>
5:13 pm - Tuesday April 18, 9009

ህወሃትማ ገና አላበቃለትም! (ፋሲል የኔአለም)

ህወሃት ገና አላበቃለትም። እንዲያበቃለትን ግን ማድረግ ይቻላል። ፈላስፋው ፕሌቶ 4 ዓይነት የመንግስት አይነቶች አሉ ይላል። አንደኛው የአንድ ሰው ፈላጭ ቆራጭ መንግስት ነው( tyranny):: ሁለተኛው ዲሞክራሲያዊ መንግስት ነው። ሶስተኛው የወታደሮች  መንግስት ነው (Timocracy)። አራተኛው ደግሞ የቱጃሮች መንግስት ነው (Oligarchy):: በኢትዮጵያ ከመለስ ዜናዊ  በሁዋላ የአንድ ሰው ፈላጭ ቆራጭ (tyranny) አገዛዝ አብቅቷል። ሁለተኛው የመንግስት አይነት የሆነው ዲሞክራሲያዊ ስርዓትም ተፈጥሮ አያውቅም። ከመለስ በሁዋላ ያለው ስርዓት ሶስተኛውና አራተኛው ተቀይጠው የመሰረቱት ስርዓት ነው ማለት ይቻላል።  ወታደራዊ አዛዦች ኢኮኖሚውን ተቆጣጥረው ከያዙት  ሰዎች ጋር ጋብቻ ፈጥረው አገሪቱን በጋራ እየዘረፉ እየገዟት ነው። በመከላከያው ( ደህንነቱ) እና በኢኮኖሚው ላይ መሰረታዊ ለውጥ ካልተደረገ በስተቀር ስርየት የለም። መከላከያው (ደህንነቱ) እንደገና መዋቀር አለበት። ኢትዮጵያዊ ቀለም የለውም።
 የአኮኖሚ ስርዓቱም እንዲሁ ነው። ኢፈርትና ሜቴክ የሚባሉ ተቋማት ሳይፈርሱ እውነተኛ ለውጥ አይታሰብም።። የኢፈርት ሃብት ለመንግስት ሊውል ይገባዋል። ኢፈርትን ሳታፈርስ ፍትሃዊ የኢኮኖሚ ስርዓትና በክልሎች መካከል ተመጣጣኝ እድገት ልታመጣ አትችልም። ኢፈርትን ሳታፈርስ የትግራይ የበላይነት የለም ብለህ ብትከራከር የሚሰማህ አይኖርም፤ ኢፈርት የትግራይን ህዝብ ጠቀመ አልጠቀመ ሌላ ክርክር ነው፤ ኢፈርት ግን የሃብት ልዩነት  አንዱ ማሳያ ሆኗል። ከኢፈርት በተጨማሪ ሜቴክም ሊፈርስ ይገባዋል። እነዚህ ሁለት ተቋማት ለአገራችን እድገት የማይጠቅሙ ብቻ ሳይሆን እርስ በርስ የሚያጋድሉ ተቋማት ናቸው። የህወሃት የስልጣን የማስጠበቂያ ተቋማትም ናቸው። እነዚህ ተቋማት እስካሉ ድረስ ኢትዮጵያውያን በኢኮኖሚው ውስጥ ነጻ ተሳትፎ ማድረግ አይችሉም።   በጥንቱ አውሮፓ እንደነበረው የጊልድ (guild) ስርዓት ዜጎች በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ በነጻነት ተሳትፎ እንዳያደርጉ አግደው የያዙ የዝርፊያና ስልጣን የማስጠበቂያ ተቋማት ናቸው ። እነዚህ ሁለት ተቋማት ሳይፈርሱ ዲሞክራሲና ነጻ ምርጫ የሚታሰብ አይሆንም። የትግራይ ህዝብ በእነዚህ ተቋማት እንዳልተጠቀመ ብዙ የትግራይ አክቲቪስቶች ሲናገሩ ይሰማል፤ በጣም ጥሩ፤ ኢፈርት የትግራይን ህዝብ የማይጠቅም ከሆነ “ኢፈርት ፈርሶ ሃብቱም ለመንግስት ካዝና ይዋል” የሚለውን ሃሳብ እንደማይቃወሙት ተስፋ አደርጋለሁ፤ አለመቃወም ብቻ ሳይሆን ከእኔና መሰሎቼ ጋር አብረው “ይፍረስ” እንደሚሉም አምናለሁ።
እውነተኛ ለውጥ የሚመጣው መከላከያ ( ደህንነት) ኢትዮጵያዊ ቀለም እንዲኖረው ተደርጎ እንደገና ሲዋቀርና ኢፈርትና ሜቴክ ሲፈርሱ ነው።  ሜቴክ “የመንግስት” መሆኑ አልጠፋኝም። በመንግስት ስም የሚያገለግለው ማንን እንደሆነ ሁሉም የሚያውቀው ነው።
Filed in: Amharic