>

ይድረስ የፈጣሪን ስም ለጠሩ ዶ/ር አብይ አህመድ (ዶ/ር ዘላለም እሸቴ)

በ 44 ዓመታት ጊዜ ውስጥ የኢትዮጵያ መሪ በመሆን ለመጀመሪያ ጊዜ “ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ”  እያሉ ንግግርዎን ሲያሳርጉ አይቶ ሕዝበ ኢትዮጵያ በደስታ ተሞልቷል። እኔ ግን እያሉ ያሉት ይህ የማሳረጊያ ቃል በሕዝብ ፊት ብቻ ሳይሆን በአምላክ ፊት ምንና ምንን በሃላፊነት ሊያስጠይቅዎ እንደሚችል የነገሩ ክብደት እጅግ አሳስቦኛል።

የፈጣሪ ስም ከተነሳ ዘንዳ፥ ይህ ፈጣሪ የሚሰጠን በረከት ምንነት ይታወቅ ዘንድ ያስፈልጋል። “ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች” ሲባል ዝንተ አለም አሳልፈን ዛሬን ደረስን። እስከ ዛሬ “ትዘረጋለች” ከማለት አልፈን “ዘረጋች” ወደማለት ሳንሸጋገር ሦስት ሽህ ዓመታት ጠበቅን። በዚህ ፅሁፌ ይህ 3000 ዓመታት ያስቆጠረው ትንቢት ተፈፀመ የሚያስብለው ሁኔታ ምን እንደሆነና፤ የፈጣሪን በረከት የጠየቁት እርስዎ ስለዚህ በረከት ሊኖርዎት የሚገባውን ግንዛቤ ለመጠቆም እሞክራለሁ። የዚህ ጉዳይ ተጠያቂነት ሁላችንንም የሚመለከት ስለሆነ የኛን ድርሻም ለማመላከት እሞክራለሁ።

ይህ ጉዳይ ከሃይማኖት የሚወግን አይደለም። ሃይማኖት የግል ነው፤ ሀገር የጋራ ነው። ሁሉም ሰው ልቡ የፈቀደውን እምነት በነፃነት እንዲለማመድ አምላክ ለሰው ልጆች የሰጠው ነፃ ምርጫን ነው። ስለዚህ መንግስት ሁሉንም ሃይማኖቶች ያለ አድልዎ በእኩልነት የሚያስተናግድ መሆን አለበት። ኢትዮጵያ ልጆቿ በተለያዩ ቤተ እምነት ጥላ ስር ናቸው። ነገር ግን ባብዛኛው ሁሉም ፈሪሃ ፈጣሪ እንዳላቸው መገንዘብ ይቻላል። ሰላምታ በተሰጣጡ ቁጥር እንኳን ይህንን ፈጣሪ በሰላምታቸው ውስጥ ሳያስገቡ አያልፉም።

የጥንት ነገስታት የአምላክን ስም እንደሚጠሩ ሁላችንም የምናውቀው እውነት ነው። የአምላክን ስም ሲጠሩ ግን የኢትዮጵያን መለኮታዊ ጥሪ ያማከለ አልነበረም። እነዚህ ነገስታት የኢትዮጵያን መለኮታዊ ጥሪ አግተው፤ በምትኩ መለኮታዊ ጥሪን በራሳቸው ዘውድ ላይ እንዲያጠነጥን አደረጉ። ስለዚህም የሰለሞን ስረወ መንግስት በመባል የሚታወቀውና የንግሥና ስልጣናቸውን ከእስራኤሉ ንጉሥ ስለሞንና ኢትዮጵያዊቷ ንግስት ሳባ የዘር ቆጠራ ጋር ያቆራኙ በርካታ ነገስታት በምድራችን እንደ ነገሡ ታሪክ ይነግረናል። ከዚህም በላይ የዛጉዬ ስረወ መንግስት የሚባለው የንግስና ስልጣናቸውን ለማረጋገጥ በእስራኤሉ ሙሴና ኢትዮጵያዊቷ ሲፓራ ዘር ቆጠራ ይደገፉ እንደነበር ይታወቃል።  

