>
5:14 pm - Wednesday April 20, 2985

የአባ ታጠቅ አስከሬን ላይ የተፈጸመ ግፍ፤ (ውብሸት ሙላት)

የዛሬ 150 ዓመት ወደ ኋላ ስንጓዝ ‘ኢትዮጵያ ባሏን ኢየሩሳሌም እጮኛዋን’ በመቅደላ አምባ ላይ አጥታለች፡፡ የመይሳው ልጅ በኩራት እና በክብር ሽጉጣቸውን በአፋቸው ጎርሰው ራሳቸውን አጠፉ፡፡ እንግሊዞቹ ፍላጎታቸው ማርኮ መውሰድ ነበርና ይህን የተረዱት ንጉሥ ከሞታቸው ከሁለት ቀናት በፊት “ወንድ ያቀፈን ወንድ አያቅፈውም” ብለው እንዳሳወቁት ራሳቸውን አጠፉ፡፡ ሞተውም ክብርና ኩራታቸው ከንፈራቸው ሁሉ ፈገግታን አልተለየውም፡፡
“ጥይት ስለውሃ ማነው የሚጠጣ
ቴዎድሮስ ብቻ ነው ጥሙን የሚወጣ ፤”ተባለ፡፡
አሳዛኙ ታሪክ የመጣው ከሞቱ በኋላ ነው፡፡ የእንግሊዝ  ወታደሮቹ የመይሳውን ሹርባ ላጩት፡፡ ብዙ ጊዜ በሦስት ጉንጉን የሚሠራውን እና አንገታቸው ላይ የሚጎዘጎዘውን ሹርባቸውን ተቀራመቱት፡፡ ይህ ጸጉራቸው አሁንም እንግሊዝ ይገኛል፡፡
የመይሳው ልጅ ብዙ ጊዜ ከላይ ይለብሱት የነበረው የእንግሊዝ ትሸርት/ሸሚዛቸው ሲሆን ሱሪያቸው ግን ኢትዮጵያዊ ስሪት ነው፡፡ ጫማ አያደርጉም፣ባዶ እግራቸውን ነው የሚሔዱት፡፡ ለእዚያውም እጅግ ፈጣን እና ተከታዮቻቸውን አብረዋቸው ለመጓዝ እስኪደክማቸው ድረስ የሚፈጥኑ፡፡
እንደሞቱ ሸሚዛቸውን፣ በደም የተበከለውን፣ የመይሳውን ልጅ ሸሚዝ “ለእኔ ይገባኛል ለእኔ ይገባኛል” በማለት ሲጓተቱት እንደነበር አሜሪካዊው ሪርተር የዐይን ምስክርነቱን ጽፏል፡፡ ባዶ እርቃናቸውን እሲኪቀሩ ድረስ ልብሳቸውን ገፈፏቸው፡፡ ይህ ደም በደም የሆነው ሸሚዛቸውም እንደሹርባቸው ሁሉ የሚገኘው እንግሊዝ ነው፡፡
የአባ ታጠቅ ከፊል ራቁት አስከሬን  ቃሬዛው ላይ ሰው እንዲያየው ተዘረረ፡፡ ሪቻርድ ሆምስ ወዲያውኑ ሳለው፡፡ ከዚያ ናፒር አስከሬኑን ልብስ እንዲለብስ አስደርጎ እስረኛ ከነበረው ከራሳም ጎጆ  ገባ፡፡ ዶ/ር ሔንሪ ብላንክም የንጉሡ የንስሃ አባት በተገኙበት አስከሬኑን ምርመራ አደረገ፡፡ ጥይቷ በአፋቸው ገብታ በጀርባው ባለው የጭንቅላታቸው ክፍል መውጣቷን  አረጋገጡ፡፡
አስከሬናቸው ለቀብር ሲዘጋጅ ግን በነጭ ጨርቅ ተጠቅልሎ፣በወርቀዘቦ ባሸበረቀ የሀገር ባህል ልብስ አልጋው ተጠቅልሎ በማግስቱ በ7/8/1860 ዓ.ም. ራሳው ባሠሩት መቅደላ መድኃኔ ዓለም ተቀበሩ፡፡
ከላይ እንደጠቀስነው እንግሊዞቹ ዋና ፍላጎታቸው መማረክ ቢሆንም ራሳቸውን በመግደላቸው ይህ ግጥም ቀረበ፡፡
“ገደልንም እንዳይሉ ሙተው አገኟቸው፤
ማረክንም እንዳይሉ ሰው የለ በጃቸው፤
ምን አሉ እንግሊዞች ሲገቡ አገራቸው፤
ለወሬ አይመቹም ተንለኛ ናቸው፡፡” ተባለ፡፡
የመይሳው ልጅ፣ አንድ ለእናቱ ግን ኢትዮጵያን አንድ አድረጎ ሞተ፡፡
“አባትና እናቱ አላንድ አልወለዱ፤
አባ ታጠቅ ካሳ ያው አንዱ ያው አንዱ
(ያ ወንዱ ያ ወንዱ)”
የአንድ ለእናቱን፣ የመይሳውን ልጅ፣ አባ ታጠቅ ካሳን፣ ዳግማዊ ቴዎድሮስን ፈጠሪ ለነፍሱ እረፍት ይስጣት፣ሳይዋቀስ ዘላለማዊ ሰላምን ይስጠው፡፡
ምንጮቻችን፡-
Henry Stanley, Commassie and Magdala
Rassam, narratives of the British Mission to Theodore
Blanc, A Narrative of Cativity in Abyssinia
ተክለጻድቅ መኩሪያ፣አጼ ቴዎድሮስና የኢትዮጵያ አንድነት
Filed in: Amharic