሰክረው በአባላቱ፣ በስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው፣ በምክር ቤቱ ወዘተ. ያለገደብ ሁሉንም ማህበረሰብ ማካተት ሲችል ብሎም የድርጅቱ እንቅስቃሴ በሁሉም አካባቢዎች ተደራሽ መሆን ሲችል ነው፡፡  ዴሞክራሲያዊ ኢትዮጵያን አሻገሮ የሚመለከት ድርጅት በዚህ ብቻ አይወሰንም ይልቁኑ በኢትዮጵያዊነት ጥላ ስር ሆነው የተደራጁ የብሔር ድርጅቶችን በማገዝና በማጠናከር በጊዜ ሂደት ከብሔር ድርጅትነት ወደ ህብረ ብሔራዊነት እንዲመጡ ይህ ባይሆን እንኳን በምክንያታዊ አስተሳሰቦች ብቻ ትግላቸውን እንዲያራምዱ ያደርጋል፡፡ ከክፍተቶች ይልቅ በጎ ግንኙነቶችን ማዳበር ከድርጅት ፍቅር ይልቅ ሀገራዊ ጥቅምን ማስቀደም ከስሜታዊነት፣ ከግልብ ሀገር ወዳድነትና ከመተቻቸት ወጥቶ ኢትዮጵያን ከተጋረጠባት አደጋ ለማዳን ትግል ከሚያደርግ ድርጅት የሚጠበቅ የበሳልነት ተግባር ነው፡፡
         ምሁራን ግለሰቦችም ቢሆኑ ኢትዮጵያዊ  ብሔርተኝነት እንዲዳብር ከነሱ ሀሳብ በተቃራኒ የቆሙትን ከመፈረጅ ከመጥላትና ከመተቻቸት ይልቅ በርን ለውይይት ክፍት አድርጎ ለመወያየት መሞከር በቀደሙ ታሪኮች ላይ ሲነታረኩ ከመዋል ይልቅ አንድነትን በሚያጎለብቱ ጉዳዮች ላይ ጠንክሮ መስራት የተገባ ነው፡፡ እነዚህንና ሌሎችንም በቅንነት ማድረግ የሚችል ድርጅት ግንባር ንቅናቄ ወዘተ. እስካለ ድረስ ኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነትን አዳብሮና ህዝቡን በአንድ አስተሳስሮ ኢትዮጵያዊነትን እንዲዘምር ማድረግ ይቻላል የምንናፍቀውና በቅርብ ርቀት እያየ ነው የምንናፍቀውን ለውጥም በእጃችን መጨበጥ እንችላለን፡፡
       ይህን ጽሁፍ የምታነቡ  ሁሉ እመኑኝ ኢትዮጵያዊነት ይዳፈናል እንጂ አይጠፋም!!!
 ያንቀላፋል እንጂ ጨርሶ አይሞትም ለጊዜው ዝም ይላ ይሆናል እንጂ ጨርሶ እንደበቱ አይዘጋም የሚጠብቀንን ጥቂት ስራ ለመስራት ዝግጁ እንሁን አንጂ  በህዝቡ ልብ ውስጥ የተፃፈ ነው፡፡ኢትዮጵያዊነት ሀይሉን አድሶ ያንሰራራል ይህ ትንቢት ሳይሆን ጥሬ ሀቅ ነው እኛ ዛሬም ነገም ኢትዮጵያውያን ነን ኢትዮጵያዊነት ያሸንፋል!!!!!!
Filed in: Amharic