>

ያለሽ መስሎሻል ተበልተሽ አልቀሻል፤ ለመላው የኢትዮጵያ ቤ/ክ ምእመናን ወምእመናት አድባራት ወገዳማት[ከይኄይስ እውነቱ]

ለመላው የኢትዮጵያ ቤ/ክ ምእመናን ወምእመናት

አድባራት ወገዳማት

ግድያ፣ ዝርፊያ፣ ሽብርና ወንጀል ዓይነተኛ መለያው የሆነው የወያኔ ትግሬ አገዛዝ ከዱር እስከ ምንይልክ ቤተመንግሥት እመራበታለሁ በሚለው መክሥተ ደደቢት (መግለጫው) የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያንን ማፍረስ የዓላማዎቹ አንድ ዓምድ አድርጎ ሲንቀሳቀስ ቆይቷል፤ አሁንም ይህንን የጥፋት ተልእኮ ቀጥሎበታል፡፡

በታሪክ እንደሚታወቀው የትግራይ ክፍለሀገር የክርስትና መሠረት ከሆኑት የኢትዮጵያ አካባቢዎች አንዱ ነው፡፡ ሕዝቡም ለረጅም ዘመናት በጠንካራ ክርስትናው እንዲሁም አድባራትና ገዳማትን እስከነ ቅርሳቸው ጠብቆ በማቆየቱ የሚታወቅ፣ በእምነቱ በመጣ ጉዳይ ሕይወቱን ጭምር ለመስጠት ወደ ኋላ የማይል፣ ክርስትናውን በተግባር የሚኖሩ በርካታ ምእመናን ያሉበት፣  የበርካታ ቅዱሳኖች መፍለቂያና የቅዱሳት መካናት ማዕከል ነው፡፡ ይህ አስተያየት አቅራቢ የዛሬ 25 ዓመት ገደማ ለመንፈሳዊ ዓላማ በትግራይ ከሚገኙ ገዳማት ወደ አንዱ በሄደበት ወቅት መቐለ ከመድረሳችን በፊት ያለች አዲ ጉደም የምትባል ገጠር ቀመስ ከተማ ላይ እረፍት ባደረገ ጊዜ ከተገረመባቸው ጉዳዮች አንዱ በየቦታው የእግዚአብሔር እንግዳን ለመቀበል የተዘጋጁ ቤቶች መኖራቸው ነበር፡፡ እኔ ካረፍኩበት/ከተስተናገድኩበት ቤት  አዛውንት አባት እና ኮረዳ ልጃቸው የእኔን እግር በማጠብ ለሚገኝ በረከት ያደረጉት ሽሚያ መቼም አይረሳኝም፡፡

ዛሬ ከዚህ የተቀደሰ ምድር የበቀሉ ጉዶች/አረሞች፣ የባዕዳን ቅጥረኛ ባንዶች መላ ኢትዮጵያን ረፍት ነስተዋታል፡፡ በተለይም የኢትዮጵያን ታሪክ ስናነሳ ተነጥላ የማትታየውን፣ ለአገራችን በርካታ ውለታዎችን የዋለችውን የኢትዮጵያ ቤ/ክ ለማፍረስ ሌት ተቀን የሚተጉ ሥጋ የለበሱ አጋንንትን (በቤ/ክ ቋንቋ ‹አፍኒንና ፊንሐሶችን›) በአድባራቷና በገዳማቷ በወረራ መልክ በማሠማራት እኩይ ተግባራቸውን –  መሠረተ እምነቷንና ቀኖናዋን ለመበረዝ ብሎም ለማጥፋት መናፍቃንን በመሰግሰግ፣ ከገዳማት ግድግዳ ላይ ሳይቀር ጥንታዊ ቅዱሳት ሥዕላትን እና ውድ መንፈሳቂ ቅርሶች በመዝረፍና በማጥፋት፣ የቤ/ክርስቲያኒቱ የአብነት ትምህርት ከምንጩ እንዲደርቅ ሊቃውንትንና የዘረጓቸውን ጉባኤያት በማጥፋትና ደቀመዛሙርት ተበትነውና ባክነው እንዲቀሩ በማድረግ፣ በቤ/ክ ዙርያ ብቻ የሚገኙ ጥንታዊ ዓፀዶችን እስከነ ብዝኃ ሕይወታቸው በማጥፋት፣  ምእመናን ለምነው ጭምር በመባዕ፣ አሥራት፣ በስእለት ወዘተ. መልክ የሚሰጡትን ገንዘብ፣ ወርቅ፣ ከብት ወዘተ. በጠራራ ፀሐይ በመዝረፍ፣ አሁን በቅርቡ በማስረጃ ተደግፎ እንደቀረበው በመዋዕለ ነዋይ ማፍሰስ ስም በአገዛዙ ሰዎች ለሚቋቋም ዳሎል ተብሎ ለሚሰየም ባንክ ከዝርፊያ የቀረውን የምእመናን ገንዘብ አሳልፎ ለመስጠት ዝግጅት ላይ መሆናቸው ወዘተ. – በመፈጸም ላይ ይገኛሉ፡፡ አፍኒንና ፊንሐስ በዘመነ ብሉይ የነበረ ኤሊ የተባለ ሊቀ ካህናት ልጆች ሲሆኑ፣ ዝርፊያን ጨምሮ አስነዋሪ ተግባራትን በቤተመቅደስ በመፈጸማቸው የተቀሰፉ ‹አገልጋዮች› ነበሩ፡፡

