>

የወያኔ የንግድ ድርጅቶችና የብዙኃን መገናኛዎች ሕገወጥ ናቸው ሊዘጉ ሊወረሱ ይገባል ሲባል ምን ማለት ነው?(አምሳሉ ገብረኪዳን)

የወያኔ ሕገወጥ የንግድ ድርጅቶችና የብዙኃን መገናኛዎች ጉዳይ ወያኔ በዘመኑ ለአንድ ቀን እንኳ ቢሆን ለሕግ ተገዥ ሆኖ የማያውቅና አንባገነን መሆኑን ወይም ከሕግ በላይ መሆኑን ከሚያሳዩ ከሚያረጋግጡ ማስረጃዎች አንዱና ከዘር ማጥፋት ወንጀሉ፣ አሰብን ለሸአቢያ ሰፊ መሬትን ለሱዳን ሰጥቶ ከፈጸመው የሀገር ክህደቱ ቀጥሎ የሚገኝ ወንጀሉ ነው፡፡
ምክንያቱም ወያኔ ራሱ ባወጣው ሕግ “የፖለቲካ ፓርቲዎች የንግድ ድርጅቶችንና የኤሌክትሮኒክ (የነርሃል) የብዙኃን መገናኛ መክፈትና ማንቀሳቀስ አይችሉም!” ብሎ ከልክሏልና ነው፡፡ ወደኋላ ላይ ደግሞ መነገድ ብቻ ሳይሆን ከገቢያቸውም ከ10% በላይ እርዳታ መቀበል እንዳይችሉ ከልክሎ እርዳታ እንኳ አግኝተው እንዳይጠቀሙ፣ አቅማቸውን እንዳያደረጁና ለሀገር ሊያበረክቱ የሚችሉትን በጎ አስተዋጽኦ እንዳያበረክቱ፣ በብቸኝነት እንደፈለገ መፋነን እንዲችል እርዳታ መቀበል የሚከለክል ሕግ አውጥቶ ከልክሏል፡፡ በዚህም መሠረት ከራሱ በስተቀር ሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች (የእምነተ አሥተዳደር ቡድኖች) ብቸኛ የገቢ ምንጫቸው ምንም ነገር ለመከወን የማያስችለው የአባላት ወርሐዊ መዋጮ ብቻ እንዲሆን አድርጎ አቅማቸው የተዳከመ ወይም የሞተ ሆኖ እንዲሮር አድርጓል፡፡
ወያኔ/ኢሕአዴግ በእንዲህ ዓይነት ኢፍትሐዊ ሀገርንና ሕዝቧን ተጠቃሚ በማያደርጉና በሚጎዱ እሱን ራሱን ብቻ ተጠቃሚ በሚያደርጉ አሠራሮች ሥራውን የሚሠራ የጥፋት ቡድን በመሆኑ ነው መንግሥት ተብሎ ለመጠራት የማይበቃው፡፡ እንጥራው ካልን ወያኔን የወንበዴ (Mafia) ቡድን እንላለን እንጅ አንድም እንኳ የሀገር መንግሥትነት መገለጫ ኖሮት ሳያውቅ መንግሥት ልንለው ከቶውንም አንችልም፡፡ አንድ መንግሥት አንባገነን ሆኖም እንኳ መንግሥት ሊባል የሚችለው ከራሱ ጥቅም ይልቅ የሀገርንና የሕዝብን ጥቅም የሚያስቀድም ከሆነ ነው፡፡ ወያኔ ግን እንደምታውቁት እጅግ በሚያሳዝንና ሊታመን በማይችል ደረጃ ለራሱ ቡድናዊና ጠባብ የጎሳ ጥቅም ሲል ዕድሜ ዘመኑን የጨረሰው የሀገሪቱን ብሔራዊ ጥቅሞች አሳልፎ በመስጠትና በመቸርቸር ነው፡፡
ወያኔ በዚህም ነውረኛ ተፈጥሮው ወይም ባሕርይው የተነሣ እራሱ በከፍተኛ ደረጃ እያጧጧፈው ያለውን ነገር ሌሎቹን መከልከሉ “ምን ይሉኛል?” ሳይል ንግዱን በማጧጧፉ ዛሬ ላይ በሀብት አቅሙ በኢትዮጵያ ተወዳዳሪ የሌለው በአፍሪካም በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀስ የትእምት (EFFORT) እና በብአዴን በኦሕዴድና በደኢሕዴን የሚተዳደሩ አስመስሎ ያቋቋማቸው ሌሎች እኅት የንግድ ድርጅቶች ባለቤት ለመሆን በቅቷል፡፡
