>

ለነጻነት ዋጋ እየከፈሉ ካሉ ታላላቅ እናቶች መካከል (የሚሊዮኖች ድምጽ)

ሁለት እህቶች ናቸው። ሁለቱም የአንድ ወንድ ልጅ እናቶች ናቸው። ሁለቱም አገራቸውን የሚወዱ። ዘር ሳይለዩ ለኢትዮጵያዉያን ሁሉ የቆሙ። ከዚያም የተነሳ ትልቅ ሰቆቃ የደረሰባቸው። ሰርካለም ፋሲል እና አስቴር ስዩም። 
ሰርካለም ፋሲል በሕገ መንግስቱ የተነደነገገዉን መብት በመጠቀም ጻፈች። ነፍሰ ጡር ነበረች።  ላይ ላዩን ስለ ሕግ መንግስት ያወራሉ፤  ግን በተግባር ሕግ መንግስቱ በጫጭቀው ጥለዉታል። ከባለቤቷ ከእስክንድር ነጋ ጋር ወደ ወህኒ ወሰዷት። ብእር በማንሳቷ አመጸኛ ተባለች። በቂ ሕክምና እንዳታገኝ ተከልክላ፣ አንድ ልጇን ናፍቆት እስክንድርን፣ በከፍተኛ ችግርና ስቃይ በቃሊት እሥር ቤት ወለደች። ሁለት አመት አልፎ እርሷም፣ ባለቤቷም ተፈቱ። ብዙም አልቆየም  ባለቤቱ እስክንደር ፣ ወንጀል ሳይፈጽም፣ አገሩን በመዉደዱ እንደገና ታሰረ። አሁን በወህኒ እየተሰቃየ ነው። ሰርካለም ደግሞ ከልጇ ጋር  ለስደት  ተዳረገች።
አስቴር ስዩም፣  ባላት የማስተር ዲግሪ ሕዝቧን እና ወገኗን በጎንደር እያገለገለች ነበር። እርሷም በሕገ መንግስቱ የተደነገገላትን መብት በመጠቀም፣ በምርጫ ቦርድ ሕጋዊ እውቅና ያለው የአንድነት ፓርቲን ተቀላቀለች። ምንም ሳታጠፋ፣ አገሯን እና ህዝቧን በመዉደዷ፣  በታጣቂዎች ታፍና ተወሰደች። በማእከላዊ ብዙ ከተሰቃየች በኋላ በአሁኑ ወቅት በቃሊት እሥር ቤት፣ ብቻዋን እየተዘጋባት ከሰው እንዳትገናኝ እየተደረገ፣ ፍትህ ተነፍጋ፣ በብርቱካን ሚደቅሳ ላይ እንደደረሰው ከፍተኛ የአካልና የስነ ልቦና ቶርቸር እየተፈጸመባት ነው። ሕጻን ልጇ፣ አሳዳጊ እናት አጥቶ፣ በችግረኛ አያቱ ቤት እያደገ ነው።
ይሄ ነው እንግዲህ በዛሬይቱ የወያኔ ኢትዮጵያ፣  የኢትዮጵያዉያን እጣ….. ወደ ወህኒ አሊያም ወደ ስደት። እስከመቼ ግን ? 
እህቶቻችን፣ እናቶቻችን፣ ለመብት፣ ለነጻነት በሚደረገዉ ትግል ከኋላ ሳይሆን ከፊት የሚቀድሙ መሆናቸውን  ሰርካለም ፋሲል እና አስቴር ስዩም አመላካቾች ናቸው። ወያኔዎች በደህንነት ጽ/ቤት፣ በፌደራል ፖሊስና በአጋዚ ጦር ይመካሉ።  እነዚህ ሕሊና የለሽ በጥቅም የተገዙ አገልጋዮቻቸውን በመላክ በመቶ የሚቆጠሩ ዜጎችን በጠራራ ጸሃይ አስገድለዋል። በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያንን በግፍ አሳስረዋል። ሰላማዊ መንደሮችን እንዲቃጠሉ አስደርገዋል።
እነ አስቴር ስዩም ግን  የታጠቀ ሰራዊት የላቸውም። በቤታቸው መሳሪያ አልተገኘም። በእጆቻቸው የወደቀዉን አነሱ እንጂ የቆመዉን ተኩሰው አልጣሉም። የሚተማመኑት በሕዝብ ጉልበት እንጂ በጠመንጃ ጉልበት አይደለም። ወኔ፣ ልብ ስላላቸው ፣ በፍርሃት ስላልተጨማደዱ፣ አምባገነኖች ሊቋቋሟቸው አልቻሉም። አዎን ገዢዎች ያሸነፉ ሊመስላቸው ይችላል። ለጊዜው ሰርካለም ተሰዳለች፣ አስቴር ደግሞ በወህኒ ናት።  አዎን አሁን ጨልሟል። ግን ሊነጋ በጣም ተቃርቧል።
አስቴር እና ሰርካለም፣ የአንድ ወንድ ልጆች እናቶች ብቻ ሳይሆኑ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዉያን እናቶች ናችው። የከፈሉት እና እየከፈሉት ያለው ዋጋ ለኢትዮጵያ ልጆች በሙሉ ነው።  ለነጻነት ለሚደረገው ትግል ላበረከቱት ትልቅ አስተዋጾ፣ እንደ ዜጋ፣ እንደ ኢትዮጵያዊ ምስጋናችንን እና አድናቆታችንን እየገለጽን፣ በእናቶች  ቀን፣  ከታላላቆች የኢትዮጵያ እናቶች፣ ከነጣይቱ ብጡል፣ ከነደራርቱ ቱሉ ጎን መድበናቸዋል።
በአስቴር እና በሰርካለም መንፈስ ፣ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ለመብት እንዲነሱና ቀና እንዲሉ ጥሪ እናቀባለን። ገዢዎች ጥቂቶች ናቸው። እኛ ሚሊዮኖች ነን። እያንዳንዳች ፣ከተነሳን፣ ፣ ከታሰሩ ወገኖቻችን ከነአስቴር ጎን ከቆምን፣ ሁላችንም የድርሻችንን ለማበርከት ከተዘጋጀን፣ የአገራችን ትንሳዔ ቅርብ ነው የሚሆነው።
ለአስቴር ስዩም፣ ለሰርካለም ፋሲል እና በኢትዮጵያና ከኢትዮጵያ ዉጭ ላሉ እናቶች ሁሉ መልካም የእናቶች ቀን ይሁን እንላለን።
Filed in: Amharic