>

ለዶ/ር አብይ መቅረብ ካለባቸው ጥያቄዎች መካከል ጥቂቶቹ (ጌታቸው ሺፈራው)

ዶ/ር አብይ አህመድ ለአማራ ወጣቶች:_ “ጅጅጋ፣ አምቦና መቀሌ ሰከላተም ሰንብቼ ስለደከመኝ  ከመጣችሁ አዲስ አበባ ኑ እና እንደተቃዋሚ ፓርቲዎች እራት ግብዣ አደርጋለሁ።  ከፈለጋችሁ ኑ! እኔ እንግዲህ ጠርቻለሁ” አይነት መልዕከት አስተላለፈ መሰለኝ። በዋና ዋና የአማራ ክልል ከተሞች ወጣቶች በጣት እየተጠቁሙ ወደ አዲስ አበባ ሊሆዱ እንደሆነ ሰምቻለሁ። ምን አልባትም በሌሎች ክልሎችም ለራት ግብዣ ተጋብዘው ይሆናል!
እንደ እኔ ወጣቶቹ አብይን መጠየቅ አለባቸው። ቢመልስም ባይመልስም! ቢያንስ!
~በዘሩ ተለይቶ ሲጠቃ የቆየ ሕዝብ እንደሆነ ለአብይ በደንብ መንገር አለባቸው። ስለማያውቀው ሳይሆን፣   በደርግ ዘመን የደረሰ ጉዳትን ክብር ሲሰጠው በአሁኑ ወቅት እየተገፀመ ያለ የዘር ጥቃት መታወቅ አለበት። በዘሩ ምክንያት የተጠቃ መሆኑ በግልፅ ተነግሮ፣ ይቅርታ ተጠይቆ፣ ካሳ ተከፍሎት፣ ያጠቁት ተጠይቀው፣ የተፈናቀለው ወደቀየው እንዲመለስ መጠየቅ አለባቸው።
~የአማራ ሕዝብ በዘሩ ለመጠቃቱ የተገደሉትን አፅም መቆፈር ደረስ መሄድ አያስፈልግም። ማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ “አማራን እናመክነዋለን” እየተባሉ የተኮላሹትን  እና ማዕከላዊ ተዘጋ ከተባለም በኋላ በእስር ላይ የሚገኙትን አበበ ካሴን፣ አስቻለው ደሴን፣ ዮናስ ጋሻውን፣ ፈረደ ክንድሻቶ  እና  በርካቶችን መጥቀስ ይቻላል።  አብዛኛዎቹ በመኮላሸታቸው ምክንያት ወደ ፍርድ ቤት እያነከሱ ሲመጡ የተነሱትን ፎቶ ማስደገፍ ይቻላል።ለአብይም  ሊነገረው ይገባል!
~እነ አብይ ስለ ኢትዮጵያ፣ የቀደሙት ስላደረጉት መልካም ነገር እያወሩ ነው።  “ኢትዮጵያ!” ስላለ “ነፍጠኛ፣ ቅኝ ገዥ ” እየተባለ በገዥዎቹ በጠላትነት የተፈረጀው ሕዝብ የደረሰበትን በደል በግልፅ መነገር አለበት።  “የሚጠላችሁ ይጥፋ” መባል ካለበት ለሁሉም ኢትዮጵያዊ  ነው። የአማራውን ሕዝብ ከጫካ ጀምሮ በጠላትነት ፈርጆ የመጣው ትህነግ/ህወሓት ነው።  ይህ የጥላቻ ማንፌስቶም በብዙዎች እጅ አለ። ገዥዎቹ ባለፉት አመታት፣ በቅርቡም እነ አብይ በሚዲያ እንዳጋለጡት የአማራን ሕዝብ ከሌላው ሕዝብ ጋር ሲያጋጩት፣ በእነ ሽፈራው ሽጉጤ ደብዳቤ ሲያስገድሉትና ሲያፈናቅሉት ኖረዋል። ይህ በግልፅ መታመን አለበት።  