>

አገራዊ መግባባት ካልን ኦብነግን፣ኦነግን እና ግምቦት 7ን ከአሸባሪነት መሠረዝ፤ (ውብሸት ሙላት)

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከአልቃኢዳና አልሸባብ በተጨማሪ ኦብነግን፣ኦነግን እና ግንቦት 7 በሽብርተኛ (አሸባሪ) ድርጅትነት የሠየማቸው መሆኑ ይታወቃል፡፡ በአሸባሪነት ከተሠየሙ በኋላ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የሽብር ድርጊት ፈጽመዋል፣ወይም ሊፈጽሙ ነበር፣ወይም ዕርዳታና እገዛ አድርገዋል ወዘተ በሚል በሽብር ወንጀል  ተከሰው የተፈረደባቸው አሉ፡፡ በክስ ላይ ያሉም አሉ፡፡ በምርመራም ላይ እንዲሁ፡፡
የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ያሳለፈውን ውሳኔ ተከትሎ አንዳንድ  በሽብር ወንጀል የተከሰሱት ሰዎችን ክሳቸው እየተቋረጠላቸው ነው፡፡ የተፈረደባቸውም በይቅርታ እየተፈቱ ነው፡፡ በተለይ ከኦነግና ግንቦት 7 ጋር በተገናኘ የተከሰሱትም ይሁኑ የተፈረደባቸው ሰዎችም እየተፈቱ ነው፡፡ ይሁን እንጂ በተሻለ ሁኔታ አገራዊ መግባባት ለመፍጠር እነዚህን ሦስት ድርጂቶች በሚከተሉት ስድስት ምክንያቶች ከሽብርተኛ ድርጂትነት ቢሰረዙ ጥሩ ነው፡፡
ለምን ሦስቱ ብቻ?
በመንግሥት ላይ ነፍጥ የመዘዙ እና አማጺ የሆኑ በርካታ ድርቶች ቢኖሩም በአሸባሪነት የተፈረጁት ሦስቱ ብቻ ናቸው፡፡ ነፍጥ ማንሳት ብቻ ሳይሆን አድራጎታቸውም ቢሆን ተመሳሳይ ነው፡፡ ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የሚሆኑት መሠረታቸውና ስያሜያቸው  ከጋምቤላ፣ከቤኒሻንጉል፣ከትግራይ፣ እና ከአፋር ሕዝቦች ጋር የሚያያዝ አማጺ ድርጂቶች ናቸው፡፡ ሁሉም በዋናነት ድጋፍ የሚደረግላቸው በኤርትራ መንግሥት ነው፡፡
የሚፈጽሟቸውም ድርጊቶች ተመሳሳይ ናቸው፡፡ በተለይ የጋምቤላ እና የቤኒሻንጉል ድርጂቶቹ ጋር በተገናኘ በርከት ያሉ ሰዎችም በሽብር የተከሰሱ እንዳሉ ይታወቃል፡፡ ድርጂቶቹ ግን አሸባሪ ተብለው አልተፈረጁም፡፡ በቅርቡ እንኳን መርሳ ወልዲያ እና ቆቦ ላይ ተፈጥሮ የነበረውን ድርጊት ተከትሎ ከግምቦት ሰባት ጋር በመሆን መግለጫ ያወጣው  ትሕዴንም ቢሆን አሸባሪ ተብሎ አልተፈረጀም፡፡
 በመሆኑም፣ተመሳሳይ ድርጊት የሚፈጽሙ፣በተመሳሳይ አገር ድጋፍ የሚደረግላቸው የትጥቅ ትግልን የመረጡ ድርጂቶች ቢኖሩም ሦስቱ ብቻ አሸባሪ መባላቸው የአገር አንድነትና ስሜት ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እና በብሔሮች መካከል ጥርጥር የሚፈጥር መሆኑን ከግምት ማስገባት ይጠቅማል፡፡ አድሏዊም ነው፡፡
የኦብነግ፣ኦነግና ግምቦት ሰባት አባላት እነማን ናቸው?
በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ የኦሮሞ፣የአማራና የሶማሌ ተወላጆች ከኦብነግ፣ከኦነግና ለግምቦት ሰባት ሰዎች ጋር ግንኙነት ፈጥሯችኋል፣የአሸባሪ ድርጂቶችን ተልእኮ አስፈጽማችኋል ወዘተ በሚል ተከሰው ጥፋተኛ ተብለዋል፡፡ በምርመራም ላይ በርካታ ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ ይሁን እንጂ በሕግ ወይም በሌላ መንገድ ተለይተው እስካልታወቁ ድረስ ከአንዳንድ በጣት ከሚቆጠሩ በስተቀር የኦብነግ፣የኦነግ እና የግምቦት ሰባት አባላት እነማን እንደሆኑ ሁሉ አይታወቅም፡፡ እንቶኔ፣እንቶኔ ተብለው ተለይተው ካልታወቁ እንማን የእነዚህ ድርጂቶች አባላት ይሁኑ አይሁኑ አይታወቅም፡፡
 በመሆኑም፣ከሳሾች እንዳሻቸው የፈለጉትን ሰው ከፈለጉት ውጭ አገር ከሚኖር አማራ፣ጉራጌ፣ኦሮሞ ወይም ሶማሌ ጋር ተገናኝተሃል፣በማኅበራዊ ሚዲያ የጻፋቸውን like or share አድርገሃል ወዘተ በሚል ለመክሰስ የተመቻቸ ብሎም የዜጎችን ሕይወት ፍርሃትና ሰቀቀን ውሥጥ የሚከት ነው፡፡
ተራ ዜጎችን ብቻ ሳይሆን የአማራ፣የኦሮሞና የሶማሌ አመራሮችንም ጭምር ስጋትና ፍርሃት ውስጥ እንደሚገቡ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ስለዚህ በግልጽ እንቶኔ እንቶኔ ተብለው ተለይተው የሚታወቁ አባላት በሌሉበት ሁኔታ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን በሽብር መክሰስ ፍትሐዊ አይሆንም፡፡
ሌሎች የወንጀል ሕግች መኖራቸው፤
በወንጀል ሕጉ ውስጥ ከተቀመጡት ወንጀሎች መካከል ብዙዎቹ የሽብር ድርጊት በሚከሰትበት ጊዜም ለመክሰስ ይጠቅማሉ፡፡ በዚያ ላይ አሸባሪ ብሎ ሳይሰይሙም ሰዎችን በሽብር ድርጊት መክሰስ ይቻላል፡፡ መሰየሙ ግንኙነት ፈጥራችኋላ፣ከእንቶኔ ጋር ተገናኝታችኋል ወዘተ በማለት ሌሎች ዜጎችን ለመክሰስ ካልሆነ በስተቀር ብዙም ፋይዳ የለውም፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ የሚኖሩ ዜጎች ለሚያደርጓቸው የወንጀል ድርጊቶች በቂ ሕጎች ስላሉ ብሎም ሥነ ልቦናዊ ፍርሃት ከመፍጠር ባለፈ የሚጠቅመው ነገር ስለሌለ በሽብር የተፈረጁት ድርጅቶች ከሽብር መዝገብ ቢሠረዙ ለአገራዊ መግባባት ጠቀሜታው የጎላ ነው፡፡
ትጥቅ ትግልና አሸባሪ መሆን የተለያዩ መሆናቸው፤
አንዳንድ ቡድኖች ከሰላማዊ ትግል ይልቅ የትጥቅ ትግልን የመረጡ ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ይህ ዓይነቱ ድረጊት ድሮም ነበር፡፡ አሁንም አለ፡፡ ምናልባት ወደፊትም ሊኖር ይችላል፡፡ የዴሞክራሲ ሜዳው ሲጠብ ሌላ አማራጭ የሚከተል ቡድን ሊኖር ይችላል፡፡ እንዲህ ዓይነቱ የትግል አማራጭ ውስጥ ዜጎች እንዳይገቡ መፍትሔው ዴሞክራሲን ማስፈን ነው፡፡ ኢሕአዴግም ሥልጣን የያዘው በዚሁ መንገድ ነው፡፡ ነገር ግን አሸባሪ አልተባለም፤አልነበረምም፡፡ Belligerent or insurgent is totally different from a terrorist group! የትጥቅ ትግል የመረጠ ሁሉ አሸባሪ አይደለም፡፡
