>

ስለ አኖሌ ሐውልት የግል አስተያየቴ፤ (ውብሸት ሙላት)

የአኖሌ ሐውልት ተሠርቷል፡፡ በመታሰቢያ ሐውልትነት ያቆሙት ኦሮሞ እህትና ወንድሞቻችን እናትና አባቶቻችን ናቸው፡፡
 ስለአኖሌ ታሪክ እውነት መሆን ወይም አለመሆን፣ሐውልቱ ከተሠራ በኋላ ለዚያውም  በአሁኑ ወቅት መከራከር አሰጥ አገባ ዓይነት ምልልስ ውስጥ መግባት ፈጽሞ ተገቢነት ያለው አይመስለኝም፡፡ መከራከር ካለባቸው ኦሮሞ ወንድምና እህቶቻችችን አባትና እናቶቻችን እርስ በራሳቸው ብቻ ነው፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ አማራ መከራከር አለበት ብዬ በፍጹም አላምንም፡፡
አንድ ጉዳይ የሕዝብ አጀንዳ ከሆነ በኋላ ሕዝብ ጋር ክርክር አይደረግም፡፡ ምክንያታዊነት የግለሰብ ባሕርይ እንጂ የሕዝብ አይደለችምና! የሕዝብ ጉዳይ፣የሕዝብ አጀንዳ የሆነን የአኖሌን ሐውልትን በሚመለከት  አማራ ወንድምና እህቶቼ ሐውልቱ ይፍረስ ወይም አይፍረስ ማለት አይገባንም፡፡
የአማራ ብሔርተኝነት ማንንም የማይነካ ሆኖ ሳለ አንዳንድ  የአማራ ወንድምና እህቶቼ የኦኖሌ ሐውልት ካልፈረሰ ….የሚል የመጨረሻ አማራጭ (ultimatum) የሚመስል ለዚያውም  በአማራና ኦሮሞ ሕዝቦች መካከል ውጥረት የሚፈጥር አጀንዳ መፍጠር ተገቢ አይደለም፡፡
ማንም ተጎዳሁ ያለ አካል ለደረሰበት ጉዳት ማስታወሻ ወይም ሐውልት ቢያቆም ጉዳት አድርሷል የተባለው አካል ጉዳት ደረሰብኝ ብሎ የሚያስበውን  ወገን ሐውልትም ሆነ መዘከሪያ እንዳትሠራ፣ከተሠራም አፍርስ ሊለው አይችልም፡፡ የአኖሌን ሐውልት ይፍረስ እያሉ መቀስቀሰ ትርፉ እልህ መጋባት ብቻ ነው፡፡
 በመሆኑም የአኖሌን ሐውልት ጉዳይ የኦሮሞ ወንድምና እህቶቻችን አባትና እናቶቻችን   ከአማራ ወንድምና እህቶቻቸው አባትና እናቶቻቸው ጋር ስላላቸውና ስለሚኖራቸው ግንኙነት ወዳጅነት ፍቀር ተከባብሮና ተዋዶ በአንድነት መኖር ላይ የሚያመጣው ነገር አለ ወይም የለም ማለትም የሚችሉት እነሱው ብቻ ናቸው፡፡   በመሆኑም የአኖሌ ሐውልት ጉዳይ የኦሮሞ ሕዝብ ጉዳይ ብቻ ነው፡፡ አማራ ወንድምና እህቶቼም የአኖሌ ሐውልት ይፈረስ እንዲህ ይሁን እንዲያ አይሁን ማለት የለብንም፡፡
አማራነትንም ኢትዮጵያዊነትንም ሁለቱንም ሳይነጣጠሉና ሳይጋጩ ለማለምለም ማንንም ማስቀየም የለብንም! ሕዝብን ከሕዝብ ጋር እልህ ውስጥ የሚያስገባ አጀንዳ መፍጠር የለብንም፡፡
ኢትዮጵያዊነትም ይለምልም!
Filed in: Amharic