>

ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ተያይዞ የሚደረጉ ፍረጃዎችን ስለመቃወም እና የሀሳብን መሠረት ስለመግለጽ (አቤል ዋቤላ)

አንዳንድ ፍረጃዎች እና የተጣመሙ አስተሳሰቦችን ለማጥራት ትንሽ ማለት ያስፈልጋል፡፡ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ ወደ ስልጣን ከመጡ አንድ ወር ቢቆጠርም የእርሳቸው እና ቲም ለማ ተረክ ወደኋላ የሚጓዝ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ሰዎች ስለ ወቅታዊው ሁኔታ የሚያንጸባርቁት አቋም ይህንን ሂደት ከቅርብ ርቀት ከመከታተል የመጣ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ አራት ኪሎ የገቡት አገር በሚያውቀው ሁኔታ ብዙዎቹ የግንባሩ ሽማግሌዎች በተለይ ህወሓታውያን ሳይፈልጉ ነው፡፡

ይህ ሂደት በመንግስት ደጋፊዎች መካከል ልዩነት መፍጠሩ የሚጠበቅ ነው፡፡ ምክንያቱም ካድሬው የግንባሩ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ እና ምክር ቤት ነጸብራቅ በመሆኑ በውስጥ የታየው መሰንጠቅ በውጭ ያለውን መክፈሉ የማይቀር ነው፡፡ ይህንን ስርዓት በሚቃወሙ ሰዎች መካከል መለያየት መፈጠሩ ግን ግራ የሚያጋባ፣ ነገሮችን በደንብ ካለመረዳት የሚመነጭ እና የሀገራችን የአደባባይ ተዋስኦ ደረጃ ዝቅተኛነት የሚያሳይ ነው፡፡

ተቃዋሚው ወገን የተወሰኑ ሰዎች እንደ ፓርቲ ኦህዴድ እና ብአዴን እና በፓርቲዎቹ መካከል ስላለው ትብብር ተስፋ ሲያሳድሩ ሌሎቹ ደግሞ አቶ ገዱን ያቀፈ የአቶ ለማ ቡድን ላይ ማተኮር ይፈልጋሉ፡፡ እኔ እንደሚገባኝ አፈቃሪ ዴሞክራሲ የሆነው የኀብረተሰብ ክፍል ለእነዚህ ኀይሎች ድጋፉን የሚሰጠው በነጻ ምርጫ እንደወከላቸው ወይም እንደ ነጻነት ሐዋርያት ቆጥሮ አይደለም፡፡ ነገር ግን ፓርቲያቸው ለ27 ዓመታት ሀገሪቱን የወሰዳትን የቁልቁለት ጉዞ በመረዳት ስህተቱን ለማረም እና ሀገሪቱን ወደ ዴሞክራሲ ለማሻገር ይረዳሉ ብሎ በማሰብ ነው፡፡ ለዚህ ተስፋ መነሻው ተራ የሽንገላ ወሬ ሳይሆን ሰዎቹ ከግንባሩ ባህል አፈንገጠው የሄዱበት መንገድ ነው፡፡ አብዮታዊ ዴሞክራሲ ተጥሷል፡፡ የዴሞክራሲያዊ ማዕክላዊነት ተነቃንቋል፡፡ ዘውጋዊ አስተሳሰብ እና መዋቅር ፈተና ውስጥ ገብቷል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከመጀመሪያው የበዐለ ሲመት ንግግራቸው ጀምሮ ኢህአዴግ በመቃብሬ ላይ የሚላቸው ነገሮችን ጥሰዋል፡፡ ለተሰሩ ስህተቶች ይቅርታ ጠይቀዋል፡፡ እንደ ፍትህ ያሉ ተቋማት በነጻነት የስራቸውን የሚከውኑበት፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎች በነጻነት የሚነቀሳቀሱበት ከባቢ ለመፍጠር ቃል ገብተዋል፡፡

ይህ ሁሉ ሲደመር በመርህ ላይ ተመስርተው በሀገራችን ነጻነት፣ እኩልነት እና ዴሞክራሲያዊነት እንዲሰፍን የሚፈልጉትን ልብ መግዛቱ የሚጠበቅ ነው፡፡ አንድ ለወገኑ፣ ለሀገሩ በጎ የሚመኝ ዜጋ በዚህ ተስፋ ማሳደር እና ጥርጣሬን ያልተየው ድጋፍ ከመስጠት በቀር ምርጫ ቢያጣ ሊፈረድበት አይገባም፡፡