ወያኔ የኢትዮጵያ ቤ/ክርስቲያንን ማፍረስ ኢትዮጵያን የማፍረስ ተልእኮው ዋና ስልት አድርጎ ሲንቀሳቀስ ቆይቷል፡፡ ለመሆኑ ክርስቲያኑ የትግራይ ምእመንን በተለይ፣ ከ40 ሚሊየን በላይ የሚሆነው የኢኦተቤ/ክ ተከታይ ምእመንን ባጠቃላይ ድንዛዜና ፍዘት ውስጥ የከተተው አዚም ምንድን ነው? አሁን እርቃኗን የቀረች ተቋም ይዘን የኢትኦተቤ/ክ አለች ብለን አፋችንን ሞልተን መናገር እንችላለን? ከዚህ ቀደም በተለያዩ አርእስት የኢኦተቤ/ክ ስለገጠማት ፈተና እንዲሁም ጊዜያዊ መፍትሔዎች ለመጠቆም ሞክሬአለሁ፡፡

ዛሬ ቤ/ክ (እግዚአብሔር ባወቀ በገዳማት ከሚገኙና በትህርምት ከሚኖሩ ጥቂት ባሕታውያን፣ መናንያንና ዝጉሐን ወዘተ. በቀር) እውነተኛ አባቶች የሏትም፡፡ ሲኖዶስ በአገር ውስጥም በውጭም የላትም፡፡ ዛሬ ምክንያቱን በግልጽ ባላውቅም ብዙ ተስፋ የተጣለባቸውና በማኅበረ ቅዱሳን ምሥረታና አገልግሎት ውስጥ ታላቅ ድርሻ ያለቸው ወጣትና ጎልማሳ ቀሳውስትና ዲያቆናት ከአገር ሸሽተው ኑሮአቸውን በውጭው ዓለም አድርገዋል፡፡ ማኅበሩ በርካታ ግዙፍ ተግባራትን በሁሉም መስክ ማድረጉና እያደረገ መገኘቱ የማይካድ ቢሆንም (አንዳንድ በግል ጥረት የሚያደርጉ ወንድሞች እንዳሉ ባውቅም) የኢትዮጵያ ቤ/ክ ህልውና ከመቼውም ጊዜ በተለየ ፈተና ላይ በሚገኝበት በዚህ አሳሳቢ ወቅት በከፍተኛ ት/ት ተቋማት፣ በየአድባራቱና ገዳማቱ የሚገኙ የሰንበት ተማሪዎችን አስተባብሮ ከመናፍቃን ብቻ ሳይሆን ከዘራፊዎችና ቀማኞች ቤ/ክርስቲያኒቱን ለመታደግ ምን እያደረገ እንደሆነ ግልጽ አይደለም፡፡ የቤ/ክርስቲያንን ህልውና መታደግ የሁሉም አማኝ የውዴታ ግዴታ መሆኑን ጠንቀቄ አውቃለሁ፡፡ ማኅበሩ ለወያኔ አገዛዝ ህልውና አደገኛ ተብለው በወያኔ ደኅንነት ከተፈረጁትና ዒላማ ተደርገው ክትትል ከሚደረግባቸው ተቋማት መካከል አንዱ መሆኑንም እገነዘባለሁ፡፡ ሆኖም ምእመኑ በተለይም ወጣቶች አስተባባሪ/መሪ ያስፈልጋቸዋል፡፡ ይህንንም ሚና ለመወጣት ሰማዕትነት ጭምር ሊጠይቅ ይችላል፡፡ ሰዎች በፖለቲካ እምነታቸው ዙሪያ ብዙዎችን በማሰባሰብ የሕይወት መሥዋዕትነት የሚከፍሉ ከሆነ ሰማያዊ ዋጋ ሰማያዊ ክብር