>

የብሔር ማንነት እና የወልቃይት ሕዝብ ጥያቄ (ጌታቸው ሽፈራው)

~”ሕዝቡ አማራ ነኝ ካለ አማራ ነው ጥያቄው እዚህ ላይ ያበቃል፡፡ ግላዊ ማንነቱን ሌላ ሰው እንዲወሥንለት መጠበቅ የለበትም!”
~”የወልቃይት ሕዝብ ጥያቄ አዲስ ማንነት እንዲሰጣቸው ሣይሆን የነበረውን ማንነታቸው ስለተነጠቁ የተወሰደ ማንነታቸው እንዲመለስላቸው ብቻ ነው፡፡ በመሆኑም የዋልቃይት፣ ጠገዴ፣ ሁመራ እና ጠለምት ሕዝብ የተነጠቀ ማንነት የማስመለስ ጥያቄ መፍትሔ ሊያገኝ የሚችለው አንድም በአስተዳደራዊ ዳኝነት ነው። ይህ ካልሆነም በፍርድ ቤት በሚሰጥ ውሣኔ ነው፡፡ ምንአልባት ሰዎች ይህ ጉዳይ እንዴት በፍርድ ቤት ሊታይ ይችላል የሚሉ ይኖራሉ፡፡ የሰው ልጅ የግል መብት ከሚባሉት አንዱና ዋናው የማንነት መብት ነው፡፡ የሰው ልጅ ንብረቱ ሲወሰድ ለማስመለስ ፍርድ ቤት ፊት ይቆማል፡፡”
~”ምሣሌ በአባትም በእናትም ከትግሬ ደም የተወለዱ ሰዎች በራሣቸው ምርጫ አማራ ሆነው ከፍተኛውን የአማራ ብሔር ሥልጣን የያዙ እንዳሉ የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡ እነዚህ ባለሥልጣኖች እራሣቸው የመረጡትን ብሔር መርጠው ሲሰየሙ ለወልቃይትና ለጠለምት ሕዝብ የደም ማንነቱን እንዳይመርጥ መከልከሉ ወይም ሌላ ሰው በመረጠላቸው ማንነት እንዲኖሩ ማስገደድ ሊያስገርም የሚችል ነው፡፡ ምክንያቱም አማራ ያልሆኑት የመረጡትን አማራ ሲሆኑ አማራ የሆኑት አማራ እንዳይሆኑ ተከልክለዋል ማለት ነውና፡፡”
(አቶ አለልኝ ምህረቱ)
የብሔር ማንነት ማለት አንዱ የማህበረሰብ ክፍል ከሌላው የማህበረሰብ ክፍል በደም ትሥሥር፣ በቋንቋ፣ በባህል እና አንዳንዴም በሃይማኖት እንዲሁም በመኖሪያ ስፍራ የተለየ ክፍል የያዘ ማህበረሰብ ማለት ነው፡፡ በኢትዮጵያ ዛሬ ሣይሆን ከጥንት ጀምሮ በማንነታቸው የሚጠሩ እና የብሔር ማንነት እውቅና የተሰጣቸው በርካታ ብሔረሰቦች እንዳሉ ይታወቃል፡፡ በአሁኑ ወቅት ግን ቀድሞ እውቅና እንዳላገኙ እየተደረገ በሚሰጠው ስብከት በተለይም በትምሕርት ወዳኋላ የቀሩትን ብሔረሰቦች በውስጣቸው ያልሆነ ስዕል እንዲይዙ በተደረገው ዘመቻ ኢትዮጵያዊነታቸውን እንዲረሱ እና ወገኖቻቸውን እንዲጠሉ ከፍተኛ ዘመቻ በመደረጉ አሁን ፍሬው መታየት ጀምሯል፡፡
በዚህ ከፍተኛ ዘመቻ ቀን ከሌሊት ሲሰሩ የቆዩ ካድሬዎች አሁንም በትጋት እየከወኑ የሚገኙ ሲሆን ወገን ከወገን በማጣላት የሚያገኙት ትርፍ ምን እንደሆነ ግን አይታወቅም፡፡ በእኔ እምነት እሳት በእጁ ይዞ ለማቀጣጠል የሚሞክር መጀመሪያ ራሱ እንደሚቃጠል የዘነጋ ይመስለኛል፡፡ እሳት ምንጊዜም ቢሆን መጀመሪያ የሚያቃጥለው የሚያነደውን ሰው ነው፡፡ ይህን የማያውቅ ሰው ካለ ከእንስሳት የሚለይበትን የማሰብ ችሎታ ያጣ ሰው ነው ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡ በማንነት ሰበብ ኢትዮጵያዊነትን እንድናጣ የሚደረገው ጥረት ለጊዜው የታቀደለትን አላማ ያሳካ መስሎ ሊታይ ይችላል፡፡ ነገር ግን የችግሩ ተካፋይ የሆነው ማህበረሰብ ውሎ አድሮ ጉዳት እና ጥቅሙን መለየቱ ስለማይቀር ያኔ እሳት ሲነድ ጭድ ይዘው ሲቀርቡ የነበሩ ድብቅ አጀንዳ ላቸው ክፍሎች ከሁሉ የበለጠ ሊቸገሩ እንደሚችሉ መገመት ያስፈልጋል፡፡ የብሔር ማንነትን እናከብራለን ማለት ብሔርን ከብሔረሰብ ማጋጨት ሣይሆን ብሔራዊ አንድነት እና እኩልነትን ማስተማር አልፎ ተርፎም ፍቅርን በተግባር ማሣየት ነው፡፡ ስለጠቅላላው ይህን ካልኩ የብሔር ማንነት ምን ምን ዓይነት ጅፍል እንዳላቸው እና እንዴት ሊከበሩ እንደሚገባቸው በዝርዝር እናያለን፡፡