ጥርጣሬው የሚነጨው አንደኛው ምክንያት ሰውየው ወይም ቲም ለማ በተግባር ያልፈጸሙት ነገር በመኖሩ ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የወያኔ አሸከር ላለመሆናቸው ማረጋገጫ የሚሆን ተጨማሪ ነገር መጠበቁ ተገቢ ነው፡፡ የወያኔ አሽከር ባይሆኑ እንኳን በራሳቸው ሀገሪቱን ባለችበት እንድትረግጥ የሚያደርግ ወይም የበለጠ የሚያደቃትን ነገር ለማድረግ የሚያስችላቸው ዕድል ሰፊ ነው፡፡ “እስካሁን ያየሁት፣ የሰማኹት በቂ አይደልም፡፡ የሀገሪቱን ከሄደችበት ቁልቁለት የሚመልስ ተግባር እፈልጋለኹ፡፡” ብሎ መሟገት ከአንድ ባለአእምሮ የሚጠበቅ ነው፡፡

ሁለተኛው የጥርጣሬው መነሻ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የሚመራው ‘ሲቪል’ መንግስት የፖለቲካ ስልጣን ማዕከል አለመሆኑን ግምት ውስጥ ያስገባ ነው፡፡ ወያኔ አሁንም የሀገሪቱን ደህንነት መስሪያ ቤት እና መከላከያ በጁ ይዞ እንዳደፈጠ የሚታወቅ ነው፡፡ በከፍተኛ ወንጀል የሚጠረጠሩ ባለስልጣናት አሁንም አንደ ነጻ ሰው እየተንቀሳቀሱ ናቸው፡፡ መሰረታዊ ተቋማት አሉ ለማለት ያስቸግራል፡፡ አሁንም የሀገሪቱ ኢኮኖሚ ስርዓቱ በፈጠራቸው የፓርቲ የኢኮኖሚ ኢምፓየሮች የተያዘ ነው፡፡ ብዙዎች አሁንም በእስር ቤት ናቸው፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አሁንም በስራ ላይ ነው፡፡ ኮማንድ ፖሰቱ የራሱ እስረኞች አሉት፤ የዜጎችን ህገ መንግስታዊ መብቶች ገርስሶ የፈለገውን ማድረግ ይችላል፡፡

ይህ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደለውጥ ሐዋርያ እንዳይቆጠሩ ስልጣናቸውም ውስን እንደሆነ በማተት ሙሉ ቅቡልነት እንዳያገኙ አድርጓቸዋል፡፡ የመሰረቱት ካቢኔም ብዙም ተራማጅ ያለመሆን ለብዙዎች የሰውየው ስልጣን ውስኑነት ማሳያ እና ማርሽ ቀያሪ አለመሆን ምልክት ሆኗል፡፡

ከዚህ በላይ ያሰፈርኩትን ሙግት አዲስ ነገር የለውም፡፡ በሁለቱም ወገን የሚነሱ ክርክሮች ሲሆኑ አሁን ያለውን የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ትኩሳት የሚያሳዩ ናቸው፡፡ እንግዲህ እንዚህን ሁኔታዎች ከግምት ውስጥ ያስገባ ንቁ ዜጋ (informed citizen) ግራ እና ቀኙን መዝኖ የራሱን ድምዳሜ ላይ ይደርሳል፡፡ ከዚህ ውጪ ለመፈራረጅ እና ለመወራረፍ የሚያበቃ ነገር ያለ አይመስለኝም፡፡

አሁንም ለውጥ እንደመጣ/እንደሚመጣ የሚያሳዩ በቂ ነገሮች የሉም ስለዚህ ብዙ ተስፋ የለንም የሚሉ ብዙ ሰዎች አሉ፡፡ ይህ በነጻ ህሊና የተደረሰበት መደምደሚያ ስለሆነ ሊከበር ይገባዋል፡፡ ያላስተዋላቸው ለውጦችን ከማብራራት እና ጠቅላዩ ተጨማሪ አሳማኝ እርምጃዎች እስኪወስዱ ከመጠበቅ በቀር ይህንን ባለአእምሮ እንደ አጉል ተጠራጣሪ እና ጨለምተኛ የሚታይበት ምንም ምክንያት የለም፡፡

