>
5:13 pm - Sunday April 19, 8725

ስብሃት ወአኮቴት ለጀግናው የጎንደር ሕዝብ! (ውብሸት ሙላት)

ጎንደር ኩሩ ነው፡፡ ጎንደር ለክብሩ  (dignity) ሟች ነው፡፡ ከክብሩ የሚያስቀድመውም የለም፡፡ ጎንደሬነት በራሱ ክብር ነው፡፡ “Death with dignity is better than life with humiliation”…. ‘በውርደት ከመኖር በክብር መሞት’ እንዲሉ!
ጎንደር ከራበህ ያበላሃል፡፡ ከጠማህ ያጠጣሃል፡፡ በክብሩ መጥተህ ከጠገብክበት ክብሩን የሚሠጥ፣ በክብሩ የሚደራደር፣ ክብሩን የሚሸጥ ጎንደሬ የለምና ፡፡  “ለጠገበ ጥይት ለራበው እንጀራ” የተባለው የባሕርይው እንጂ የፈጠራ አይደለም፡፡
ጎንደር የሊቃውንት የዐሊም፣የመጽሐፍት የኪታብ አገር ነው፡፡  የእውቀትና የጥበብ መፍለቂያ ነው፡፡  የባሕርይው ነው፡፡ እንደ ሕዝብ መገለጫው ነው፡፡ የሊበን ገብረ ኢትዮጵያን  (ዶናልድ ሌቪን) ሰምና ወርቅን (Wax and Gold) ማንበብ ነው፡፡
ጎንደር ፍቅርም ነው፡፡ ሲወድህ ሥልጣኑን ሳይቀር ይሰጥሃል፡፡  ደንታው አይደለም፡፡  ጎንደር መሬቱን ሰጥቶ አጋርቶ ያኖርሃል፡፡  ጎንደር ለሌሎችም መሬቱን ሰጥቷል፡፡ ለዚህ ደግሞ ኦሮሞ ወንድሞቹና እህቶቹ ዋና ምስክር ናቸው፡፡ ለትግራዋይ ወንድምና እህቱም መሬትም ሥልጣንም አጋርቷል፡፡
ጎንደር አንገቱን ደፍቶ ክብሩ ተገፎ መኖር ሞቱ ነው፡፡ ከነክብሩ በደስታ ይሞት እንደሁ እንጂ ክብር የሌለው ጎንደሬነትን መቼም አይመርጥም፡፡  ዐጼ ቴዎድሮስ እንኳን ራሰቸውን ሲገድሉ በክብር እና በፈገግታ መሆኑን ከሞቱም በኋላ ከንፈራቸውና የፊት ቆዳቸው ምስክር ነበር-የሔንሪ ብላንክን መጽሐፍ ማየት ነው፡፡ ወጣቷ ንግሥት ስንት ግፍና ስቃይ አረመኔዎቹ አድርሰውባት ሁሌም ከፊቷ ክብርና ፈገግታ አይለያትም ነበር-ምክንያቱም ጎንደሬ ናትና!  ጎንደሬ ለአመነበት ሁሉን ነገር በኩራትና በክብር እንጂ ተለማምጦ፣አጎንብሶ፣ለምኖ ክብሩን አይሰጥም-ምክንያቱም ጎንደር ማለት ጀግና ማለት ነውና!
ጎንደር “የማን አባት ገደል ገባ” ባዮች እርስ በርስ ለማጣላት ሰላም ለመነሳት የጠነሱሰለትን ሴራ ቢበጣጥሰውም ሰላም አጥቶ ከርሟል፡፡ ግምቦት ሰባት ምናምን እያሉ ለሞት፣ለእስራት፣ለግርፋት፣ለስደት ሰበብ እየደረደሩ በሺዎች የሚቆጠሩ ልጆቹ ታስረውበታል፡፡ ተገርፈውበታል፡፡ተገድለውበታል፡፡
ጎንደር ማለት ክብር ነውና ጎንደር ማለት ጀግንነት ነውና ጎንደርን አስረኸውም፣ገረፈኸወም ፣ገድለኸውም ክብሩን አይሰጥህም፤ ጀግንነቱ አትነሳውም፡፡ ሲሞትም ከነክብሩ ነው፡፡ ከነጀግንነቱ ነው፡፡ ምክንያቱም ጎንደር ማለት ጀግና ማለት ነውና!