የፌደራል ዐቃቤ ሕግ በጋምቤላ እና ደቡብ በአማራው ላይ በመንግስት ባለስልጣናት ትዕዛዝ የተፈፀመ የዘር ማፅዳት እንደተደረገ አምኗል። ከአራት በላይ መዝገቦችን በዋቢነት ማቅረብ ይቻላል። አንደኛው መዝገብ ላይ የዘር ማፅዳቱ በክልሉ የፖሊስ አዛዥ  ትዕዛዝ የተፈፀመ መሆኑን አቃቤ ሕግም አምኗል። ይህ የመንግስት ሰነድ ነው። አብይ የሚያስቀጥለው መንግስት የፈፀመውን የዘር ማፅዳት ክፉ ታሪክ ማፅዳት ካለበት ይህ ግፍ በመሪዎች አፍ መነገር አለበት። ይህ ክፉ ታሪክ የሚፀዳው  በደሉ በግልፅ በሚዲያ ተለፍፎ ነው።  ትዕዛዝ የሰጡት የመንግስት አካላት ተጠይቀው ነው። የተበደሉት ተክሰው ነው። እነ አብይ እውነት ስለ ኢትዮጵያ የሚናገሩ ከሆነ፣ ሱሳቸው ከሆነ “ኢትዮጵያ” በማለቱ ስለተገደለው ሕዝብ በመንግስት ደረጃ ይፋ መደረግ ያለባቸው ሀቆች ይፋ መደረግ አለባቸው።  በፕሮግራም ደረጃ ሕዝብን ጠላት አድርጎ የመጣ ቡድን፣ አሁንም ያን አላማውን እያስፈፀመ እነ አብይም (የአማራና ኦሮሞን እያጋጨ) የያዙትን ቡድን ገመና መነገር አለበት። ይቅርታ መጠየቅ፣ መወቀስ፣ መወገዝ፣ በሕግ መቀጣት አለበት።
~በፕሮግራም ደረጃ አማራውን ጠላት ያደረጉት አካላት በኢኮኖሚ አድቅቀውታል። እነሱ ስልጣን ከመያዛቸው በፊት የነበረውን እንኳን አበላሽተውታል። ወይንም ወስደውታል። በአሁኑ ዘመን አማራው የሚማረው በዳስ ነው።  አብይ የጠራቸው ወጣቶች ትህነግ ከደርግ ጋር የጦር ሜዳ ያደረገውን የዋግህምራ ጨምሮ በመላው አማራ ክልል ህፃናት ዝናብ እና ፀሀይ እየተፈራረቀባቸው የሚቀመጡባቸውን ዳስ ትምህርት ቤት ፎቶዎች ለአብይ ማሳየት አለባቸው።  ከትምህርት ተቋማት በተጨማሪ የጤና ተቋማቱን ድቀት፣ በቃሬዛ  ተገቢውን የማዋለድ አገልግሎት ወደማያገኙባቸው የፈራረሱ ጤና ጣቢያዎች የሚሄዱትን እናቶች ፎቶ በማስደገፍ መጠየቅ አለባቸው። በዚህ ዘመን በትውልዱ ላይ ከዘር ማጥፋት ባሻገር አደንቁሮ መግዛት በፖሊሲ ደረጃ መያዙን ማስረዳት አለባቸው። አስፓልቱ ላያቸው ላይ የተነሳውን መንገዶች፣ የመሰረት ደንጋይ ተጥሎባቸው መና የቀሩትን ከ200 በላይ ፕሮጀክቶች ዝርዝር መረጃ ይዘው መሄድ አለባቸው። ይህ የሚደረገው ሆን ተብሎ ሕዝብም ለማድቀቅ መሆኑን መናገር አለባቸው።  ከህዝብ የተዘረፈ ሀብትና ቅርስ  ለሕዝብ እንዲመለስ መጠየቅ አለባቸው።  ገዥዎች በፖሊሲ ደረጃ ያደረጉት ይህ አደህይቶ መግዛት ለሕዝብ ግልፅ መሆን እንዳለበት መጠየቅ አለባቸው።
~አሁን የተጠሩት አማራ ወጣቶች መሆናቸውን ነው የሰማሁት።  ምን አልባት ሌሎች ወጣቶችም ከተጋበዙ ከአማራው ተመሳሳይ ጥያቄ ማንሳት ይገባቸዋል። የአማራና ጉራጌ ወጣቶች “ግንቦት 7″፣ የኦሮሞ ወጣቶች “ኦነግ” በሚል ፍርጃ ስቃያቸውን አይተዋል። ማዕከላዊ “አንተ አማራ፣ አንተ ኦሮሞ፣አንተ ጉራጌ” እየተባሉ በሕዝብ ስም ተዘልፈዋል፣ ተገርፈዋል። እነ አብይ ማዕከላዊን ዘጋን ሲሉ አስከፊ ታሪኩም በዚሁ መዘጋት አለበት። ማዕከላዊ ወጣቶች ሲገረፉ የነበሩት በሕዝብ ስም ነው፣ የተገረፈው ሕዝብ ነው፣ የተሰደበው ሕዝብ ነው! ባለፉት 27 አመታት ማዕከላዊ ስለተፈፀመው ሁሉ ሕዝብ ይቅርታ ሊጠየቅ ይገባል! በይፋ! ይህን ወጣቶቹ ለአብይ ማቅረብ አለባቸው።