የኢትዮጵያ መለኮታዊ ጥሪ ግን በአንድ ሰው መሪና በእርሱም ንግስና የሚተረጎም አይደለም። ኢትዮጵያ (ሕዝቧ ሁሉ እንደ አንድ ሆነው) እጆቿን እንደምትዘረጋ ታየላት። የኢትዮጵያ ጉዳይ ከእስራኤል ታሪክም የተለየ ነው። የእስራኤል ታሪክ በግለሰብ ላይ ያጠነጠነ ነበር። ጥንት አንድ ግለሰብ የሆነው አብርሃም እጆቹን ወደ ፈጣሪው ስለዘረጋ፤ ዛሬ አይሁድ ሙስሊምና የክርስትና እምነት ተከታዮች ሁሉም አብርሃምን አባታችን ነው ብለው እንደ አዕማድ ያዩታል። የኢትዮጵያ ታሪክ ግን በሕዝብ ላይ ያጠነጠነ ነው። ስለዚህም የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደ አንድ ሰው ሆኖ፤ ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ ፈጣሪ በዘረጋች ጊዜ፤ ዓለም ሁሉ በምሳሌነት የሚያያት ምድር እንደምትሆን ነገን የሚደርስ ሰው የሚያየው ጉዳይ ነው። የኢትዮጵያ አብሮነት (መደመር) እንደ ዘር ሆኖ የአፍሪካን አብሮነት (መባዛት) ይፈጥር ዘንድ ማን ያውቃል?  

የኢትዮጵያን ነገሥታት ታሪክ የተደመደመው በጃንሆይ ንግሥና ነበር። ከዚያ በሁዋላ እስከ ዛሬ ድረስ ያሉት መንግስታት ራሳቸውን ንጉሥ ብለው አይጥሩ እንጂ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ባለስልጣን ሆኖ አገልጋዩ እንዲሆን መንግስትን ለመምረጥ ስላልታደለ፤ እነዚህ መንግስታት ንጉሦች እንደሆኑ መቁጠር እንችላለን። በዐመፅ ወይም በውርስ ነግሠዋልና።

የኢትዮጵያ መለኮታዊ ጥሪ መቼ ይፈፀማል? ይህ መለኮታዊ ጥሪ እንዲፈፀም አንድ መንግስት አዋላጅ መንግስት ለመሆን መወሰን አለበት። ይህም አዋላጅ መንግስት ስልጣንን ለሕዝብ አስረክቦና ሕዝብን ንጉሥ አድርጎ፤ ንጉሥ የሆነው ሕዝብ በተራው አገልጋይ የሚሆነውን መንግስት በሐቅ ምርጫ እንዲመርጥ ዕድል ሲያገኝ ነው። ያኔ ይህ ንጉሥ ለመሆን የሚታደለው የኢትዮጵያ ሕዝብ፤ በምርጫው ፈጣሪን የምድራችን ንጉሥ እንደሆነ ዕውቅና ለመስጠት ፋታ ያገኛል። ያኔ ኢትዮጵያ እጆቿን ዘረጋች ተብሎ የእፎይታ ዘመን ጅማሬ ይሆንልናል።

ሃይማኖትና መንግስት ለየቅል ሆነው እና ክህደት ተስተናግዶ ሲያበቃ፤ ለመጀመሪያ ጊዜ ፈጣሪ ኢትዮጵያን እንዲባርክ በባለስልጣናት ጉባኤ የተጠየቀበት ጊዜ ቢኖር ዛሬ ነው። ዶ/ር አብይ አህመድ “ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ” በማለት ለሚቀጥሉት መሪዎቻችን ፈር ቀዳጅና ፋና ወጊ ሆነዋል። ይህ አባባል የራስዎን ግንዛቤ እንደ ግለሰብ የሚያሳይ ብቻ ሳይሆን፤ በሕዝብ ልብ ውስጥ ያለውን የጋራ ግንዛቤ ማስተጋባትዎ እንደሆነ ጭምር መቆጠር አለበት። ከእንግዲህ የመንግስትም ሆነ የተፎካካሪ ፓርቲ መሪዎች ይህንን የፈጣሪ በረከት ለመጠየቅ ህሊናቸው ብቻ ፍቃድ ይስጣቸው። ይሁንና ከእነርሱ በላይ ባለስልጣን የሆነ የኢትዮጵያ አምላክ እንዳለ ተዐምረኛዋ ኢትዮጵያ ይታወቅላት።