በሌላ በኩል ጠቅላዩ በመሠረታዊ ሀሳባቸው ከኢህአዴግ ያፈነገጡ መናፍቅ ናቸው፡፡ እስካሁን ያሳዩት ግስቸር ሂሳዊ ድጋፍ እንድሰጣቸው በቂ ምክንያት ነው፡፡ በሀገር ቤትም በውጭም ያለ አፍቃሪ ዴሞክራሲ፣ ዲፕሎማቲክ ኮሚኒቲ እና በሌሎች ማኀበረሰባዊ እንቅስቃሴዎች ከታገዙ ሀገሪቱ የራሷን ቁስል እንድታክም እና ወደፊት እንድትጓዝ አስተዋጽኦ ይኖራቸዋል ብሎ የሚያስቡ ሰዎች አሉ፡፡ እኔ ከመጀመሪያዎቹ ይልቅ ወደ ሁለተኞቹ አደላለኹ፡፡

ይህ ማለት ግን እንደመደበኛ ኮተታም ካድሬ ጠቅላዩ እና መንግስታቸው ለሚሰሩት ስህተት ምክንያት እየፈለጉ በማንኛውም ሁኔታው ውስጥ ፐርሰናሊቲ ከልት መገንባት አይደለም፡፡ ለመጥፎ ነገር ሁሉ ወያኔን ተወቃሽ ለበጎ ነገር ሁሉ ዶ/ር አብይን ተወዳሽ ማድረግ ማድረግም ተገቢ አይደለም፡፡ የሚያወሩትን እንዲራመዱ፣ ታሪካዊ ስህተት ከመሆን ታሪክ እንዲሰሩ ማገዝ እና መገፋፋትን ይጠይቃል፡፡

በመጨረሻም ተቃዋሚው ተቋውሞውን በተደራጀ ሁኔታ ወደማሰማት ማምጣት ይኖርበታል፡፡ እንደበፊቱ ወጣቶች እና ህጻናት ወደ አደባባይ እየወጡ ከየት እንደተተኮሰ ለማይታወቅ ጥይት ሰለባ እንዳይሆኑ ማድረግም ያስፈልጋል፡፡ ተሳትፎ ማድረግ፣ መደራጀት፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎችን፣ የሀገር ሽማግሌዎችን ማገዝ ይገባል፡፡ ስርዓቱን መሠረታዊ ሪፎርም እንዲያደርግ የሚያስገድዱ የተጠኑ የተቃውሞ እንቅስቃሴዎችን መደገፍ ያስፈልጋል፡፡

አቦ ለማ መገርሳ ተቃወሞ በጋለበት ወቅት ወደ አደባባይ ለወጣው ህዝብ እንዲህ ብለው ተናገረው ነበር “ያለውን መዋቅር ተጠቅመን ለውጥ ማምጣት ካልቻልን እኔ እና የትግል አጋሮቼ ወደ እናንተ እንቀላቀላለን፡፡”

ዶ/ር አብይ በዚህ መዋቀር ጫፍ ላይ ተቀምጠዋል፡፡ የህዝብ አጀንዳ አጀንዳቸው እንደሆነ ደጋግመው ተናግረዋለው፡፡ በመዋቅሩ ተጠቅመው ጥቂቶችን እና ራሳቸውን ብቻ ለመጥቀም ከሰሩ የህዝብ ተቃውሞ መዋቅሩን ከስሩ መንግሎ ሲጥለው አብረው መውደቃቸው አይቀርም፡፡ በተለይ በመዋቅሩ ጫፍ ላይ በመሆናቸው የአወዳደቃቸው ክፋት እኔ እሳቸውን አያርገኝ የሚያሰኝ ነው፡፡ መዋቅሩን ተጠቅመው የህዝብ አጀንዳ ለማስፈጸም ከቆረጡ አብረናቸው ነን፡፡ እርሳቸው ፍላጎቱ ኖሯቸው መዋቅሩ የማያሰራቸው ከሆነ ኦቦ ለማ እንደተናገሩት ወደ ህዝብ ተቀላቅለው ትግሉን እንዲቀጥሉ ጥሪ እናስተላልፋለን፡፡

ቀብሶን ኢቲ ፉፋ!!!

Filed in: Amharic