የብሔረሰብ እውቅና በኢ.ፌ.ዲ.ሪ ሕገመንግሥት:_
እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ ሕገመንግሥት ስለብሔር ብሔረሰብ ተደንግጎ የምናየው በቡድን መብት (Groop Right) ላይ ብቻ ያተኮረ ነው፡፡ ስለግል ማንነት እና ስለግለሰብ መብት አይጨነቅም፡፡ ለዚህ ምክንያ ደግሞ ሕገንግሥቱ ሲቀረፅ ልዩነትን ለማጉላት እንጅ አንድነትን ለማጠናከር የታሰበበት አይመስልም፡፡ ለዚህ ማስረጃ የሚሆነውም የሕገመንግሥቱ አንቀጽ 39 ነው፡፡ የተጠቀሰው አንቀጽ ከብሔረሰብ ትርጉም አስቀድሞ ብሔረሰቦች የመለያየት መብት ላቸው መሆኑን በንዑስ አንቀጽ አንድ ይገልፅ እና እንዴት እንደሚለያዩ ሥነሥርዓቶቹን በሰፊው ከተነተነ በኋላ ብሔረሰብ ማለት ምን ማለት እንደደሆነ ትርጉም ይሰጣል፡፡ ቅድሚያ መሰጠት የነበረበት ብሔረሰብ ማለት ምን ማለት እንደሆነ ትርጉም ማስጠት ነበረበት፡፡ ይህ የድንጋዎች የአደረጃጀት ችግር ነው ተብሎ አይታለፍም፡፡ ‹‹ከባል ፊት ልጅ ይስጥሽ›› አይነት እንዳሆነም መገመት አይከብድም፡፡ ለማንኛውም የዚህ ፅሑፍ ዓላማ ወደሆነው ርዕስ እንግባ እና በኢትዮጵያ ሕገመንግሥት መሠረት ማንነት እንዴት ሊከበር እና እውቅና ሊሰጠው እንደሚገባ እናያለን፡፡
ከላይ እንደተገለፀው በሕገመንግሥቱም ሆነ የፌዴሬሽን ምክር ቤትን ሥልጣን እና ተግባር ለመወሠን በወጣው አዋጅ ቁጥር 251/11993 ተደንግጎ የምናገኘው ስለመገንጠል እና የራስን የአስተዳደር ክልል ለመወሠን እንጅ ማንነትን ለማሣወቅ ወይም ማንነትን ለማወቅ የሚያስችል አንድም ድንጋጌ የለም፡፡ በሕገመንግሥቱ አንቀጽ 39፣ 46 እና 48 እንዲሁም በአዋጅ ቁጥር 251/1993 አንቀጽ 19 እና ተከታዩ ላይ ተደንግጎ የሚገኘው የራስን የአስተዳደር ክልል ለመወሠን የሚደረግ ጥያቄን ብቻ ነው፡፡ የግል ማንነትን በሚመለከት በሕገመንግሥቱም ሆነ በተጠቀሰው አዋጅ አለመደንገጉ ሁለት ምክንያቶች አሉት፡፡
የግል ማንነት የሚባለው አንድ ሰው ራሱን ‹‹አማራ ነኝ››፣ ‹‹ትግሬ ነኝ››፣ ‹‹ኦሮሞ ነኝ›› … እና የመሣሠሉት ሲሆኑ እነዚህ መብቶች ደግሞ በተፈጥሮ የደም ትሥሥር የሚገኙ መብቶች ስለሆኑ በሕግ መደንገግ አያስፈልጋቸውም፡፡
ከላይ የተጠቀሰው ተፈጥሮአዊ መብት በራሱ ማንነቱን በሚያምነው ሰው የግል መብት የሚወሠን እና ሌላ ሰው ወይም ሌላ የመንግሥት አካል ሊወሥንለት እንደማይገባ ታምኖበት የተተወ ነው ብለን እንገምት፡፡ ነው ብለን ለማመን ግን የማያስችለን በቂ ምክንያት አለ፡፡
ይኸውም ጥቂት ሰዎች የደም ትሥሥር ሣይኖራቸው የሌላውን ማንነት ይዘው በሥልጣን ላይ ሲንደላቀቁ እውነተኛ የደም ትሥሥር አለን ብለው የተነጠቀ ማንነት እንዲመለስላቸው የሚጠይቁ ደግሞ ሕገመንግሥቱ በማይፈቅደው ሁኔታ ከላይ ከታች ሲሉ እንዲቆዩ ተደርጎ አሁን የአሸባሪ ቡድን አባላት ናችሁ ተብለው እስር ቤት ተወርውረዋል፡፡
የወልቃይት ሕዝብ ጥያቄ እና ሕገመንግሥቱ:_