በጸረ-ሽብር ሕጉ ግን እነዚህንም ያካትታል፡፡ የትጥቅ ትግል ሕጋዊ ነው ማለት ሳይሆን አሸባሪነት ግን ላይሆን ይችላል፡፡ ስለዚህ የትጥቅ ትግል የመረጡ ቡድኖችን በሙሉ አሸባሪ ማለት አሳማኝ አይደለም፡፡
በሁለት ሚዛን መመዘኑ፤
ከወራት በፊት ከእስር የተለቀቁት ዶ/ር መረራ ጉድና አውሮፓ በሔዱበት ወቅት ከግንቦት ሰባት መሪ ከሆኑት ከፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ጋር ተገናኝተዋል በሚል ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሶማሌ ርዕሰ መስተዳድር እና ሌሎች ግለሰቦች በቅርቡ ከኦብነግ አመራር ጋር በኬንያ ድርድር ላይ መሳተፋቸው በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ተዘግቧል፡፡ የኢፌዲሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አሸባሪ ብሎ ከሰየመው አካል ጋር ድርድር አድርገዋል፣ተገናኝተዋል፡፡
እንግዲህ ዶ/ር መረራም ቢሆኑ በአንድ ወይም በሁለት መድረኮች ላይ ከፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ ጋር ከመገናኘት ባለፈ ኢትዮጵያ ውስጥ መጥተው የሽብር ድርጊት አልፈጸሙም፤መዘጋጀታቸውም ይሁን መሞከራቸው ለክሳቸው መነሻ አልሆነም፡፡ አቶ አብዲ ኢሌ ያደረጉት በባሕርይ ሰላም ለማምጣት ነው፡፡ ዶ/ር መረራም ቢያንስ የሽብር ድርጊት ለመፈጸም አይደለም፡፡ በመገናኘት ብቻ ከሆነ አብዲ ኢሌና አብረው የተሳተፉትም መከሰስ ነበረባቸው፡፡ የተገናኙበት ዓላማ ግምት ሳይገባ ዶ/ር መረራ ተከሰዋልና! በአጭሩ ከጣት ጣት የሚለይም ተግባር እየተፈጸመበት ስለሆነ ከአሸባነት ቢሰረዙ ለአገር ይጠቅማል፡፡ ተመሳሳይ ተግባራትን በሁለት ሚዛን መለካት ኢፍትሐዊ ነው፡፡
ከጣት ጣት ስለለዬ፤
የኢሕአዴግ ሥራ አስፈጻሚ ውሳኔን ተከትሎ በርካታ በሽብር ወንጀል የተከሠሱ ሰዎች ክሳቸው ተቋርጦ አሊያም በይቀርታ ከእስር ተለቀዋል፡፡ የተለቀቁት እንዳለ ሆኖ በሽብር ተከሰው ክሳቸው ያልተቋረጠላቸው ወይም በይቅርታ ያልተለቀቁ አሉ፡፡ የተወሰኑትን በመልቀቅ ሌሎቹን መተው እጅግ ሲበዛ አድሏዊነት ነው፡፡ ዘፈቀዴያዊነትም ጭምር፡፡ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ክስ ለማቋረጥም ይሁን በይቅርታ ለመፍታት ግልጽና አድሏዊ የሆነ መለኪያ ተጠቅሟል ማለት እጅግ አዳጋች ነው፡፡
ስለሆነም የተሻለ አገራዊ መግባባት ለመፍጠር  ግለሰብን መሠረት ያደረገ የክስ ማቋረጥና የይቅርታ ተግባር ውስጥ ከመግባት ምህረት በማድረግ በሽብር የተፈረጁትንም መሰረዝ ይሻላል፡፡ አልበለዚያ ያው አንዱን በመፍታት ሌላውን መተው ከጣት ጣት መለየት ነው፡፡
Filed in: Amharic