ለሚያስገኘው የእምነት ጉዳይ ሲሆን ማፈግፈጉን ምን አመጣው? የክርስትና አስተምሕሮ አንዱ መሠረት ባለቤቱ ክርስቶስ እንዳሳየን በሞቱ ሞትን ማሸነፍ ከሆነ፣ በሞት ተዘርቶ በትንሣኤ መነሣት ከሆነ እምቢ ማለትን ማን ከለከለን? ከየአጥቢያ ቤ/ክርስቲያን ጀምሮ አገዛዙ በሐሰት በተሰጠ የቤ/ክ ማዕርግ ያስቀመጣቸውን ሐሳውያን ‹‹አገልጋዮች›› (ካድሬዎች) በዓይነ ቁራኛ ከመከታተል ጀምሮ አጋልጦ ከሕዝበ ክርስቲያኑ ጋር ማስወገድ፣ በየደረጃው የሚገኙ ቅርሶችና ሀብቶችን መጠበቅ እንዴት አቃተን? በቀደመ አስተያየቴ አጽንዖት ሰጥቼ እንዳሳሰብኩት ገንዘባችንን ለዘራፊዎች ሰጥተን (ምንም ጥፋት እንዳልፈጸምን፣ ይልቁንም የፅድቅ ሥራ እንደሠራን ቆጥረን) ወደየቤታችን መግባት እስከ መቼ ይቀጥላል? ሁሉን ለሰጠን እግዚአብሔር መልሰን የምንሰጠው ገንዘብ ላይ ለምን አንጨነቅም? ከመነሻውስ ይህ ‹ክፉ ጊዜ› እስኪያልፍ ከእጦታችን የምንሰጠውን ገንዘብ (ከድቃቂ ሳንቲም ጀምሮ) ለምን አናቋርጥም? ወጣቱም፣ ጎልማሳውም አዛውንቱም ቤ/ክ መለ መላውን ስትቀር እስከ መቼ የበዓል ክርስቲያን በመሆን ‹እልል› እያልንና እያጨበጨብን፣ በጮሌ ካድሬዎች አውቀንም ሆነ በእምነት ስም እየታለልን በዘልማድ እንመላለሳለን? እስከ መቼ በሥጋዊውም ሆነ በመንፈሳዊ ሕይወታችን ድንቁርና ሠልጥኖብን ይኖራል? እስከ መቼ ከእኛ ያነሱ ድውያነ አእምሮዎች (ደናቁርት) አገራችንንና ቤ/ክርስቲያናችንን ሲያጠፉ በአስደንጋጭ ዝምታ እንቀጥላለን? ኧረ ክርስትና በጊዜውም ያለጊዜውም ጸንቶ መገኘት ነው፡፡ ኧረ ክርስትና የነፍስና የሥጋ ባለቤትን ማክበር እንጂ ሥጋን የሚበድሉትን አለመፍራት ነው፡፡  ኧረ ክርስትና መብታችንንና ነፃነታችንን በሰማዕትነት ማስከበር ነው፡፡ ኧረ ክርስትና በትንሹ ታምኖ መገኘት ነው፡፡ ኧረ ክርስትና የኹላችን ዓፀድ የሆነች ኢትዮጵያን ከክፉዎች መታደግ ነው፡፡ ኧረ ክርስትና ለአገር ለዓለም የሚጸልዩ ገዳማውያን አባቶቻችን በወህኒ ቤት ሲማቅቁ እምቢ እነዚህ ለዓለም ምዉት የሆኑ የሰማያዊ ንጉሥ ገንዘቦች ናቸው አትንኳቸው፣ ልቀቋቸው (ወደ በአታቸው መልሷቸው) ብሎ ጠበቃ መቆም ነው፡፡

