>

ጠ/ምኒስትሩ በህወሀታውያኑ ላይ እንደ ቀትር መብረቅ የሚያስደነግጡ ውሳኔዎችን ማሳለፍ ይጠበቅበታል!!! (ቬሮኒካ መላኩ)

እኔ እንደሚመስለኝ አብይ አህመድ አሁን ማድረግ ያለበት በቦይንግ ዲሪምላይነር አይሮፕላን ከአንዱ ክልል ወደ ሌላው እየተሽከረከር ዲስኩር ማሰማት ሳይሆን ቤተመንግስቱን ቀርቅሮ ዘግቶ የሀይለማሪያምን አሮጌ ካቢኔ አፍርሶ የራሱን አዲሱን ካቢኔውን ማዋቀር ነው። ይሄ ደሞ ህገ መንግስቱ የሰጠው የመጀመሪያው በጣም ቀላሉ መብት ነው።  በተጨማሪም እንደ አንድ ስልጣኑን የሚጠቀም ጠቅላይ ሚኒስቴርም እንደ ቀትር መብረቅ የሚያስደነግጣቸውና ሰርፕራይዝ የሚያደርግ ውሳኔ ወስዶም ሊያሳይ ይገባዋል ።
በሀይለማሪያም ካቢኔ ለውጥ አመጣለሁ ብሎ የሚያሳብ ከሆነ የሀይለማሪያምን ጫማ ከነካልሲው የደነቀረ ከሀይለማሪያም የባሰ አሻንጉሊት ሆኖ ነው የሚቀረው። አሁን እንደምንሰማው ሴረኞቹ መቀሌን ፣ አምቦን ፣ እና ሌሎችን  ክልሎች እየዞረ እንድናገር ፕሮግራም አበጅተውለታል። የእነሱ አላማ አብይን ከክልል ክልል እየዞረ ህዝብ በተሰበሰበበት የሚጮህ  ድስኩረኛ ሊያደርጉት ነው።  እሱ ሰው በተሰበሰበበት እየዞረ እንደ ድዮጋን ሶጮህ እነሱ ቤተመንግስቱን ዘግተው ከነበረው አንፃራዊ የፖለቲካ መሰረት ከሆነው ህዝብ እየነጠሉት ነው።
በሌላ በኩል አቢይ አህመድን ገና 1 ወር እንኳን ሳይሞላው ሱሪ በአንገት አውጣ እያሉ መወጠሩ ተገቢ አይመስለኝም። እያስተዳደረ  ያለው አጋሮን ሳይሆን  በውስብስብ ችግሮች የተተበተበችውን ታላቅና ጥንታዊ አገር ነው።  አገር ማስተዳደር ከብቶችን ወደ ግጦሽ አሰማርቶ እንደመጠበቅ ቀላል አይደለም። እነእንቶኔ ገና በበአለ ሲመቱ አስደናቂውን ንግግር ካደረገ ጀምሮ እንደጠመዱት ግልፅ ነው ። እነሱ የጠበቁት ስልጣን በያዘ በነገታው በየአንዳንዱ ቄሮ ቤት ውስጥ ወተት በቧምቧ እንድያስገባላቸው ነበር።
አንድ መታወቅ ያለበት ነገር አብይ አህመድ ከውጫዊው ትግል በተጨማሪ የውስጣዊ ትግል ውጤት መሆኑን ነው። ህውሃትን በአፍጢሟ ደፍቶ ዙፋን ላይ እንድወጣ ያስቻለው የኦህዴድና የብአዴነን ጥምረት ትግል ተጨምሮበት እንጅ  ውጫዊ ትግል ብቻ ያመጣው ውጤት አይደለም።ህውሃት ቂሟን ለመወጣት አብይን ከህዝብ ለመነጠል እንደ ዛሬው ያለ ቀሽም ሴራ መጎንጎኗ አይቀርም።  በህውሃት ሴራ ተጠልፎ አብይ አህመድ ላይ ካምፔይን መጀመር ቅሽምና ነው።
Filed in: Amharic