>
5:13 pm - Tuesday April 19, 0489

የዶ/ር አብይ አህመድ ፈተናና የህወኃት አሸናፊ ሆኖ ዳግም መውጣት (የኪዳን ሰው)

“አገሬ ኢትዮጵያ ሞኝ ነሽ ተላላ ፣ የሞተልሽ ቀርቶ የገደለሽ በላ” ሲባል በፊት ብዙም ስሜት አይሰጠኝም ነበር። ምክንያቱም ማን እንደሞተላት፣ ማን ደግሞ እየገደላት እንጀራዋን እንደሚበላ በልጅነት ዘመኔ ብዙም የሚያሳስበኝ ጥያቄ ስላልነበረ እንዲሁ ቃሉን ከመስማት ባለፈ ለምን ብዬ መጠየቅ የጀመርኩት እድሜዬ እየጨመረ፣ መረዳቴ እያደገ፣ እውቀቴም እየሰፋ ከሄደ በኋላ ነበር። የታሪክ ድርሳናትን ስንመረምር፣ የአባቶቻችን የትናንት አርበኝነት፣ አገር ወዳድነትና ዓለምን ያስደመመ የዓድዋ ድል ታሪክ ስንፈትሽ ኢትዮጵያ አገራችን የጀግኖች እናት መሆኗን ከማዎቅም በላይ እነዚያ ጀግና ጥቁር ህዝቦች የሰሩት አኩሪ ታሪክ ዛሬ ያለውን ብቻ ሳይሆን መጪውን ትውልድም የሚያኮራ ጀግንነት መሆኑን አይተናል።
ነገር ግን አገራችን ኢትዮጵያ የጀግኖች መፍለቂያ ብቻ ሳትሆን የከሃዲዎችም መወለጃ አገር እንደሆነች የትናንቱና የዛሬው ታሪካችን ህያው ምስክሮች ናቸው። አዲሱ ጠቅላይ ሚንስትር በወርቃማ ቃላት ያሽሞነሞኑት የትግራይ ህዝብ በሙሉ በእውነት እንደተባለው ነውን? አፄ ቴዎድሮስን የእንግሊዝን ጦር መርቶ በማስገባት በጠላትነት ያስገደሉት የአፄ ዮሐንስ የአገር ክህደት ወንጀል ጀግንነት ተደርጎ ተወድሶ ይሆን? በአድዋው ጦርነት ወቅት ከምንሊክ ጋር የዘመቱት ስዊድናዊ ዜጋ “የሐበሻ ጀብዱ” በሚለው መጽሐፋቸው ላይ የትግራይ መኳንንቶችንና ገበሬዎችን የክህደት ስራ በሰፊው ዘርዝረውታል። በዶ/ር አብይ የተዘመረው የትግራይ የኢትዮጵያዊነት ከፍታ ወዴት ይሆን ጎበዝ? ዛሬም የህወኃት የአገር ክህደት ወንጅል፣ ትውልድን የመጨፍጨፍና አፈና እንደ ጀግንነት ተደርጎ መወደስ የአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር የፓለቲካ ኪሳራ ከመሆኑም በላይ “ትሻልን ሰድጄ ትብስን አመጣሁ” እንደተባለው ሆኖ እያየነው ነው። የህወኃታዊያን ደቀ መዛሙርት ዋናውና ትልቁ መለያቸው ሁሌም አድር ባይነት፣ ሆድ አደርነትና የትግራይን ታላቅነት አምላኪነት ነው። አዲሱ ተጠቅላይ ሚኒስትርም በተግባር ያሳዩንና ያረጋገጡልን እውነትም ይህን ነው።
ወደ ዋናው አጀንዳዬ ስመለስ አዲሱ ጠቅላይ ሚንስትር ተፈትነው የወደቁባቸውንና ተጠቅላይ ሚንስትር መሆናቸውን በመቀሌው ስብሰባ ያረጋገጡልንን እውነታዎች እንደሚከተለው አብራራለሁ።
