>

ጠቅላይ ሚንስቴር አብይ አህመድን አስመልክቶ አጭር አስተያየት (አበጋዝ ወንድሙ)    

 

   የካቲት 8 ቀን 2010 ዓም ከ ኢህአዴግ ሊቀ መንበርነትና ከ ጠቅላይ ምኒስቴር ስልጣኑ ለመውረድ  የስራመልቀቂያ ማመልከቻ’ ያስገባው ሀይለማርያም ደሳለኝን ፣በማን ልተካ በሚል ባለፉት ሁለት ሶስት ወራት ኢህአዴግ በስብሰባ ተወጥሮ ምጥ ውስጥ ነበር።  

          ይሄንን በማስመልከት ከዛሬ ወር በፊት ‘የኢህአዴግ ምናልባት ብቸኛ የተስፋ ገመድ በለማ መገርሳ የሚመራው አዲሱ  ኦህዴድ ነው’ በሚል አጭር ጽሁፍ ውስጥ፣ ከኦህዴዱ ሊቀ መንበር አብይ አህመድ ውጭ አማራጭ እንዳልነበረው ጠቅሼ ፣ህወሃትም አብይ ላይ የነበረውን ተቃውሞ ወደ ጎን በማድረግ መተባበር እንደሚገባው ሃሳቤን ገልጨ ነበር።

       ከሁሉም በላይ ስልጣንና ራስ ወዳድነቱ ጥያቄ ውስጥ የማይገባው ህወሃት በሀገሪቱ ውስጥ ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ አገናዝቦ፣ ባይዋጥለትም፣ አዋጭ የሆነውን መንገድ ተቀብሎ አብይ የኢህአዴግ ሊቀ መንበርና የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስቴር እንዲሆን ይሁንታውን ሰጥቷል

        አብይ የኢህአዴግ ሊቀ መንበር ሆኖ እንዲመረጥ አብላጫ ድምጽ ማግኘቱ ዕሙን ቢሆንምና፣ድምጽ አሰጣጡን አስመልክቶ ብዙ የተባለ ቢሆንም፣ድምጽ አሰጣጡ በግልና በሚስጥር ስለነበር ማን ለማን እርግጠኝነት ድምጹን እንደሰጠ መናገር አይቻልም።

       ሆኖም፣  በኔ እይታ አብይ  በርካታ ድምጽ ኦህዴድ እና ብአዴን የምክር ቤት አባላት ማግኘቱ እርግጥ ቢሆንም፣ ከደቡብና ከህወሃትም ጭምር ድጋፍ  ማግኘቱን ልንቀበል ይገባል የሚል እምነት አለኝ ህወሃት ፣አብይ ላይ ያለውና የነበረው ጥርጣሬ የኢህአዴግን መሰረታዊ የፖለቲካ መስመር አያስቀጥል ይሆናል በሚል ሳይሆን፣ ያለፉት አመታትን ህዝባዊ ትግል ተከትሎ በኦህዴድ ውስጥ የተፈጠረው መነሳሳትና በራስ መተማመን፣ በኢህአዴግ ውስጥ ያለንን የበላይነት ሊያሳጣን ይችላል የሚለው ነው።

     በህወሃት ውስጥ ያሉ አንዳንድ የቀድሞ  አመራሮችና ደጋፊዎቻቸው ባይዋጥላቸውም የተወሰኑቱ ደግሞ አንጻራዊ ሰላም ሰፍኖ የኢህአዴግ ቀጣይነት እስከተረጋገጠ ድረስ የአብይን ስልጣን ላይ መውጣት በጸጋ የሚቀበሉት ነው የሚል እምነት አለኝ