የዋልቃይት፣ ጠገዴ፣ ሁመራ እና ጠለምት ሕዝብ ለበርካታ ዓመታት ማንነቴን ተነጥቄአለሁ እያለ ይጮሀል፡፡ መልስ ሣያገኝ የነበረው የዋልቃይት፣ የጠገዴ፣ የሁመራ እና የጠለምት ጉዳይ ሐምሌ 5 ቀን 2008 ዓ/ም ጎንደር ላይ በአስተዳደራዊ ችግር ምክንያት በድንገት እንዲፈነዳ ተደረገ፡፡ የፈነዳው ታምቆ የቆየ ችግርም ጊዜ ሣይወስድበት መላውን የአማራ ሕዝብ አነቃነቀ እና ለ25 ዓመታት በኢትዮጵያ ሕዝቦች ልብ ውስጥ ተሠንቅሮ የቆየውን የዘረኛነት ሰንሰለት የሚሰብር የአንድነት መልዕክት ሐምሌ 24 ቀን 2008 ዓ/ም ጎንደር ላይ በተደረገው ታላቅ ሰላማዊ ሰልፍ ‹‹የኦሮሞ ሕዝቦች ደም ደማችን ነው›› በሚል መሪ መፈክር በርካታ የአንድነት ስብከቶችን የያዙ መልክቶች በአደባባይ ላይ ወጥተው ዓለምን በአንድ ጊዜ ጉድ በማሠኘት ለ8 ወራት ሲቀጣጠል የቆየውን የኦሮሞ ሕዝቦች ተቃውሞ አጉልቶ አወጣው፡፡ በጎንደር ሰልፍ ላይ የወጡ መፎክሮች እና በባነር ላይ የተፃፉ መልዕክቶች የአማራን ምዕራባዊ ከፍል ማለትም ባህርዳር፣ ፍኖተሰላም፣ ደብረማርቆስና ሌሎች ትንንሽ ከተሞችን ካዳረሱ በኋላ ከኢትዮጵያ አልፈው በዓለም ባሉ ኢትዮጵያውያን እየተንፀባረቁ ለዓለም መንግሥታት እየቀረቡ ሰፊ ሽፋን አግኝተዋል በአደባባይ ደጋግመው ተገልፀዋል፡፡ ‹‹ጎንደር ውስጤ ነው›› የሚል አገላለፅም በውጭ ሀገራት ሲደረጉ በነበሩ ሰልፎች ሲታዩ ቆተዋል፡፡ እዚህ ላይ የምንረዳው ጎንደር ላይ የተደረገው ታላቅ ሕዝባዊ ሰላማዊ ሰልፍ የአሸባሪነት ባህሬ እንዳልነበረው እና የመብት ጥያቄ እንደሆነ በግልፅ ያስረዳል፡፡
ሐምሌ 24 ቀን 2008 ዓ/ም ጎንደር ከተማ ላይ የተደረገው የሕዝብ ሰላማዊ ሰልፍ በሕገ መንግሥቱ የተሰጠውን መብት ያረጋገጠ እውነተኛና ዓለምን ያስደመመ ታላቅ ሰላማዊ ሰልፍ ነበር፡፡ በዚህ ዕለት የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎችም አንድም ጥይት ወደሰማይ እንኳን ሣይተኩሱ ሰልፉ በሰላም መጠናቀቁ መንግሥት ትክክለኛ ግዴታውን ተወጥቶ ነበር ለማለት ያስችላል፡፡ ነገር ግን ይህ ሁኔታ ባለመቀጠሉ ከዚህ ቀን በኋላ በባህርዳርና በተለያዩ የአማራ ክልል ከተሞች የተደረጉ ሰልፎች የብዙ ሰዎች ሕይዎት ያለፈባቸው፣ ንብረቶች የወደሙባቸው ሲሆኑ እያደር ወደግጭት ተለወጠ፡፡ እንደእኔ እምነት መንግሥት ታጋሽነቱን ቀጥሎ ጥያቄዎች ሁሉ በሰላማዊ መንገድ እንዲፈቱ ጥረት አደርጎ ቢሆን ኖሮ አሁን የተፈጠረው ሁሉ ሊፈጠር ባልቻለ ነበር፡፡ ለ40 ዓመታት በተለያዩ የፖለቲካ ሰዎች እና በወልቃይት ጠለምት ተወላጆች በየጊዜው እየተነሣ ነገር ግን መልስ አጥቶ የነበረው የማንነት ጥያቄ ራሱን የቻለ የፖለቲካ አጀንዳ ሆኖ ብዙ አነጋገረ፡፡
በተለይም ከመንግሥት ባለሥልጣናት በየቀኑ የሚቀያየሩ ታቃራኒ መልሶች ሲሰጡ ስለነበር ሕዝቡን ወደአመፅ ሲገፋፉ መንግሥት ደግሞ ሰላማዊ መፍትሔ ከመፈለግ ይልቅ በኃይል እንዲቆም በመሞከሩ ሕዝብን እና መንግሥትን የበለጠ አራራቀ እንጅ አላቀራረበም፡፡ እንደኦሮሞ ሕዝቦች ተቃውሞ እያደር እየሰፋ እየተቀታጠለ ሄደ እንጅ እንደታሰበው በኃይል ዝም ማሰኘት አልተቻለም፡፡ እንግዲህ የፅሑፉ መነሻ የሊዝ ሕግ መዘዝ ሲሆን በዚህ ምክንያት ሆድ ባሰኝ በሚሉ ሕዝቦች በመሬት ጉዳይ ከተነሳው ተቃውሞ ጋር ስለተቀላቀለ ከዚህ ጋር አያይዠ በሊዝ ሕግ መዘዝ በከፊል መልስ በማግኘት ‹‹የጋሙጎፋ ሰው ነው ካርታውን የሠራው›› ስለተባለለት ታላቁ የራስ ደጀን ተራራ (የአማራን እና የትግራይን ክልል የሚያዋሥን ካርታ) እና እስከአሁን መልስ ላላገኘው ስለወልቃይት ጠለምት ጉዳይ በዚህ ፅሑፍ መጥቀስ አስፈላጊ ነው ብየ ስላመንኩ መጠነኛ አስተያየት ሰጥቸ አልፋለሁ፡፡
