>

የማለዳ ወግ ... አይዞህ ናፍቆት እስክንድር ነጋ ! ላንተም የጨለመው ይነጋል ...(ነቢዩ ሲራክ)

አይዞህ ናፍቆት ! አንተ አባትህ ለሚወዳት ኢትዮጵያና ህዝቧ ሲል እንደ አብሃም ልጅ ይስሓቅ ለመስዋዕት የቀረብክ ነህና ጻድቁን ትመሰላለህ ! ልበ ሙሉው ሀገር ወዳድ አባትህ ለመስዋዕት ያቀረበህ ስለሚወዳት ሃገሩ ፍቅሩን ሲያሳየን ነበር። እስክንድር ኢትዮጵያን የሚወዱ ሁሉ ብርቅየ ልጅ ነህ ! የልበ ሙሉዎች ወላጆችህ የአብራክ ውጤት ፣ የኢትዮጵያ ብሩህ ዘመን አርበኛ ልጅም እንልሃለን ! ያኔ … ትር ትር አያልክ ወደ ትምህርት ቤት ወስዶ ሲመልስህ የሆነው ትዝ እያለ የሚያውከው ማናችንንም ቢሆንም ትዝታው ላንተ የህመም ሁሉ ህመም እንደሚሆንብህ ይገባኛል። አባትክን እስክንድርን በፈለጉት ቦታና ጊዜ መያዝ እየቻሉ ከአንተ ለይተው በካቴና ጠፍረው ለመውሰድ ያስገደዳቸው ጀግናውን ለመፈተን እና ለማንበርከክ ቢሆንም እስክንድር የሚከፍለው መከራ ከአንተ አልፎ ለቀረው ትውልድ በመሆኑ ሃዘኑ ጎድቶ ያልጎዳው ብርቱ አባት ነው! አንተ ግን ጨክነው ከአባትህ አጅ ስለመነጠቁህ ስለለያዩህ አትዘን ፣ ቂምም አትያዝ … ሁሉንም በቀል ለሚመልሰው ፈጣሪ አምላክ ስጥ ! እንደ ሊቁ አባትህ ተማር ተመራመር እንጅ በደልን በበቀል ለመመለስ አትነሳ !
አባትህ እስክንድር ነጋ “ወንጀለኛ ነው ” ብየ አላምንም። አለምም ወንጀለኛ ነው ብሎ አለማመኑን በሚሰጠው ክብር እየተገለጠ መገኘቱን በአደባባይ እያየን ነው። እስክንድር ወህኒ ከተወረወረ ወዲህ እንኳ የመናገርና የመጻፍ ብሎም ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ ነጻነትን የሚደግፉና የሚያቀነቅኑ ቁጥራቸው አናሳ የማይባል ተቋማት አባትክን በክብር እያነሱ በየዓመቱ የክብር ተሸላሚ ሲያደርጉት እንጅ ሲያወግዙት አላየንም። “እስክንድር ነጋ ወንጀለኛ አይደለም! “ሲሉ ድምጻቸውን በማሰማት አባትህ እየከፈለው ላለው መስዋዕትነት ክብር ሞገስ ሰጥተውታል ።
እኛም የታሳሪው መስዋዕት አባትህ አስተምሮት ተጠቃሚዎች ነን። ኢትዮጵያን እና ህዝቧን ከወደድን ፍርሃታችን መፍራት ማቆም እንድንጀመርና መስዋዕነቱን “እስከቀራንዮ ” ተግተን እንድንገፋበት ካስተማሩን ትንታግ የሃገሬ ልጆች ቀዳሚው እስክንድር ነጋ ለመሆኑ ጥርጥር የለኝም። እነሆ ዛሬ ያለ ፍርሃት መጻፍ መናገር የጀመርነው ዲሞክራሲያዊ መብቱን ከለላ አድርገን ሳትሆን አባትህ ያስተማረን የሃገር ፍቅር ስሜትን መከታ አድርገን ለመሆኑ አንዱ ምስክር ነኝ ። እናም የወዳጀ ልጀ ! አባትህ የእኔንም የፍርሃት ቀንበር ሰባሪው አባትህ ነው ። አባትህ ትንታጉ እስክንድር ድሎትን አሻፈረኝ ብሎ ሲነሳ ለእሱ ለራሱ ስሜት ብቻ አልኖረምና የእኔንም የመሰሎቸን ፍርሃት ከላያችን ላይ ገፋፊው እሱ ነበር ። እነሆ ያ ሆነና እውነቱ ያመንን የተከተልነው ለሰብአዊ መብት መከበር ተግተናል ። በክፉ ተኩላዎች ተከበን በአደጋ ላይ ተከበን ስንናገር ስንጽፍ ለሚደርስብን ቅንጣት ታክል አንፈራም ! ደግሞም በኢትዮጵያ አምላክ እንጠበቃለን !
እናም የእስክንድር ቅምጥል ናፍቆት ልጃችን ሆይ አይዞህ ! … ጨለማው ነግቶ ኩሩውና ትንታጉ አባትህ የእሙሃይ ልጅ ወዳጀ እስክንድር ነጋ ይመጣል ! በእቅፉም ያሞቅሃል ! በፍቅሩ ያደምቅሃል ! አይዞህ የወዳጀ ልጅ ወዳጀ !!!!
የኢትዮጵያ ትንሳኤ ቀን … !

የአባትህ ወዳጅ ወንድምህ …
ነቢዩ ሲራክ

 

Filed in: Amharic