>

አዲሱን ጠ/ሚ አለመደገፍ የለውጥ ጭላንጭሉን ማዳፈን ነው (ዘ አብ ለይኩን)

መቼም የተግባር ሁሉ ጅማሮ ሐሳብ ነውና ከዚህ አንፃር ዶ/ር አብይን ለማድነቅ ብዙ ምክንያቶች አሉ ብዬ አምናለሁ፡፡ ”ምን ተይዞ አድናቆት” የሚል ሰውም በወያኔ የኋላ ታሪክና የሴራ ፖለቲካ መነሻነት ዶ/ሩን በጥርጣሬ ቢያየው ወይም በጉዳዩ ላይ ዝምታን ቢመርጥ አልተሳሳተም፡፡ ነገር ግን መቃወም ሱስ የሚሆን ካልሆነ በስተቀር ዶ/ሩን ለመቃወም አሁን ጊዜው በጣም በጣም ገና ይመስለኛል፡፡ ጎበዝ! እያወራሁ ያለሁት ግን ስለ ኢህአዴግ አይደለም፤ በብዙ ጉዳዮች ከራሱ ፓርቲ መርህና አሰራር በተቃራኒው እየተንቀሳቀሰ ስላለው ዶ/ር አብይ እንጂ፡፡
እንዲያውም ጠሚው ከወያኔ ጫና ተላቆ እንዲሰራና ለሕዝቡ እየገባ ያለውን ቃል ወደ ተግባር ተቀይሮ ለማየት የምንሻ ከሆነ ድጋፋችንን የበለጠ ልንቸረው የሚገባ ይመስለኛል፡፡ያለ ወያኔ መልካም ፍቃድ በሕዝብ ግፊት ብቻ ስልጣን ፈልቅቆ መውሰድ ለቻለ አካል የህዝብ ድጋፉ ተጠናክሮ ቢቀጥልለት የወያኔን የ27 ዓመታት የአፈና አገዛዝ ታሪክ ለማድረግ የሚከብደው አይሆንም፡፡ ዶ/ሩም ከክልል ክልል እየተዘዋወረ ያለው ለቀጣይ ዕቅዶቹ ተፈፃሚነት የሚያስፈልገውን ድጋፍ ቀድሞ ለማረጋገጥ ይመስለኛል፡፡
በኔ እምነት ዛሬ ከኦህዴድ ከተነሳው የለውጥ ነፋስ የተሻለ ተስፋ ወደየትኛውም አቅጣጫ ብናማትር ያለ አይመስለኝም፡፡  እናም ዛሬም እንደ ትናንቱ በተቃውሟችሁ የምትገፉ ሰዎች ከመቃወማችሁ በፊት ተቃውሟችሁ ጠሚውን በመደገፍ ከሚገኘው ጥቅም የበለጠ ትርፍ እንደሚኖረው ሁለቴ ብታስቡበት መልካም ነው፡፡ ምናልባትም የዘመኑ ፖለቲካ የጠላትን ጠላት በወዳጅነት የሚያ ሆኖ እያለ እናንተ ግን በዶ/ሩ መመረጥ ቆሽታቸው ካረረው  ወያኔና ጭፍራዎቹ ጋር ተመሳሳይ አቋም እያራመዳችሁ መሆኑንም አብሮ ማሰብ ያስፈልጋል፡፡
እርግጥ ነው የመጨረሻው ግብ ኢህአዴግን አሽቀንጥሮ መጣል መሆን አለበት፡፡ ዶ/ር አብይንም እናበረታታው ስል ቢያንስ  የተጫነብንን ቀንበር በማንሳት የመጫወቻ ሜዳውን ሊያደላድልልን ይችላል በሚል ተስፋ ነው እንጂ ቋሚ ደጋፊው ሆኜ አይደለም፡፡ ትንሽ ጊዜ ሰጥተን አይተነው ተስፋችን ሁሉ እንዳይሆን ከሆነም ከፀፀት ጋር “ዱሮ ብለን ነበር” የሚሉትን ጎራ መቀላቀል ማን ይከለክለናል?
Filed in: Amharic