በነገራችን ላይ በልማድ ‹‹የራስ ዳሸን ተራራ›› እየተባለ የሚጠራው ትክክል እንዳልሆነ እና እውነተኛ ስሙ ‹‹ራስ ደጀን ተራራ›› መሆኑን የአካባቢው ታላላቅ ሰዎች ገልጸውልኛል፡፡ ይልቁንም ‹‹ዳሸን›› የሚለው ቃል እየተለመደ የሄደው ቱሪስቶች በብዛት የማይለዩበት ተራራ በመሆኑ የአማርኛውን ቃል በትክክል መናገር ሲከብዳቸው ‹‹ደጀን›› ለማለት ‹‹ዳሸን›› የሚለውን ቃል እየተጠቀሙ በጉብኝት ዘገባቸው ላይ እየፃፉት ስለተለመደ ነው የሚል አስተያየት አላቸው፡፡ ይህ አባባልም ትክክል የሚመስል ስለሆነ ከአካባቢው ሕዝብ የበለጠ የተራራውን ስም የሚያውቅ ሊኖር ስለማይችል ‹‹የራስ ደጀን ተራራ›› ብለን ልንጠራው ይገባል፡፡ ምክንያቱም ጥንታዊ ስሞችን መቀየር አንዱ የታሪክ ማጥፊያ ዘዴ ስለሆነ ያለምንም ምክንያት ታሪካዊ ስሞችን መቀየር ታሪክ የለሽ እንደመሆን ያስቆጥራል፡፡ በተለይም በዚህ ወቅት በርካታ የሀገራችን ከተሞች እና አካባቢዎች የዩንቨርሲቲ ስሞች ሣይቀሩ ያለምክንያት ወይም የውጤት ለውጥ ሣይኖር በፊደልና በመሣሠሉት ሣይቀር ሲቀየሩ ይታያል፡፡ ለምሣሌ ዓለም ማያ ዩንቨርሲቲ ‹‹ሐሮማያ ዩንቨርሲቲ››፣ አዋሣ ‹‹ሀዋሣ›› … ተብለው ተቀይረዋል፡፡
በአንድ ወቅት የአማራ ክልል ፕሬዝዳምት በቴሌቪዥን ቃለምልልስ ሲሰጡ ‹‹የትግራይ ፀገዴ›› ‹‹የአማራ ጠገዴ›› እያሉ ሲናገሩ ጠገዴ ያው ጠገዴ መሆኑ እየታወቀ በ ‹‹ፀ›› እና በ ‹‹ጠ›› ፊደላት ሊሸነግሉ መሞከራቸው አስገራሚ ነበር፡፡ ‹‹ፀ›› ፊደል ተጨምሮ የሚነገርበት ቃል ሁሉ የትግራይ ነው የምንል ከሆነ ‹‹ፀያፍ›› ብለን ብንናገር ትግርኛ መሆኑ ነው፡፡ ‹‹ፀ›› ፊደል የሚጨመርበት ብቻ የትግራይ ነው ብለን ከወሰድን ደግሞ ‹‹ጠለምት ወረዳ›› ተብሎ የሚታወቀው አብዛኛው ቦታ ለምን የትግራይ ክልል ሆነ? ለምን እንቆቅልሾች እንደሚበዙም አላውቅም፤ ሀገር የሁሉም ሰው ናት ታሪኳ ቢጠበቅ ማንም አይጎዳም፤ ታሪኳ ቢበላሽ ግን ሁሉም ተጎጅ ነው፡፡ በአንድ ሀገር የታሪክ ብልሽት ተጠቃሚ የሚሆኑት ባዕዳን እና የወቅቱ የባዕዳን ጉዳይ አስፈፃሚዎች ብቻ ናቸው፡፡ የባዕዳን ጉዳይ አስፈፃሚዎችም ቢሆኑ ለጊዜው ቁሣዊ ተጠቃሚዎቹ ይሆኑ እንደሆነ እንጅ የሕሊና ተጎጅዎች ናቸው፡፡ ወደተነሣሁበት ጭብጥ ስመለስ የራስ ደጀንን ተራራን፣ የመተማን፣ የአርማጭዎን እና የቋራን ምዕራባዊ ክፍሎች ወደትግራይ ክልል አድርጎ ካርታ የሠራው የጋሙጎፋ ሰው ነው የሚለው የመንግሥት ባለሥልጣኑ አባባል ብዙዎችን ፈገግ ያስደረገ ነው፡፡ እንኳን የሀገር ካርታ የቅር እና 100 ካሬ ሜትር የቤት መሥሪያ ካርታ እንኳን የሚሠራው በባለሙያ ነው፡፡ የካርታ ባለሙያ አስከሆነ ድረስ የጋሙጉፋ ሰው የሀገር ካርታ የማይሠራበት ምን ምክንያት አለ? በሌላ አባባል የሀገር ካርታ የሚሠራው በየጎጡ ተወላጆች ብቻ ነውን? የሀገር ካርታ ሲሠራ በርካታ ጥናቶች ተደርጎበት፣ ማስረጃዎች ተሰባስበው እና በዘመናዊ መሣሪያም ታግዞ ስለሆነ ካርታውን የማንኛውም ጎጥ ተወላጅ ቢሠራው እንዲህ ዓይነት ጉሉህ ስህተት ይሠራል ተብሎ ስለማይታሰብ ‹‹ታሪካዊ መልስ›› ተብሎ ቢታለፍ ከሚሻል በቀር የጋሙጎፋ ሰው ስለሠራው ስህተት ነው ብሎ መናገር ግን መልሱ በውስጡ የያዘውን መልእክት የሚያውቁት ተናጋሪው ብቻ ናቸው፡፡