1•የወያኔ ጥያቄ  ዶ/ር አብይ አህመድ የህወኃት እውነተኛ ልጅ ከሆንህ የፀረ ሰላም ኃይሎች እኛን ነፍሰ ገዳይ፣ አምባገነን፣ ከሃዲና ፀረ ኢትዮጵያ ናችሁ የሚሉትን አሉቧልታ ገልብጠህ በማንበብ የትግራይን ጀግንነት፣ ታላቅነት፣ አሸናፊነትና ቀዳማይ ኢትዮጵያዊነት አወድስ የተባለውን በመፈፀም ኢትዮጵያዊያን ካስቀመጡት ከፍታ በፀሐይ ፍጥነት ወርዶ ደደቢት በረሃ ላይ ተጋዳላይ ሆኖ ሲዋጋ ታይቷል።
2• ህወኃቶች ስለ አንተ ይጠነቀቁልሃል፣ እግርህም በድንጋይ ከቶ እንዳይሰናከል በእጃቸው ደግፈው ይይዙሃል፣ ስለዚህ አንተ በእኛ ቋንቋ ታላቅነታችንን አወድስ፣ኢትዮጵያዊነታችንም መስክር፣ ጀግንነታችን ተርክ፣ ያለ እኛ ኢትዮጵያ እንዳልተፈጠረችና እንዳልኖረችም ተናገር ተባለ፣ እሱም አሳምሮ ውዳሴ ወያኔነትን ተረከልን፣ ለህወኃት ያለውን ታማኝነትም በደማቅ  ብዕር ፃፈልን።
3• ህወኃትም እንደገና አብይ አህመድን ወያኔነትን (አምባገነናዊ ተመላኪነትን) አትፈታተነው፣ ታዘዘው፣ ፈቃዱንም ፈፅምለት አለው። ሁለተኛው ተጠቅላይ ሚንስትርም ጎንበስ ብሎ የጌቶቹን እጅ በመንሳት የወያኔ ደቀመዝሙርነቱንና ሎሌነቱን በፋይ በቃል ኪዳን አፀና፣ በፊርማውም አረጋገጠ።
4• ህወኃትም ዶ/ር አብይ አህመድን ከፍ ወዳለው የክብር ስልጣን እንዴት እንዳወጣው ነገረው፣ ከሁሉ በላይም መሆኑን አሳየው፣ በመጨረሻም እንዲህ አለው:-   ወድቀህ ብትሰግድልን፣ ይህ አሁን እያየኸው ያለ ደስታና ጌትነት በህይወት ዘመንህ አይወሰድብህም፣ ወደ ቀኝም ወደ ግራም እንዳትል። ከዚህ በተቃራኒው ለመጓዝ በፈለግህ ጊዜ ግን በዘመዶችህ ላይ የዘነበውን የጥይት በረዶ፣ እስር፣ ስቃይና ሞት ነጋሪ አያስፈልግህም፣ ታውቀዋለህና። ዶ/ር አብይ አህመድም በሰማዕቱ መለስ ዜናዊ አፅምና ነፍስ እየማለና እየተገዘተ እንዲህ አለ። ጌቶቼ ሆይ ቃላችሁ ቃሌ ነው፣ ኪዳናችሁ ኪዳኔ ነው፣ ራዕያችሁ ራዕዬ ነው፣ ህልማችሁም ህልሜ ነው፣ በዚህ ሁሉ በጎነታችሁና ለእኔ ባደረጋችሁት ቸርነትና መልካምነት ፈቃዳችሁን አለመፈፀም እንዴት ይቻለኛል? በቀሪው ዘመኔ የእናንተን ቃል ባልፈፅም የመለስ አጥንት ይውጋኝ፣ ራዕዩንም ባላስቀጥል ነፍሱ በቀንና በሌሊት ታሳደኝ። ይህን ቃል ኪዳን በመፈፀም ላይ መሆኔ ደግሞ የሰሞኑ እንቅስቃሴዬ በቂ ምስክር ነውአላቸው።
በአጠቃላይ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በዚህ ወጣት የተስፋ ቃል ነፍሱ ያልተነቃቃ አልነበረም። ነገር ግን ለህዝብ የገባውን ተስፋ፣ የለውጥ ጉዞና የነፃነት ናፍቆት ወር ባልሞላ የስልጣን ዘመኑ በወያኔ ደመና ሸፈነው፣ በትግራይ ታላቅነትና ኃያልነት ነጎድጓድ ቀየረው፣ ይህም ታላቅ ክህደት ከመሆኑም በላይ እንደ መሪ ረጅም ሳይጓዝ በአጭሩ መሸነፉን ሲያሳይ የወያኔን በጨዎታው አሸናፊነት ግን በደማቁ ፅፎታል።
Filed in: Amharic