    ይሄን ስል እነዚህ ክፍሎች ለኦህዴድም ሆነ ለአብይ ስስ ልብ ስላላቸው ሳይሆን፣ ከድርጅታዊ በላይነቱ በላይ ለዚህ ወገን ወሳኙ ጉዳይ የኢህአዴግ ስርዓት እስከቀጠለ ድረስ፣የአብይ ስልጣን ላይ መውጣት ባለፈው 27 ዓመት፣ እነሱና በነሱ ከለላ ያደገው ጥገኛ የህብረተሰብ ክፍል ያከማቸውን ንብረትና የኢኮኖሚ የበላይነት የማይገዳደር መሆኑን ስለሚገነዘቡት ጭምር ነው።

   አብይ አህመድ የኢህአዴግ ሊቀ መንበር ሆኖ ከተመረጠ በኋላ የሀገሪቱ  ጠቅላይ ሚኒስቴር እንዲሆን ድርጅቱ እጩ አድርጎ ለፓርላማው ባቀረበውና ባጸደቀበት ቀን ባደረገው ሰው ሰው የሚል፣ ትሁትና መሳጭ ንግግር የብዙ ኢትዮጵያውያንን ቀልብ ሊስብ ችሏል።

    ከዚህ ቀደም ከነበሩት ሁለት የኢህአዴግ ጠቅላይ ሚኒስቴሮች በተለየ መልክና ይዘት ያቀረበው ንግግርም፣  በሀገሪቱ ሰፍኖ የነበረውን ስጋት በማርገብ ረገድ የራሱን ሚና ከመጫወቱም በላይ ተስፋ ጫሪም ጭምር ነበር።  ባለፉት ሁለት ሳምንታትም በተለያዩ የሀገራችን ክፍል በመዘዋወር ያደረጋቸው ንግግሮች ይሄንኑ ስጋት የማርገብና የተስፋ ጫሪነት ተግባር የሚያጠናክሩ ነበሩ።

      የአብይ ጠቅላይ ሚኒስቴር ሆኖ በኢህአዴግ  መሾም በሀገራችን ላይ አጥልቶ የነበረውን የስጋት ደመና ለጊዜውም ቢሆን  መግፈፉ እርግጥ ቢሆንም፣ የጫረው ተስፋ ምንድነው በሚለው ላይ ግን በጣም የተለያዩ አስተያየቶች እንዳሉ ግልጽ ነው።

      አንዳንድ ወገኖች አብይ የኢህአዴግ አባል መሆኑንና የድርጅቱም ሊቀ መንበር መሆኑን በመዘንጋት በሚመስል መልኩ፣ የሱ ወደ ስልጣን መምጣት የኢህአዴግን አገዛዝ በመሰረታዊ መንገድ እንደሚለውጥ አድርጎ ማሰብ ብቻ ሳይሆን፣ በውስጡ ስላሉ ድርጅቶች በተለይም ስለ ህወሃት ክስመት ወይንም ፍጻሜነት ድረስ በግነት እስከማወጅ ደርሰው ነበር

        እንዲህ ያለ የዋህነት ከስሜታዊነት የሚመነጭ እንጅ በተጨባጭ መሬት ላይ ባለ ሁኔታ የተመሰረተ ባለመሆኑ፣ የአንዳንድ ነገሮች አካሄድ እነሱ በወጠኑት መንገድ ወይንም ፍጥነት አለመሄድን በማየት፣ እነዚህ ወገኖች ወር ባልሞላ ጊዜ ተስፋቸውን ወደ ማጨለም ሲሄዱ እየታየ ነው።

      አብይ  ጠቅላይ ምኒስቴር ለመሆን የበቃው የኢህአዴግ ሊቀመንበር በመሆኑ እንጅ በህዝባዊ ምርጫ አለመሆኑን በሀገራችን የተዘረጋውም ስርዓት ይሄንን የሚፈቅድ እንዳልሆነ፣ ከአብይ ሊገኝ የሚችለው የድርጅቱ ፕሮግራምና ያለው ህገ መንግስት የሚፈቅደው ብቻ እንደሆነና፣ ይሄንንም ለማድረግ መጀመሪያ ድርጅቱን አሳምኖ ይሁንታ ካገኘ ብቻ መሆኑን፣ ከዚህ ውጪ ግን አብይ ብቻውን ሊያደርገው የሚችለው ውሱን መሆኑን መገንዘብ ያሻል።