የሆኖ ሆኖ ካርታውን የሠራው ሰው የጋሙጎፋ ሰው ነው ሲባል የራስ ደጀን ተራራ በትግራይ ክልል ይገኛል በማለት በመማሪያ መፃህፍቶች ውስጥ የፃፈው የየትኛው ብሔር ተወላጅ እንደሆነ ግን እስከአሁን አልታወቀም፡፡
ወደዋልቃይት ጠገዴ ጉዳይ እንመለስ እና እንደሚታወቀው የዋልቃይት የሁመራና የጠለምት ሕዝብ ጥያቄ አማራዎች ስለሆንን ያለፍላጎታችን ትግሬ መሆን አንፈልግም የሚል ነው፡፡ የማንነት ጥያቄአቸውን በተመለከተ ከሕገመንግሥቱ አንጻር ትንሽ አስተያየት መስጠት ያስፈልጋል፡፡ የማንነት ጥያቄ ሁለት ዘርፎች አሉት፡፡ 1ኛው የራስ (የተናጠል) ማንነት ለምሣሌ የደም ትሥሥርን ተመርኩዞ የሚነሣ አማራ ነኝ፣ ትግሬ ነኝ፣ ኦሮሞ ነኝ፣ የሚል እና የመሣሠለው ሲሆን 2ኛው የቡድን ማንነት ማለትም የቡድን መብት እንዲከበር የራስ አስተዳደር እንዲሰጠው ወይም ሌላ የቡድን መብት እንዲከበርለት የሚጠይቅ የጋራ ጥያቄ ነው፡፡ ከዚህ አንፃር የዋልቃይትና የጠለምት ሕዝብ የመጀመሪያው ጥያቄ የደም ትሥሥርን፣ ባህልን፣ ወግን እና ልማድን መሠረት አድርጎ አማራዎች ነን የሚል በመሆኑ ብዙ ሕዝቦች ማንነታቸው እንዲከበር ቢጠይቁም ጥያቄአቸው የየአንዳንዱ ሰው የግል ማንነት ጥያቄ ስለሆነ የቡድን ጥያቄ በሚነሣበት ወይም የቡድን መብት በሚጠየቅበት ሕገመንግሥታዊ ሥርዓት የሚታይ አይደለም፡፡ በዚህም መሠረት የወልቃይትና የጠለምት ሕዝቦች ጥያቄ በራሣቸው በሕዝቦቹ ብቻ የሚወሠን እንጅ በሌላ በማንኛውም የመንግሥት አካል ሊወሠን የሚችል አይደለም፡፡ ዋቢያችን ሕገመንግሥቱ ስለሆነ ድንጋጌዎችን እንመልከት፡፡ በሕገመንግሥቱ አንቀጽ 39፣ 46 እና 47 ላይ የተገለፁት ሁሉም ስለቡድን መብት የሚናገሩ ናቸው፡፡ የግል መብትን በሚመለከት ማንኛውም ሰው ማንነቱን መወሠን የሚችለው እራሱ ስለሆነ የሕግ ሽፋን ባለማስፈለጉ ይመስላል በሕገ መንግሥቱ ስለግል ማንነት በግልፅ የተደነገገ ነገር የለም፡፡
በርግጥም ግላዊ ማንነት በዘር ሐረግ በደም ትሥሥር የሚገኝ እና በራሱ በግለሰቡ ብቻ የሚወሠን ተፈጥሮአዊ መብት ስለሆነ በተፈጥሮ የተገኘውን መብት በሕግ እንደሚገኝ እንደ ዲሞክራሲ መብት ከለላ ማበጀት አያስፈልግም፡፡ ከለላ ማበጀት ካስፈለግም በተፈጥሮ የተገኘው መብት እንዳይጣስ ብቻ ሊሆን ይገባል፡፡ የግል ማንነትን በተመለከተ አንዱ የሌላውን ሰው ማንነት ሊወሥን እንደማይችል ትክክለኛ ማስረጃ የሚሆን ምሣሌ ማቅረብ ይቻላል፡፡ ቁጥራቸውን እና ስማቸውን መግለፅ አስፈላጊ ባይሆንም በተጨባጭ የምናውቃቸው ራሣቸውን በሚፈልጉት ማንነት ወሥነው ከደም ትሥሥራቸው ውጭ እራሣቸው በመረጡት ማንነት የመንግሥት ሥልጣን የያዙ በርካታ ሰዎች እንዳሉ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ስለሚያውቅ ስም መዘርዘር አያስፈልገኝም፡፡ ለምሣሌ በአባትም በእናትም ከትግሬ ደም