ለወራት ኦሮሞ ወንድምና እህቱ ሲገደሉ ቢያይ የኦሮሞ ደም የኔ ደም ነው አለ፡፡ የራሱ ልጆች ታሥረውበት እንኳን አስቀድሞ እነበቀለ ገርባ ይፈቱ አለ፡፡ እየተገነባለት የነበረውን የሐሰት የጥል ግንብም ናደው፡፡ ኦሮማራ 2008 ዓም. በሐምሌ ወር ጎንደር ላይ ተበሠረች፡፡ አሁን እየሠፋችና እየዳበረች ኢትዮጵያዊነት ሆነች፡፡ ምክንያቱም ጎንደር ለአንዲት ኢትዮጵያ ምን ጊዜም ዋልታና ማገር ናትና!
በዘመነ መሣፍንት ስትታመስ የነበረችውን አገር መልሶ ጎንደሬው የመይሳው ልጅ አንድ አደረጋት፡፡ አሁንም ቢሆን የኦሮሞ ደም የእኛም ደም ነው ብሎ ጀምሮ በአንድ በኩል ጎንደሬነቱን የአማራነቱን  የክብር ሰንደቅን ክፍ አድርጎ በማውለብለብ ሲያበረታታ በሌላ በኩል የተለመደ ፍቅሩን አጋርነቱን ወዳጅነቱን አሳየ፡፡ መልሶም ኢትዮጵያን ከፍ አደረጋት፡፡
ጎንደር ልጆቹን ግብሮ.ለእስርና ለእንግልት ዳርጎ፣ 2008 ሐምሌ ላይ ጎንደር ላይ ያን ችቦ ባይለኩስ ዛሬ ጀግኖች ያልናቸው መሪ ያደርግናቸው ለዚህ ባልበቁ ነበር፡፡ ታስሮ ተንገላቶ ሙቶ ለአማራነት ሰነደቅ፣ኦሮማራነትን ፈጥሮ ችቦ  ለኩሶ አብርቶ እዚህ አድርሷል፡፡ በዘመነ መሣፍንት እንደ ሀገር እየፈራረስን ባለንበት ወቅት ጎንደሬው የመይሳው ልጅ አባ ታጠቅ ካሳ ኢትዮጵያን ታደጋት፡፡ እንደ ዘመነ መሣፍንቱ እየፈረስን በነበርንበት ወቅት ዳግም ኦሮማራን አብሥሮ ዳግም ኢትዮጵያዊነትን ነፍስ ዘራበት-ጎንደር!
“ጎንደር ጎንደር የቴዎድሮስ አገር፣
ላንዲት ኢትዮጵያ ዋልታና ማገር፣
ነፍሱን የሰጣት ለካ ዓለም ንቆ፣
አገር ሊያቆም ነው ቴዎድሮስ ወድቆ፡፡”  አይደል ብላቴናው ያለው፡፡
ጎንደር ሁሉ ነገሩ ጀግና ነው፡፡ ለዚያውም አገር የሚያድን! ፋሲል አገር አዳነ! ቴዎድሮስ አገር አዳነ! የአሁኖቹ ቴዎድሮሶችም አገር አዳኑ! እንደመይሳው ልጅ ሞትን የናቁ እንደውም ሞታቸውን ክብራቸው ያደረጉ የአሁኖቹን አእላፋት ጀግናዎች ቤት ይቁጠራቸው! ታሪክ ግን መቼም አይረሳቸውም!
ያው ጎንደሬነት ጀግንነት ነውና ፈሪዎችን ማሸበሩ አይቀርም፡፡ በጎንደር መነኩሴም ሁን ባልቴት፣ አንድ ፍሬ ሴት ልጅም ሁን ሌላ፣ ጎንደሬ ነህና ጀግንነትህ ሊያሸብራቸው ይችላል፡፡ መቼም እነ አባ ገብረ ሥላሴ፣ እነ ንግሥት ይርጋ፣ እነ እማዋይሽ በክብራቸው በአማራነተቻው ጉዳይ አልደራደራም ቢሉ፣ ቢጀግኑ እንጂ፣ እልሃቸው እንጂ የሚያሸብር ከዚህማ ወዲያ አሸባሪ ሆነው እንዳልሆነ አሳሪዎቹም፣ ከሳሾቹም ፣ ዳኞቹም ልባቸውም ያውቃል፡፡
 ጎንደሬ ስትሆን ሞት አይፈሬ ትሆናለህ፡፡ ሞት ጎንደሬን አያሸብረውም፡፡ ጎንደሬ ግን ሞትን ያሸብራል፡፡ አንድ ብቻ አብነት እንጥቀስ ሞት በጀግና ፊት እርባና ቢስ ከንቱ እንደሆነ የሚያሳይ፡፡ ጣሊያን ኢትዮጵያን ወርራ ይዛ በነበረበት ወቅት ጎንደር መረባ ላይ ህዳር 7 ቀን 1928 የተፈጸመው የተፈጸመ ነው፡፡ የገሪማ ታፈረ፣ጎንደሬ በጋሻው ላይ ተከትቧል ታሪኩ!