    ኢህአዴግ ደግሞ እንደ ድርጅት በዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት የሚመራ በመሆኑ ፣ በዘረጋው የአስተዳደር ስርዓት የበላይነት ያለው መንግስታዊ ስልጣን ሳይሆን፣ በኢህአዴግ ውስጥ ያለ ስልጣን በመሆኑ፣ የመንግስት ባለስልጣን ተብለው የሚሾሙ ሁሉ ከኢህአዴግ  ፖሊሲዎችና ውሳኔዎች ውጭ ቢንቀሳቀሱ በተሾሙበት ፍጥነት ከስልጣን አንደሚባረሩ ማወቅ ጠቃሚ ነው።

  ይሄን ሳናገናዝብ  ግን በግሉ ሁሉን ማድረግ የሚችል አድርጎ ከማሰብ ተነስተን እከሌን ይሹም እከሌን ይሻር ይሄን ያድርግ ያን አያድርግ ብሎ ማለት ባዶ ምኞት ከመሆን አያልፍም።

በኔ ግምት፣ የአብይ ቡድን መነሻውም ሆነ መድረሻው  በኢህአዴግ ውስጥ ያሉት ድርጅቶች እኩልነት ጥያቄና በሕገመንግሥቱ የተደነገጉ ህጎች ተግባራዊ የመሆን ጉዳይ በመሆኑ፣ በተወሰነ ደረጃ እነሱን እንኳን ማሳካት ከቻለ የፖለቲካ ምህዳሩን ስለሚያሰፋው፣ ለመሰረታዊ ለውጥ ለመታገል ለሚሹ አመቺ ሁኔታ ስለሚፈጠር በዚያው ልክ ሊደገፍ የሚገባው ነው።

 ይሄን ተግባር  ሊያሳካ ይችላል ወይንም አይችልም፣ ምን አይነትስ ተግዳሮት ያጋጥሙታል፣ እነሱንስ ለመወጣት ምን ያህል ቁርጠኝነት አለው፣ ከእናት ድርጅቱም ሆነ ከሌሎቹ ምን ያህል ድጋፍ ሊያገኝ ይችላል… ወዘተ የሚለው በሂደት የሚታይ ቢሆንም አንዳንድ ጅምሮቹ ውሱን ቢሆኑም  አበራታች መሆናችውን መገንዘብ ይቻላል።  

    ካለፉት አምስትና ስድስት አመታት ጀምሮ አየከረረና አየሰፋ የመጣው ህዝባዊ  ትግል በኢህአዴግ ውስጥ አስገዳጅ ሁኔታ በመፍጠር ስርዓቱን አናግቶ፣ በአንድ ዓመት ተኩል ጊዜ ውስጥ ሁለት አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አሳውጆ አዲስ ጠቅላይ ሚንስቴር እስከመሾም አድርሶታል።

  አብይ የጠቅላይ ሚንስተርነቱ ሹመት በፓርላማ ሲጸድቅም ሆነ ከዛ በኋላ ባደረጋቸው ንግግሮች የገባቸውን ቃላት ተግባራዊ ማድረግ ከቻለ፣አጋጣሚው የሚፈጥረውን ክፍተት በመጠቀም የህዝብ መሰረታዊ ጥያቄዎችን ወደፊት በማቅረብ ትግል ማድረግ ከተቃዋሚ ወገኖች የሚጠበቅ ነው።

  ከዚህ አንጻር ቃል የገባላቸው ጉዳዮች ሁሉ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ ፈጽሞ ሊከወን እንደማይችል በማስገንዘብ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ አሁኑኑ እንዲነሳ የተባበረ ጥሪ ማድረግና ፣ በቀጣይም የጸረ-ሽብር ሕጉን የመሰሉ አፋኝ ህጎች አንዲሰረዙ መታገል ያስፈልጋል።  

አበጋዝ ወንድሙ

Filed in: Amharic