>

ዶ/ር አብይ አገር ለአገር የሚዞረውስ ለምንድነው? (ሞሀመድ አሊ መሀመድ)

ለመሆኑ ኢትዮጵያን ለኦሮሞ; ለአማራና ለትግሬ ብቻ የሰጠው ማነው?

ሞሀመድ አሊ መሀመድ
–  ዶ/ር አብይ አገር ለአገር የሚዞረውስ ለምንድነው?
–  ኢትዮጵያ ወደ ደቡብ አፈገፈገች እንዴ?
ይህን የምለው ጠቅላይ ሚ/ር አብይ አህመድ አዋሳ ስታዲዬም በተሰበሰበው የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝብ ፊት በተለመደው አገላለፅ “ትንሿ ኢትዮጵያ” ሲሉ ስለሰማሁ አይደለም። ይልቁንም በአዋሳ “ሚሊኒዬም” አዳራሽ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ለውይይት የታደሙ የክልሉ ማህበረሰብ አባላት የሰጧቸው “ቁጭትና ተስፋ”  የተቀላቀለባቸው አስተያዬቶች ኢትዮጵያዊነት “የተዳፈነ ረመጥ” መሆኑን በተጨባጭ አረጋግጠዋል።
ይበልጥ ያስገረመኝ ደግሞ የክልሉ ርዕሰ-መስተዳድር በኢትዮጵያ አንድነት ላይ ያሳዩት የጋለ ስሜት ነው። ርዕሰ-መስተዳድሩ አቶ ደሴ ዳልኬ በሀገራችን ተፈጥሮ የነበረውን አስፈሪ ሁኔታ አስታውሰው ሥልጣን ወደ ዶ/ር አብይ መሸጋገሩን ተከትሎ በህዝቡ ዘንድ “አዲስ ተስፋና ራዕይ” መፈንጠቁን አብስረዋል።
በአዋሳ ሚኒሊዬም አዳራሽ የተሰባሰቡና ከዚያም ውጭ አሰተያዬታቸውን የሰጡ የክልሉ ነዋሪዎች ጠባብ ብሔርተኝነትና ዘረኝነት ምን ያህል እንዳማረራቸው ሲገልፁ ተደምጠዋል። ለኢትዮጵያ አንድነት ያላቸውን ቀናኢነት በማያሻማ አኳኋን የገለፁት ነዋሪዎቹ ዶ/ር አብይን ማመስገን የሚችሉበት ቋንቋ አጥተው በደፈናው “አላህ ከላይ የላከው”  ማለትን መርጠዋል።
ከህዝቡ ስሜትና አስተያዬት በመነሳት የክልሉ ርዕሰ-መስተዳድር “የኢትዮጵያን አንድነት ለማጠናከር የክልሉ ህዝብ ከጎንዎ ነው” በማለት የሰጡትን ማጠቃለያ እንደወረደ ላለመቀበል በቂ ምክንያት አይኖርም። ዱሮም ቢሆን አበው ሲተርቱ “የዓሣ ግማቱ ከጭንቅላቱ” እንዲሉ ከላይ የተጫነው ከፋፋይ የአገዛዝ ፍልስፍና ተጭኖት እንጅ ከሥር ያለውን አመራር ጨምሮ ህዝቡ ለአንድነቱ ሁሌም ቀናኢ ነው።
TeamLema እንደዋዛ ያቀነቀነው ኢትዮጵያዊነት ኦሮሚያን አልፎ መላውን ኢትዮጵያ እንደ ሰደድ እሳት ሲያዳርስ እያየነው ነው። እስካሁን ድረስ ዶ/ር አብይ በተጓዙባቸው ክልሎችና በተገኙባቸው መድረኮች ኢትዮጵያዊነት ሲወደስና አስተሳሰቡም እንደዋዛ ሲታደስ ታዝበናል። በተለይ የደቡብ ኢትዮጵያ ማህበረሰብ አባላት ስለጠባብ ብሔርተኝነት አደጋና ስለአንድነት አስፈላጊነት የሰጧቸው ገንቢ አስተያዬቶች “ኢትዮጵያ ወደ ደቡብ አፈገፈገች እንዴ?” የሚያሰኝ ነው። ዶ/ር አብይም ማህበረሰቡን “የአንድነትና የአብሮነት ድርና ሸማ” በማለት በውብ ቋንቋ ገልፀውታል።