የርእሴን ስያሜ ለአስተያየቴ መቋጫ ላድርገው፡፡ ነገሩ ባጭሩ እንዲህ ነው፡፡ ሰውየው ገበሬ ነው፡፡ በአንድ ወቅት አዝመራው ሠምሮለት በዓውድማው ከምሮ በመገረም ይመለከተዋል፡፡ በክምሩ ከመደሰት ይልቅ ሐዘኔታ ይሰማዋል፡፡ ለካስ ያ የሰጠ አዝመራ ናላውን እስከሚያዞረው ድረሰ ከወሰደው ብድር የሚተርፍ አይደለም፡፡ የዚህን ጊዜ፣ አይ አንች አዝመራ ያለሽ መስሎሻል ተበልተሸ አልቀሻል፡፡ አለ ይባለል፡፡ ዛሬ ቤ/ክ የወያኔ ‹አይጦች› አጽሟን አስቀርተዋታል፡፡ ለቅዳሴ፣ በዓላት ስንሄድ ያለች ይመስለናል፡፡ የተቀደሰውን በፍጹም ብልግናው የደፈረው ፣ በወንጀል በጨቀየ እጁ አይነኬውን የነካው ፍልፈል ወያኔ ግን በእጅጉ ሸርሽሯታል፡፡ የዚህ ቅጥ ያጣ ርኵሰት መጨረሻ ምን ይሆን ? ቅ/ዳዊት ‹ርኢክዎ ለኀጥእ ዐብየ ወተለዐለ ከመ አርዘ ሊባኖስ፤ ወሶበ እገብዕ ኃጣእክዎ፡፡› (አገርና ሕዝብ ያዋረደውን ወያኔ እንደ ደጋ ዛፍ ከብሮ ገንኖ ዓየሁት፤ መሠረቱ ውንብድና፣ ሌብነትና ቅጥፈት በመሆኑ ከወገኖቼ ጥቂት መክሬ ኢትዮጵያዊነት ይዤ በተመለስኁ ጊዜ አጣሁት፡፡ ስንኳን ሰውነቱን ስም አጠራሩንና ቦታውን አላገኘሁትም፡፡) ያለው ቃል መፈጸሚያዎች እንደሚሆኑ አልጠራጠርም፡፡

ኢትዮጵያ በዋናነት የምትመካበት መንፈሳዊ ሀብቷ ነው፡፡ የአብሮነታችን፣ የአንድነታችን፣ በባህልም ሆነ በብሔራዊ ሥነ ልቦና መልክ የሚገለጹ መልካም እሴቶቻችን ኹሉ ዋልታና ካስማ ነው፡፡ መንፈሳዊ ድርቅ የመታውና ድቀት ያገኘው ኅብረተሰብ መጨረሻው እንደ ነውረኛውና ሰብአዊነት ከውስጡ ነጥፎ ክፉ አውሬነቱ በማስፈራርቾነት ከሚታየው የወያኔ ትግሬና ሎሌዎቹ ስብስብ ጋር መደመር ነው፡፡