የሞት ከንቱነቱ ታሪክ ይህ ነው፡፡ ልጅ አንዳርጌ ደስታ ከልጃቸው ከዋኘው አንዳርጌና ከባለቤታቸው ወይዘሮ ከበቡሽ ደሴ እና ሌሎች 15 ገደማ ወታደሮች ጋር ሆነው በአንድ ኮሌኔል የሚመራ የጣሊያንን ጦርን ከተራራ አላስወረድ ብለው ለአራት ቀን ተዋጉ፡፡ ልጅ አንዳርጌ ወታደሮቻቸውን እየተዘዋወሩ ሲያስተባብሩ ሌላ የጠላት ጦር ደርሶ በሩምታ ተኩሶ ገደላቸው፡፡
ወይዘሮ ከበቡሽ በፍጥነት አስከሬኑን ወደጫካ በመጣል ቅጠል አለበሱት፡፡ ለልጃቸውም አባትህ በዚያኛው በኩል እያጠቃ ነውና በርትተህ ተዋጋ የሰከረ አሳ እንዳያመልጥህ  ብለው ወይዘሮ ከበቡሽ በፍጥነት ላኩ፡፡ ወዲያውኑም ጥሩምባ ይዘው ማዋጋቱን በጀግንነት ከወደቀው ባላቸው ተረከቡ፡፡ ልጃቸውም አንድ የመቶ አለቃ ማእረግ ያለውን የጠላት ወታደር በጥይት ሲመታው አስከሬኑ ተሸከርክሮ ወደ ታች ይወድቃል፡፡ ይሄኔ ወይዘሮ  ከበቡሽ እንዲህ በማለት ፎከሩ፡፡
“የዋኘው እናት አንገት አስደፊ
ከአፋፍ ላይ ሆና ጥሩንባ ነፊ፣
የባህር ልጁ ዋኘው አንዳርጌ፣
ያባቱን ጠላት ጣለው ከግርጌ፣”  እያሉ ፉከራቸውን ቀጠሉ፡፡
ቤተሰብ ሞትን ንቆ በአንድነት ጦርነት ይገባል፡፡ ባል ሞቶ ሚስት አታለቅስም፡፡ ይልቁንም ትፎክራለች፣ታዋጋለች እንጂ፡፡ ስለሀገር ስለክብር ከሆነ በጎንደር ፊት ሞት ከመጤፍ አይቆጠርም፡፡ በጣሊያን፣በደርግ በኢሕአዴግ ዘመንም ጎንደሬ ተገድሏል፣ ታስሯል፣ ተገርፏል፣ተሰዷል፡፡ ሞትም፣እስራትም፣ግርፋትም፣ስደትም ግን ጎንደርን አያሸብረውም፡፡
ጎንደርን በታጠቀ በሠለጠነ ሠራዊት ጣሊያንም ደርግም ኢሕአዴግም ቢወጉት ቢገሉት ቢያስሩት  ቢያሰድዱት ጎንደር ግን ጎንደር ነው፡፡ ከጀግንነት ማማው ዝቅ አይልም፡፡ አሁንም ቢሆን ያው እንደስከዛሬው ጎንደር ነው፡፡ እንደውም እንደጉዳይ በአንድ ቀን ጀግና ይወልዳ፡፡ ከጎንደርነት ሥፍሩ ትንሽም እንኳን አይጎድል! እንደውም ክብሩም፣ጀግንነቱም፣ዕውቀቱም ጥበቡም ሁሉ ነገሩ እያደር ይጠነክራል! ምክንያቱም ጎንደር ነውና!
ስብሃት ለጎንደር ክብሮ ለሚያስከብረው!
ስብሃት ለጎንደር ጀግንነት ባሕርይው ለሆነው!
ስብሃት ለጎንደር እውቀትና ጥበብ አርማ ላደረግው!
ስብሃት ለጎንደር የጣለት ክንድ  ይበልጥ ለሚያበረታው!
ስብሃት ወአኮቴት ለጎንደር ኢትዮጵያን ለሚታደገው!
ጎንደርን አለማመስገን ንፉግነት ነው፡፡ ጎንደርን አለማወደስ ከፍርሃት መጣባት፣ከክብር ይልቅ ውርድን መምረጥ ነው፡፡ የጎንደርን  ጀግንነት ብርታት እና ጽናት አለማድነቅ ከሰው ባሕርይ አይጠበቅም፡፡
የፍቅር፣ የልማት፣ የብልጽግና፣ የነጻነት፣ የፍትሕ፣ የሰላም ዘመን ለጎንደር!
Filed in: Amharic