ከዚህ ጋር ተያይዞ ግን አንድ መጥራት ያለበት ብዥታ አለ። ብዙዎቻችን የኢትዮጵያ አንድነትና ህልውና/ዕጣ ፈንታ በኦሮሞ; በአማራና በትግራይ “ልሂቃን” እጅ ላይ የወደቀ ነው የሚል “ጨለምተኛ” አስተሳሰብ ተጠናውቶናል። በርግጥ ባለፉት አራት አሥርተ ዓመታት በተለይ ከሦስቱ ትላልቅ ማህበረሰቦች በወጡ “ልሂቃን” መካከል የተፈጠረው ፖለቲካዊ ንትርክና አጉል እልኸኝነት የኢትዮጵያን አንድነትና ህልውና በእጅጉ ፈትኖታል። ከነዚህ ማህበረሰቦች የወጡ አንዳንድ ጠባብና ግብዝ ፖለቲከኞች “ካልሆነ ሀገሪቱ ትፈርሳለች” በሚል ማስፈራሪያ ሸብበው እንደፈረስ ሊጋልቡን ሞክረዋል።
እኛም እንጠይቃለን;
የኢትዮጵያን ጉዳይ ለኦሮሞ; ለአማራና ለትግራይ ብቻ ማነው የሰጠው?
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ዶ/ር አብይ አፋርን ሳይጎበኙ መደበኛ ሥራቸውን እንዳይጀምሩ ማሳሰብ እወዳለሁ። እዚያ በኢትዮጵያነቱ የማይደራደር; ለኢትዮጵያ ነፃነት የብረት አጥር ሆኖ የኖረ ኩሩ ህዝብ አለ። ዶ/ር አብይም በምድረ-ሉሲ ተገኝተው ብዙ የሚሉት ነገር ይኖራቸዋል።
አንዳንዶች “አገር ለአገር መዞሩን ትቶ ለምን ሥራውን አይጀምርም” ሲሉ ይተቿቸዋል። በእኔ እይታ የአንድ አገር መሪን የሥራ ቅደም ተከተል በቅጡ ካለመገንዘብ የመነጨ ይመስለኛል። ዶ/ር አብይም ይመልሳሉ; “የህዝብን ፍላጎት ሳናውቅ; የአባቶችን ምክር ሳንሰማ ወደሥራ አንገባም” በማለት።
እውነታቸውን እኮ ነው። ዶ/ር አብይ በህዝብ አልተመረጡም። ስለሆነም ቢያንስ በኢህአደሰግ ም/ቤት ከተመረጡ በኋላ የህዝብን ይሁንታ (vote of confidence?) ማግኘታቸው አስፈላጊና ወሳኝ ነገር ነው። ወደ ሥራ ሲገቡ ብዙ ፈተና ይገጥማቸዋል። የመረጣቸው ፓርቲ (በተለይም ህወሓት) በአብዮታዊ ዴሞክራሲ ከፋፋይ ፍልስፍና እንዲመሩ እጃቸውን ለመጠምዘዝ መሞከሩ አይቀሬ ነው። ለጊዜው ያደፈጠ ቢሆንም የዘረኝነትና ከፋፋይነት አስተሳሰብ ገና ሰንኮፉ አልተነቀለም።
ህዝቡም ይጠራጠራል። ለመሆኑ “ያሰሩታል ወይ?” ሲል በአፅንኦት ይጠይቃል። ጥርጣሬው መሠረተ-ቢስ አይደለም። ለጊዜውም ቢሆን መከላከያውና ደህንነቱ በህወሓት እጅ ነው። በዚህ ሁኔታ የዶ/ር አብይ አስተማማኝ ደጀን ማነው? የዶ/ር አብይ አስተማማኝ ደጀን “የአንድነት ተስፋና ራዕይ” የፈነጠቁለት ህዝብ ነው – እናም የአንድነት ኃይሉ!
የእንድነት ኃይሉ ወደ ዶ/ር አብይ አልሄደም። ዶ/ር አብይ ግን ወደ አንድነት ኃይሉ መጥተዋል። ስለሆነም “እንኳን ደህና መጡ” ተብለው የክብር አቀባበል ሊደረግላቸው ይገባል። መንግሥታዊ ሥልጣን ይዘው የአንድነት ኃይሉ ጠብቆ ያቆያቸውን እሴቶች ሲያወድሱ ቢጨበጨብላቸው አይበዛም። ከዚህ በተቃራኒው ጥቃቅን ስህተቶችን መፈለግና አቃቂር ማብዛት “እኛ የሌለንበት ሠርግ አይደምቅ” የሚል ተራ ቅናትና ምቀኝነት መኖሩን ያሳብቃል።
“ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይባርክ!” አለ ዶ/ር አብይ።
እኛም እጆቻችንን ወደ ፈጣሪያችን ዘርግተን “አሜን!!!” ብለናል።
Filed in: Amharic