ታዲያ ለመጀመሪያ ጊዜ ዶ/ር አብይ ይህንን የፈጣሪ ስም ሲጠሩ፤ እንደ ቀድሞ የእግዚአብሔርን ስም ይጠሩ እንደነበሩ ንጉሦች የመንግስትን ንግሥና ለማስቀጠል ሳይሆን፤ ሕዝቡ ንጉሥ የሚሆንበት አዲሲቷ ኢትዮጵያ እንድትወለድ፤ አዋላጅ ባለስልጣን መሆንን ብቸኛ ተልዕኮዎ እንደሆነ መቁጠር ይገባዎታል። ለዚህም በሕዝብ ዘንድ እንደ ስጦታ እየተቆጠሩ እንደሆነ የኢትዮጵያ ልጅ የሆኑት ዶ/ር አብይ አህመድ እርስዎም የሚያውቁት ይመስለኛል።

የተቃዋሚ ፓርቲዎችን ተፎካካሪ ብለው እንደጠሩ ተሰምቶ ደስ አለን። ግን እነዚህን ፓርቲዎች ተፎካካሪ ስለተባሉ እውነትም ተፎካካሪ ሊሆኑ አይችሉም። የዲሞክራሲ ምህዳሩ ከሌለ አማራጭ ሃይል ለመሆን በአሳብ ዙሪያ ለመሰብሰብ አይችሉም። ያላቸው ምርጫ ዲሞክራሲ እስኪወለድ ድረስ መቃወም ነው። ስለዚህ ሌሎች ተፎካካሪ ፓርቲዎች እንዲሆኑ፤ በመጀመሪያ ዲሞክራሲን የሚያዋልዱ አዋላጅ ለመሆን ቆርጠው መነሳት ይኖርብዎታል። አዲሲቷ ኢትዮጵያ የምትወለደው ልጆቿ ሁሉ ሲሳተፉ ስለሆነ፥ በመጀመሪያ ዲሞክራሲ መወለድ አለበት። ያኔ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ተባባሪ አዋላጅ ሆነው ይገለጣሉ። በመጨረሻም አዲሲቷ ኢትዮጵያ በሕዝቧ ንጉሥነት ትወለዳለች። በዚያን ጊዜ ኢትዮጵያ ወደ ፈጣሪ እጆቿን ለመዘርጋት የምርጫ ነፃነት ይኖራታል። እስከ አሁን ግን ለዘመናት የንጉሣውያን መንግስታት እስረኛ እንደሆነች አለች።

የኢትዮጵያ ሕዝብ ንጉሥ የመሆን ዕድል ካገኘ፤ ፈጣሪን የምድራችን ንጉስ እንደሆነ ዕውቅናን በደስታ እንደሚሰጥ የሚያውቅ የኢትዮጵያ አምላክ፥ እስካሁን ኢትዮጵያን ከጥፋት እየጠበቀ ዛሬ ደረስን። ዘረኝነት ከፋፍሎን እንዳያጠፋን ስጋት ውስጥ ገብተን ነበር። ዛሬ ፍቅር አሸንፎ በአንድ ልብ እንደ አንድ ቤተሰብ ለመሆን እየተሰራንና እየተያያዝን ያለንበት ወቅት ነው። የሁሉም ነገር ማሰሪያ ፍቅር እንዲሆን እያደረግን፤ ምድራችን በዲሞክራሲ፥ በፍትህ፥ በመልካም አስተዳደርና በልማት እንድትመነጠቅ ሁላችንም ለበጎ ስራ ተግተን አዲስ ታሪክ ይሰራ።

ዶ/ር አብይ አህመድ ይህንን ታላቅ ተልዕኮ እንዲወጡ፤ ሁላችንም ወደ ፈጣሪ እሳቸውን በፀሎትና በምልጃ የምናቀርብበት ጊዜ ነው። ኢትዮጵያ በምጥ ላይ ነችና ሁላችንም አብረን በምጥ ሆነን ወደ ፈጣሪ እንቃትት ዘንድ ይገባል።

ትልቁ የፈጣሪ በረከት ለዚህ ሁሉ ተልዕኮ መሠረት የሆነውን የኢትዮጵያ ህዝብ ቤተሰብነት ወደ ብርሃን ማምጣት ነው። ይህንንም በተመለከተ አንድ ነገር ልበልና ልቋጭ፦ አሜሪካኖች ስለ አሜሪካ “One Nation Under God” (በአምላክ ስር ያለ አንድ ሕዝብ) ይላሉ። ኢትዮጵያ ደግሞ “One Family Under God” (በፈጣሪ ስር ያለ አንድ ቤተሰብ) ይሁንልን!

እግዚአብሔር ኢትዮጵያን አሰበ

እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርካታልም

ኢሜል ethioStudy@gmail.com

Filed in: Amharic