~ትህነግ/ህወሓት የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ለመቆጣጠር በነደፈው የተስፋፊ እቅዱ  የጉራጌ ተወላጆች  በስልታዊ መንገድ፣ ከ1997 በኋላ ደግሞ በይፋ ከንግድ ተፈናቅለዋል። ይህ ተጠንቶ  የተፈናቀሉት ወደቦታቸው ተመልሰው፣ ስልጣንን ተገን አድርገው ታታሪ ነጋዴዎችን የነቀሉት ለህግ መቅረብ አለባቸው።
~አዲስ አበባ ዙሪያ ያሉ የኦሮሚያያሉ እንዲሁም ሌሎች ክፍሎች በኢንቨስትመንት ስም ከገበሬው ተነጥቆ ለካድሬ፣ ለዘመነኛ ገዥዎች የተሰጠ መሬት በሙሉ ተጠንቶ መመለስ አለበት፣ ተጎጅዎቹ ተክሰው፣ ሙሰኞቹ ለህግ መቅረብ አለባቸው!
~አንዴ ሀገር ለመገንጠል፣ ሌላ ጊዜ ሕገ መንግስቱን በሀይል ለመናድ፣ አሁን ደግሞ “አሸባሪ” እየተባሉ የታሰሩት በሙሉ መፈታት አለባቸው። በእስር ወቅት ለደረሰው ሰቆቃ፣ ታፍነው ደብዛቸው ለጠፋው ዜጎች ገለልተኛ ኮምሽን ተቋቁሞ ምርመራ ማድረግ አለበት።
~የማንነት ጥያቄ ስላነሱ የሚታሰሩት፣ የተገደሉት፣ የተፈናቀሉት ጉዳይ በዝርዝር መቅረብ አለበት!
~ከላይ የተዘረዘሩትን በጣም ጥቂት ጥያቄዎች አብይ ሊያውቃቸው ይችላል። ግን  ሊነገረው ይገባል። ህዝብ እነዚህ ጥያቄዎች ካልተመለሱለት ጥያቄ እንዳልተመለሰለት፣ በቀጣይም እንደሚጠይቅ ማወቅ አለበት። ካላወቀው ማወቅ አለበት። ቢያንስ በሚናገረው መጠን መፈተን አለበት። እሱ ባለበት ጊዜ የተፈፀሙ፣ እየተፈለሙ ያሉ ስለሆነ ሕዝብ እንዳወቀ መገንዘብ አለበት፣ (አቅም  አይኖረውም እንጅ) ካወቀም መፍታት ግዴታው መሆኑን፣ ወደፊትም የሚገጥመውን ፈተና ማወቅ አለበት። ይህን ሁሉ የፈፀመ ድርጅት መሪ ተንብሏልና ማፈር አለበት፣ እንደ መሪ ይቅርታ  መጠየቅ አለበት። ባያደርገው እንኳ መጠየቅ አለበት። መልሱን እንሰማለን! አካሄዱን እናያለን!
#”ኢትዮጵያ!ኢትዮጵያ” እየሉ በዚህ አቋሙ ስለተበደለ ሕዝብ ዝም ማለት ቃልአባይነት ይሆናል
“አንዱ የሌላውን እየቀማ የሚባለበት ሀገር አይኖረምንም” እየተባለ የቀሙት የተቀማውን ሀብት፣ የተቀሙት ድህነትን ተሸክመው እንዲቀጥሉ መፍቀድ የቀማኞች ጠበቃ፣ ከዛም ሲያልፍ ቀማኝነት ነው!
~”መጠየቅ መብት ነው”! እየተባለ የማንነት ጥያቄ ያነሱት ሲሳደዱ፣ ከቀያቸው ሲፈናቀሉ፣ ሲገደሉ ዝም  ማለት እስካሁን የተባለው “ጉራ ብቻ” ያደርገዋል!
Filed in: Amharic