ለመሆኑ እነኝህን ድርጅቶች ሕገወጥ የሚያደርጓቸው ምን ምን ጉዳዮች ናቸው? ፦
1ኛ. አስቀድሜ እንደጠቆምኳቹህ ወያኔ እራሱ ባወጣውና ሀገሪቱ እየተገዛችበት ባለችው ሕግ መሠረት የፖለቲካ ፓርቲ (የእምነተ አሥተዳደር ቡድን) የንግድ ድርጅቶችን ማቋቋምና ማንቀሳቀስ በጥብቅ የተከለከለ ሆኖ እያለ ሕግን በመተላለፍ ተቋቁመው በሕገ ወጥና ኢፍትሐዊ በሆነ መንገድ ሲሠሩ ሲዘርፉ የቆዩና ያሉ ድርጅቶች በመሆናቸው፡፡
2ኛ. ትእምት (EFFORT) ወያኔ ሀገሪቱን ተቆጣጥሮ ሥልጣን ከመያዙ በፊት ከየቦታው ከዘረፈው የመንግሥት ባንኮች (ቤተንዋዮች) እና ድርጅቶች በተጨማሪ መንቀሳቀሻ ሀብቱ ወያኔ ሥልጣን በጨበጠ ማግሥት ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ካዝና አራቁቶ ብድር ይሁን ምን ሳይገለጽ በተወሰደና ሳይመለስ በቀረ 1.6 ቢሊዮን (ብልፍ) የሕዝብ ሀብት የተቋቋመ በመሆኑ፡፡
3ኛ. እነኝህ የወያኔ የንግድ ድርጅቶች ግብርና ቀረጥ ሳይከፍሉ የሚነግዱና የሚሠሩ በመሆናቸው፡፡
4ኛ. ከቀበሌ ጀምሮ እስከ ከፍተኛ የመንግሥት ተቋማት ያሉ የመንግሥት ንብረቶችንና ሠራተኞችን ያለምንም ክፍያና ሕገወጥ በሆነ መንገድ የሚጠቀሙ በመሆናቸው፡፡
5ኛ. እነኝህ የወያኔ የንግድ ድርጅቶች በዚህ መልኩ ሕገወጥ በሆነ መንገድ የሚሠሩ በመሆናቸው ፍትሐዊ የሆነ የንግድ ፉክክር በሀገሪቱ እንዳይኖር በማድረጋቸው የሀገር ውስጥ ባለሀብቶችን ከገበያ አስወጥተው የንግድ እንቅስቃሴውን በብቸኝነት በመቆጣጠራቸው ለኢፍትሐዊ የሀብት ክፍፍል ዋና መሣሪያ በመሆናቸው፣ የዜጎችን ሠርቶ የማደር መብት እንዳይኖር በማድረጋቸው፣ ሕገወጥና ኢፍትሐዊ እንቅስቃሴያቸው ከውጭ ወደ ሀገር ውስጥ የሚመጣ የመዋዕለ ንዋይ ፍሰትን (investment) እንዳይገባ እንቅፋት ሆኖ ለሀገር ዕድገት ከፍተኛ መሰናክል በመሆናቸው፡፡
በእነኝህ ምክንያቶች ነው አጠቃላይ የወያኔ የንግድ ድርጅቶችና እንደ ፋና፣ ድምፀ ወያኔ፣ ዋልታ፣ ኢ.ኤን.ኤን. ያሉ የብዙኃን መገናኛዎቹ ሕገወጥ የሚሆኑት ወዘጋትና በመንግሥት መወረስም የሚኖርባቸው፡፡
በእነዚህ ምክንያቶች ወያኔ ከየአቅጣጫው እነኝህ ድርጅቶች ሕገወጥነታቸው እየተጠቀሰ መጠየቁ፣ መወቀሱ፣ መተቸቱ ሲበዛበት ብልጥ ሆንኩ አለና ምን መላ ፈጠረ መሰላቹህ የንግድ ድርጅቶቹን “የትግራይ ሕዝብ ንብረት ናቸው የኔ አይደሉም ለትግራይ ሕዝብ በኢንዶውመንት (በስጦታ) ተላልፈዋል!” አለ፡፡ እራሱ እያንቀሳቀሳቸው፣ እየመራቸው፣ እያስተዳደራቸው ዕየታየ እኮነው ዓይኑን በጨው አጥቦ ሸምጥጦ ለመካድ የሚሞክረው!
እነ ፋናን በተመለከተ ደግሞ ከወያኔ ንብረትነት አውጥቶ በጥቂት አመራሮቹ ስም የአክሲዮን (የጋራ) ድርጅት አድርጎ አስመዘገበውና “የግለሰቦች የጋራ ንብረት ነው!” በማለት ከአፋጣጩ ጥያቄ ለማምለጥ ሞከረ፡፡ ጣቢያው እኮ በግልጽ በይፋ የወያኔ ፖለቲካ (እምነተ አሥተዳደር) የፕሮፓጋንዳ (የልፈፋ) መሣሪያ መሆኑ በግልጽ እየተደመጠና እየታየ የራሱ ሰዎች እያስተዳደሩት እኮነው የእኛ አይደለም “የኔ አይደለም የግለሰቦች የጋራ ንብረት ነው!” የሚለን! ዓይነደረቅነቱ አይገርማቹህም???
ነገር ግን እውነቱን ማንም ስለሚያውቀው ወያኔ በዚህ የቂል የማምለጫ ምክንያቱ ማንንም መሸወድ አይችልም፡፡ ድርጅቶቹ ንብረትነታቸው “የትግሬ ሕዝብ ነው፣ የግለሰቦች ነው!” የሚለው ምክንያቱ የማይሠራበት ሌላው ምክንያት የሕዝብ ገንዘብ እየዘረፈ የእነኝህን ድርጅቶች ሀብት ያካበተው ወያኔ እንጅ የትግሬ ሕዝብ ስላልሆነ ነው፡፡
ለነገሩ በወያኔ ስሌት ወያኔና የትግሬ ሕዝብ የማይነጣጠሉ የአንድ ሳንቲም ገጽታዎች ናቸውና ለውጥ የለውም፡፡ ንብረቱ ለትግሬ ሕዝብ ተሰጥቷል ቢባልም እንኳ ይህ ንብረት ከኢትዮጵያ ሕዝብ የተዘረፈ ንብረት በመሆኑ ተመልሶ የኢትዮጵያ ሕዝብ ንብረት መሆን ይኖርበታል፡፡ ይሕ እንዲሆን ሕግ ያስገድዳል፡፡ ሕግ ወንጀለኛ የሚያደርገው ሌባን ብቻ አይደለም የሌባን ተቀባይ ጭምር እንጅ፡፡ በመሆኑም የትግሬ ሕዝብ ቢያስብበት መልካም ነው፡፡ መቸ እንደሚያፍሩበትና እንደሚሰማቸው አናውቅም እንጅ የኢትዮጵያን ሕዝብ ገንዘብና ንብረት ዘርፈው ሲያበቁ “ገንዘቡ ንብረቱ የትግራይ ሕዝብ ነው!” ማለት አሳፋሪና ነውረኛ የውንብድና ተግባር ነው፡፡
እነሱ ግን በዚህ አሳፋሪ ተግባራቸው ሲኮሩበትና ለሌላ ዝርፊያ ሲዘጋጁ እንጅ ሲያፍሩበት አይታዩም፡፡ ሰብእናቸው የውንብድና ሰብእና ነውና፣ የስርቆት የውንብድና ነውርነት ጭንቅላታቸው ውስጥ የለምና፣ በስርቆት በውንብድና በዝርፊያ ማፈር መሸማቀቅ የሚባል ነገር ሥነልቡናቸው ውስጥ የለምና ወደፊትም የሚያፍሩበት የሚሸማቀቁበት አይመስልም፡፡
ሲጀመር የፖለቲካ ፓርቲ ባለቤቱ ንብረትነቱ ሕዝብ ነው፡፡ ስለዚህ አንድ የፖለቲካ ፓርቲ ንብረት ቢኖረው ንብረቱ ሊያገለግለው የሚፈልገው ሕዝብ ንብረት ነው እንጅ ፓርቲው ውስጥ ያሉት የጥቂት ግለሰቦች የግል ንብረት አይደለም፡፡ ከመጀመሪያው ጀምሮም የዚያ ንብረት ምንጩ ሕዝብ ነውና፡፡ የፖለቲካ ፓርቲ ባለቤቱ ሕዝብ የማይሆነው ያ የፖለቲካ ፓርቲ የሚያራምደው አቋም፣ ዓላማና ግብ ሕዝብን ያማከለ ያልሆነ እንደሆነና የፓርቲው አንቀሳቃሽ ግለሰቦች ዓላማ፣ አቋምና ግብ ብቻ የሆነ ከሆነና የሚታገሉትም ለራሳቸው ብቻ ከሆነ ነው፡፡