የተወለዱ ሰዎች በራሣቸው ምርጫ አማራ ሆነው ከፍተኛውን የአማራ ብሔር ሥልጣን የያዙ እንዳሉ የአደባባይ ምስጢር ነው፡፡ እነዚህ ባለሥልጣኖች እራሣቸው የመረጡትን ብሔር መርጠው ሲሰየሙ ለወልቃይትና ለጠለምት ሕዝብ የደም ማንነቱን እንዳይመርጥ መከልከሉ ወይም ሌላ ሰው በመረጠላቸው ማንነት እንዲኖሩ ማስገደድ ሊያስገርም የሚችል ነው፡፡ ምክንያቱም አማራ ያልሆኑት የመረጡትን አማራ ሲሆኑ አማራ የሆኑት አማራ እንዳይሆኑ ተከልክለዋል ማለት ነውና፡፡
በርካታ ሰዎች የሕግ ባለሙያዎችም ጭምር የወልቃይት እና የጠለምት ሕዝብ ማንነት በሕገመንግሥቱ አንቀጽ 47 መሠረት ሊታይ ይገባል ሲሉ እሰማለሁ፡፡ እንዲያውም በአንድ ወቅት በአማራ ክልል ቴሌቢዥን የተጋበዙ አንድ የሕግ ባለሙያ የወልቃይት ጠለምትና ሁመራ ሕዝብ ጥያቄ ሊፈታ የሚችለው በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 48 መሠረት ነው ሲሉ በአይኔ አይቸ በጆሮየ ሰምቻለሁ፡፡ ለመሆኑ የወልቃይት፤ የሁመራና የጠለምት ሕዝብ የአማራ ነኝ ጥያቄ በየትኛው አግባብ ነው የሕግ መንግሥቱ አንቀጽ 48 ላይ ሊወድቅ የሚችለው፡፡ ሕዝቦቹ ያነሱት ጥያቄ እኮ የራሣችን የአማራ ማንነት ይመለስልን የሚል እንጅ የክልል ድንበር እንዲወሥንላቸው አይደለም፡፡
የሕዝቡ ጥያቄ ማንነታችን የደም ትሥሥራችን አማራ ነው የሚል ብቻ ከሆነ በምን አግባብ የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 48 ተፈፃሚ ሊሆን ይችላል? የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 48ስ በግለሰብ ጥያቄ የሚታይ ነው ወይ? በርግጥ የወልቃይት፣ ሁመራና የጠለምት ሕዝብ ጉዳይ በአማራ ክለል መንግሥት ተጠይቆ ቢሆን ኖሮ የሕገመንግሥቱ አንቀጽ 48 ተግባራዊ እንዲሆን አስፈላጊ በሆነ ነበር፡፡ ነገር ግን የአማራ ክልላዊ መንግሥት አስቀድመው ወደትግራይ ያልተከለሉትን አማራዎች ለትግራይ ክልል ፈርሞ ሲያስረክብ እንጅ የወለቃይትን ሕዝብ ጥያቄ የራሱ ጥያቄ የአማራ ክልል መንግሥት ጥያቄ ለማድረግ ሀሣብ እንደሌለው ጳጉሜን 2 ቀን 2009 ዓ/ም በአቶ ገዱ አንዳርጋቸው ‹‹የአማራ ክልል መንግሥት ፕሬዝዳንት›› እና በአቶ አባይ ወልዱ የትግራይ ክልል ፕሬዝዳንት መካከል የተፈረመው ውል በቂ ማስጃ ነው፡፡ እዚህ ላይ ግን የሕገመንግሥቱ አንቀጽ 46(2) በዚህ ክፍልም እንደገና ሊታይ የሚገባው ነው፡፡
ቀደም ሲል ከላይ የተጠቀሰው የሕገመንግሥት ድንጋጌ በተተነተነበት ክፍል እንዳየነው የአንድን ክልል ወሠን ለመለየት ወይም አንድን ሕዝብ ከአንድ ክልል ወደሌላ ክልል ለመስጠትም ሆነ ለመቀበል የሕዝቦች ፈቃድ የግድ አስፈላጊ እንደሆነ አይተናል፡፡ የሕገመንግሥቱ ድንጋጌ በግልፅ የሚናገረው የአንድ ክልል ወሠን ከሚለይበት ወይም ሕዝቦች ወደሚስተዳደሩበት ክልል ከመነገሩ በፊት ሕዝቦቹ ራሣቸው ፈቃደኝነታቸውን መጠየቅ እንዳለባቸው በሕገመንግሥት የተሰጠ የማይጣስ መብት ነው፡፡ ጳጉሜን 2 ቀን 2009 ዓ/ም በሁለቱ ሰዎች መካከል የተፈረመው ውል ግን ከአማራ ክልል ወደትግራይ ክልል የተገፈተሩትን ግጨው የሚባል አካባቢ ሕዝቦች ፈቃድ አላገኘም ወይም አልተጠየቁም፡፡ እንግዲህ አንድ ሰው የአንዱን አካባቢ ሕዝብ ብድግ አድርጎ አሣልፎ የሚሸጥ ከሆነ የባሪያ ንግድ በተዘዋዋሪ መንገድ ተመልሶ መጣ ማለት ይቻላል፡፡ እንዲያውም አንዳንድ ሰዎች ‹‹ገዱ አንዳርጋቸው የግጨውን አካባቢ ሕዝብ ለአቶ አባይ ወልዱ የእንቁጣጣሽ ስጦታ አበረከተ›› በማለት የሚናገሩ አሉ፡፡ ከሕገመንግሥቱ አንፃር ይህ አባባል እውነትነት አለው፡፡ ምክንያቱም አንድን ሕዝብ ያለፈቃዱ አንድ ባለሥልጣን እንደፈለገው የሚሰጠው እና የሚያዝበት ዕቃ ከሆነ ‹‹የአዲስ ዘመን ስጦታ›› የሚለው አባባል በፍፁም ስህተትነት የለውም፡፡
ወደዋናው ነጥብ ስንመለስ አንዳነድድ የፖለቲካ ሰዎች እና የሕግ ባለሙያዎች እንደሚሉት ግን የወልቃይት ጠገዴ ሁመራና ጠለምት ሕዝቦች የማንነት ጥያቄ በሕገመንግሥቱ አንቀጽ 47 እና 48 መሠረት የሚታይ አይደለም፡፡ የደም ማንነት ጉዳይ እና የመሬት አከላለል ጉዳዮች ወይም የቡድን ማንነት ጥያቄ እና የግል ማንነት ጥያቄ ፈፅሞ የማይገናኙ እና የተለያዩ ናቸው፡፡ ብዙዎችም የወልቃይትና የጠለምት ሕዝቦች የማንነት ጥያቄ በሕገ መንግሥቱ መሠረት እንዲወሠን አስተያየት የሚሰጡት የመሬት አከላለል ጥያቄን ከግል ማንነት ጋር አዳምረው  በመመልከት፣ እንዲሁም የተነጠቀ መብትን ለማስመለስ የሚቀርብ ጥያቄን እና አዲስ ማንነት የሰጠን የሚል ጥያቄን አለያይቶ አለማወቅ ይመስለኛል፡፡
በእኔ በኩል ግን ሁለቱ ጥያቄዎች በተናጠል የሚታዩ የተለያየ የሕግ ሽፋን ያላቸው ናቸው፡፡ ከላይ እንደጠቀስኩት የግል ማንነት የሚወሠነው በራሱ ማንነቱን በሚፈልገው ሰው ብቻ ስለሆነ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 47 እና 48 ላይ ያሉት ድንጋጌዎች ለእንደዚህ ዓይነቱ ጉዳይ አስፈላጊ አይደሉም፡፡ ሕዝቡ አማራ ነኝ ካለ አማራ ነው ጥያቄው እዚህ ላይ ያበቃል፡፡ ግላዊ ማንነቱን ሌላ ሰው እንዲወሥንለት መጠበቅ የለበትም፡፡ ቀጣይ ጥያቄውም ቢሆን ሊስተዳደሩበት የሚፈልጉትን ክልል የመምረጡ ጉዳይ ስለሆነ ማንነታቸውን እስካስመለሱ ድረስ የሚስተዳደሩበትን ክልልም የመምረጡ መብት የራሣቸው የሕዝቦቹ በመሆኑ ሌላ ወሣኝ ክፍል አያስፈልግም፡፡ የሕገመንግሥቱን አንቀጽ 46(2) መመልከት ያስፈልጋል፡፡
ከመንግሥት የሚጠበቀው ሕዝቦቹ ሊተዳደሩበት ወደፈለጉት ክልል እንዲካተቱ አስተዳደራዊ እውቅና መስጠት ብቻ ነው፡፡ የዋልቃይትና የጠለምት ሕዝብ የማንነት ጥያቄ በሕገመንግሥቱ አንቀጽ 47 እና 48 መሠረት መታየት የማይችለው ከዚህ በሚከተሉት ምክንያቶች ነው፡፡ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 47(3) እና አንቀጽ 48 መሠረት መፍትሔ መፈለግ የሚቻለው ጥያቄዎቹ ከዚህ የሚከተሉት ዓይነት  የቡድን ወይም ራስን የማስተዳደር ጥያቄዎች ከሆኑ ብቻ ነው፡፡
በአንድ ክልል ውስጥ የነበረ ከክልሉ ሕዝብ የተለየ ስነልቡና ማንነት እና ቋንቋ ያለው ብሔረ ሰብ (ቡድን) በሕገመንግሥቱ አንቀጽ 47(2) መሠረት የራሱን ክልል ለመመሥረት ጥያቄ ያቀረበ እንደሆነ በንዑስ ቁጥር 3 ከ ‹‹ሀ›› እስከ ‹‹መ›› ያሉት መስፈርቶች ሲሟሉ የራሱን ክልል እንዲመሠርት ለማድረግ፡፡
በክልሎች መካከል የድንበር ጥያቄ የተነሣ እንደሆነ የድንበር ጥያቄው በሕገመንግሥቱ አንቀጽ 48 ላይ በተደነገገው መሠረት የድንበር ወሠን እንዲለይ ማድረግ ሲሆን ብቻ ነው፡፡