በመሆኑም ለኢትዮጵያ ቤ/ክ ምእመናንና ምእመናት (በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ የምትገኙ)፣ በተለይም የቤ/ክ ተረካቢ ወጣቶች አድባራትና ገዳማት በሙሉ የቤ/ክርስቲያናችን ህልውና አደጋ ላይ የወደቀው ወያኔ ገና ከማለዳው በጥላቻና በዘር ፖለቲካው ተመርዞ ኢትዮጵያን፣ ሕዝቧን፣ ባለውለታዋ የሆነውችን የኢኦተቤ/ክ፣ የዚህች ቤ/ክ ጠበቆች ናቸው ብሎ ያሰባቸውን የኅብረተሰብ ክፍሎች  ለማጥፋት አቅዶና ሆን ብሎ ከ27 ዓመት በፊት በጽሑፍ ነድፎ፣ ይህንኑ መክሥተ አጋንንት በተግባር ማዋል ሲጀምር ነው፡፡ የቤ/ክርስቲያናችን ፈተና ከአጠቃላዩ የአገር ፈተና ተለይቶ ባይታይም የልጆቿን አፋጣኝ ውሳኔና ተግባራዊ እንቅስቃሴ የሚጠይቁ ጉዳዮች ፊታችን ስለተደቀኑ ጊዜ ሳንሰጥ አቅማችን የፈቀደውን ሁሉ እንድናደርግ በአገርና በቤ/ክ ጉዳይ ውስጤ እየደማ በሕማም የምገኝ ታናሽ ወንድማችሁ በምትወዷትና በምታከብሯት በወላዲተ አምላክ ስም እማፀናችኋለሁ፡፡ በዚህም መሠረት፣

  • ወያኔ በቤ/ክርስቲያናችን ከመንፈሳዊው ሥርዓትና ሕግ ውጭ ያስቀመጣቸው (ከርእሰ ሊቃነጳጳሳት እስከ ተራ አገልጋይ ምእመናን የማያውቋቸውና በፖለቲካ ‹ተሿሚነት› የተሰየሙ በመሆናቸው) ከገጠር እስከ ከተማ የሚገኙ ምእመናን በየአጥቢያው ሳይመክሩበትና ሳይስማሙበት ከዝርፊያ የተረፈውንና በልዩ ልዩ ባንኮች ውስጥ የሚገኘውን ጥሪት በሙሉ በኢንቨስትመንት ስም ለወያኔዎች ለማስተላለፍ ብሎም ቤ/ክርስቲያኗን የማፍረስ ሂደት ለማፋጠን የሚደረገውን ደባ በአስቸኳይ ማስቆም፤
  • ከጠቅላይ ቤ/ክህነት እስከ አጥቢያ ቤ/ክ ሰርገው የገቡትንና አሁን ባሉት ካድሬዎች እገዛ የሚደረግላቸውን መናፍቅን (ተሐድሶዎች) ከማጋለጥ ጀምሮ በአፍ በመጣፍ መለየት፤
  • ወያኔና ጉዳይ አስፈጻሚው አቦይ ማትያስ ያሰማሯቸውን ሰራቅያን ወፈያታውያን (ሌቦች፣ ቀማኞችና ወንበዴዎች) ከአጥቢያ ቤ/ክ ጀምሮ በኅብረት በማጋለጥና ሰላማዊ ሰልፍ በማድረግ መቃወም (አዲሱ ጠ/ሚ ይህንን ነፃነታችንን ለመጠቀም እንድንችል በጎ ፈቃድ አሳይቷል)፤
  • (የድኆች/ምስኪኖች ችግር ስለሌለብን እነሱን መርዳት፣ ለእውነተኛ አገልጋዮች በንስሓ ልጆች በኩል ለመተዳደሪያቸው ተገቢውን ማድረግ እንደተጠበቀ ሆኖ) በበዓላትም ሆነ በአዘቦት የሙዳየ ምፅዋት፣ ልዩ ልዩ መባዕ እና በንግሥ በዓላት የሚደረጉ ሥጦታዎችን በሚመለከት (የገንዘብ÷ ወርቅ እና ከብት) ማዕቀብ ማድረግ
  • ማኅበረ ቅዱሳን የሰንበት ተማሪዎችን በማስተባበር፤ ከኢትዮጵያ ውጭ የምትገኙ የቤ/ክርስቲያኒቷ ልጆችና ካህናት ክርስቶስ ሠላሳ ቦታ አልተከፈለምና በጎሣ (በመንደር ልጅነት) መቧደኑን፣ ቤ/ክርስቲያንን ለዘመድ አዝማድ መጠቀሚያ ማድረጉን በአስቸኳይ አቁማችሁ እና ነፃነታችሁን ተጠቅማችሁ በምትችሉት ኹሉ ቤ/ክርስቲያንን የመታደግ ሥራ ላይ እንድታተኩሩ በአክብሮት ጥሪዬን አስተላልፋለሁ፡፡
Filed in: Amharic