ከዚህ ውጭ ግን የፓርቲ ንብረት እራሱን ፓርቲውን ጨምሮ የሕዝብ በሆነበት ሁኔታ አንድ ፓርቲ ንብረቱን “የሕዝብ ነው እንጅ የኔ አይደለም!” ሊል አይችልም፡፡ እሱም እራሱም የሕዝብ ሆኖ እያለ “የኔ አይደለም!” ካለ እራሱን ከሕዝብ ንብረትነት፣ ሀብትነት መለየት ይሆንበታል ማለት ነው፡፡ ወይም ደግሞ የሕዝብ አይደለሁም ማለት ይሆንበታል ማለት ነው፡፡ ወያኔ ድርጅቶቹን “የኔ አይደሉም የትግራይ ሕዝብ ናቸው!” ብሎ ሲል “እኔ የሕዝብ አይደለሁም!” ማለቱ እንደሆነ አልገባውም፡፡
ስለሆነም የወያኔ “የትግራይ ሕዝብ ነው እንጅ የኔ አይደለም!” የሚለው ምክንያት ውኃ የሚቋጥር ወይም አመክንዮአዊ ምክንያት አይደለም ማለት ነው፡፡ ለነገሩ ለወያኔ ይሄ ውኃ የማይቋጥር ምክንያቱ መከላከያ ማምለጫ የሚሆነው “አባቱ ዳኛ ልጁ ቀማኛ!” በሆነበት በራሱ ዘመንና መድረክ ብቻ እንጅ ፍትሕ በሰፈነበት ዘመንና መድረክ ላይ ወይም ሥልጣኑን ባጣበት ወቅት ላይ አይሆንምና የሚያሳስብ አይደለም፡፡
ነገር ግን ወያኔ/ኢሕአዴግ ወይም አዲሱ የጠ/ሚ ዐቢይ አሥተዳደር ተጠያቂነትን አሰፍናለሁ፣ ዕኩል የኢኮኖሚ (የምጣኔ ሀብት) ተጠቃሚነትን አረጋግጣለሁ፣ የሕግ የበላይነትን አሰፍናለሁ፣ ሙስናንና የአሥተዳደር ብልሹነትን አከስማለሁ….. ማለቱ እውነት ከሆነ የኢትዮጵያ ሕዝብ እነኝህን በእብሪትና በማንአለብኝነት ከሕግ ውጭ ተመሥርተው ሕገወጥ በሆነ መንገድ ሲንቀሳቀሱና ሀብት ሲያከማቹ የኖሩ ሕገወጥ የንግድ ድርጅቶችና የብዙኃን መገናኛዎች  ተዘግተው ሀብት ንብረታቸው ገቢ ለመንግሥት እንዲደረግ መጠየቅና ማስፈጸም ይኖርበታል፡፡
እንደምናየው ግን ይሄ እየሆነ አይደለም፡፡ ዐቢይ ባለሀብቶችን ሸራተን ሆቴል (ቤተ እንግዳ) ላይ በሰበሰበ ጊዜ ይሄ ጥያቄ በባለሀብቶች መነሣት ሲገባው ሳይነሣ ቀርቷል፡፡ አገዛዙ ይሄንን የሕዝብ ጥያቄ የሚፈጽም ካልሆነ ግን እየተወሸከተ ያለው ነገር ሁሉ ሕዝብ ማታለያ ማዘናጊያና ማወናበጃ ባዶ ልፈፋ መሆኑን አውቀህ በጊዜ ንቃና ሕዝባዊ ዐመፅህን ግፋ!!!
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!! ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!
ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው 
Filed in: Amharic