የወልቃይትና የጠለምት ሕዝብ ጥያቄ ከላይ ከተጠቀሱት ከሁለቱም ነጥቦች በተለየ ሁኔታ እኛ አማራ ነን በነበረው የአማራ ባህላችን ውስጥ መኖር እንፈልጋለን የሚል ስለሆነ እንዲህ ዓይነቱን የማንነት ጥያቄ ለመመለስ ከመንግሥት የሚጠበቀው ሣይፈልጉ ከገቡበት ማንነት መውጣታቸውን እውቅና መስጠት ብቻ ነው፡፡ ያለሰዎቹ ፍላጎት በግድ የሰዎችን ማንነት መለወጥ አይቻልምና፡፡ ቀደም ብየ ከላይ እንደገለፅኩት አንድ ሰው እራሱ ፈቅዶ እና ወዶ ትግሬው አማራ ትግሬው ኦሮሞ ሊሆን ይችላል ተችሏልም፡፡ ከራስ ፈቃድ ውጭ ያልሆነውን እንዲሆን ማስገደድ ግን መሠረታዊ የሆነውን ሰብአዊ መብት መጣስ ነው፡፡ በዋልቃይትና በጠለምት ሕዝብ ጥያቄ ላይ አከራካሪ የሚሆነው የሰዎቹ ማንነት አይደለም ሰዎቹ አማራ ነን ብለዋል አማራ ናቸው፡፡ ተገድደው ያልፈለጉትን ማንነት እንዲይዙ ሊያደርግ የሚችል ሀገራዊም ሆነ አለምአቀፋዊ የሕግ መሠረት የለም፡፡ ምንአልባት አከራካሪ ሊሆን የሚችለው እነዚህ ሕዝቦች የሰፈሩበት አካባቢ ብቻ ነው፡፡
ይህም ቢሆን ሕዝቦቹ አማራ መሆናቸውን ማሣወቃቸው ብቻ በቂ ሆኖ ሊስተዳደሩበት የሚችለውን ክልል በተመለከተ ቀድሞውኑም የአማራ ሕዝቦች ክልል ተብሎ የተመሠረተ ኩታ ገጠም ክልላዊ መንግሥት ስላለ ከላይ የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ 47 እና 48 እንደገለፅኩት አዲስ ክልል መመሠረት ስለማያስፈልጋቸው በሌላ በኩልም የማንነት ጥያቄ ያነሱት ሕዝቦች የሠፈሩበት ቦታ በታሪካዊ አመጣጥም ሆነ በጅኦግራፊያዊ አቀማመጡ ከአማራ ክልል ጋር የተያያዘ በመሆኑ ሕዝቦቹ በየትኛው ክልል ሥር መሆን እንደሚችሉ የሚያስቸግር ሕገመንግሥታዊ ወይም ፖለቲካዊ ሁኔታ የለም፡፡
በመጨረሻም በአጭሩ በድጋሜ ሊሰመርበት የሚገባው የወልቃይት ሕዝብ ጥያቄ አዲስ ማንነት እንዲሰጣቸው ሣይሆን የነበረውን ማንነታቸው ስለተነጠቁ የተወሰደ ማንነታቸው እንዲመለስላቸው ብቻ ነው፡፡ በመሆኑም የዋልቃይት፣ ጠገዴ፣ ሁመራ እና ጠለምት ሕዝብ የተነጠቀ ማንነት የማስመለስ ጥያቄ መፍትሔ ሊያገኝ የሚችለው አንድም በአስተዳደራዊ ዳኝነት ነው። ይህ ካልሆነም በፍርድ ቤት በሚሰጥ ውሣኔ ነው፡፡ ምንአልባት ሰዎች ይህ ጉዳይ እንዴት በፍርድ ቤት ሊታይ ይችላል የሚሉ ይኖራሉ፡፡ የሰው ልጅ የግል መብት ከሚባሉት አንዱና ዋናው የማንነት መብት ነው፡፡ የሰው ልጅ ንብረቱ ሲወሰድ ለማስመለስ ፍርድ ቤት ፊት ይቆማል፡፡ ከንብረት በላይ የሆነው የማንነት መብቱ ሲወሰድ በፍርድ ለማስመለስ አይጠይቁም ብሎ መከራከር ግን የሚቻል አይመስለኝም፡፡ ይልቁንም እስከአሁን ወደማይመለከተው የፌዴሬሽን ምክር ቤት እና ለትግራይ ክልላዊ መንግሥት አቤቱታ ለማቅረብ ያባከኑት ጊዜ ኮሚቴዎቹን ዝም ለማሰኘት ለእሥራት ካበቃቸው ምክንያቶች አንዱ እንደሆነ መገመት ይቻላል፡፡
(አቶ አለልኝ ምህረቱ የኮ/ል ደመቀን ጨምሮ ለወልቃይት አማራ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ አባላት እንዲሁም ለበርካታ  በወልቃይት ጥያቄ ለተከሰሱት ጥብቅና የቆሙ የሕግ ባለሙያ ናቸው። ፅሁፉ በፎቶው ከሚታየው መፅሐፋቸው የተወሰደ ነው)
Filed in: Amharic