>

የተሿሚው ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ ንግግርና የወያኔ/ኢሕአዴግ መግለጫ ሲፈተሽ! (ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው)

የወያኔ/ኢሕአዴግ ምክር ቤት ከመጋቢት 11 ቀን እስከ መጋቢት18 ቀን 2010 ዓ.ም ድረስ መደበኛ ስብሰባ ማድረጉን በመግለጽ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ላይ መግለጫ አውጥቷል፡፡ የመግለጫው መንፈስ ወይም ይዘትና አዲሱ ጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ አሊ ትናንትና በበዓለ ሢመታቸው ላይ ባነበቡት ጽሑፍ ላይ “መንግሥት ቁርጠኛ ነው!” እያሉ ያቀረቡት ጽሑፍ መንፈስና ይዘት ፈጽሞ የመይገናኝና የሚቃረንም ነው፡፡ የሚስማሙበትም ቦታ አለ እሱን ወደ ኋላ እናየዋለን፡፡
እኔ መግለጫቸውን በአጭሩ ግለጸው ብባል “ቢበርም ፍየል ነው!” ብየ ነው ልገልጸው የምችለው፡፡ ሁለት ገጠር የሚኖሩ ልጆች ናቸው አሉ ከርቀት ፍየል ይሁን አሞራ በውል ያልለየ ነገር ተመልክተው አንደኛው ፍየል ነው ሲል ሌላኛው አሞራ ነው ስላለ ተወራረዱና ተጠግተው ለመመልከት ወስነው ተራመዱ፡፡ ርቀቱን እንዳጋመሱ አሞራ ነው ያለው ልጅ “እዚያ ድረስ መድከም አያስፈልገንም!” ብሎ ድንጋይ ያነሣና ይወረውርበታል፡፡ ነገርየው ለካ አሞራ ኖሮ ሲወረወርበት በረረና ሔደ፡፡ አሞራ ነው ያለው ልጅም ፍየል ነው ያለውን ልጅ “ዓየኸው? ስወረውርበት በሮ ሔደ!” ቢለው ፍየል ነው ብሎ የነበረው ልጅ “ቢበርም ፍየል ነው!” ብሎ እርፍ!፡፡
ወያኔ/ኢሕአዴግ በዚህ መግለጫው ድርጅቱ በሁሉም ረገድ ከፍተኛ ስኬትና እመርታ ለሀገሪቱና ለሕዝቧ እንዳስመዘገበ፣ ዲሞክራሲን (መስፍነ ሕዝብን) እንዳሰፈነ፣ በብሔረሰቦች መካከል እኩልነትን መሠረቱ ያደረገ ሰላምና አንድነት እንደፈጠረ፣ እራስን በራስ የማሥተዳደር መብት እንዲሁም ነጻነት ማጎናጸፉን…. ያትታል፡፡ ይገርማል! ይህ መግለጫ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳየው ነገር ቢኖር ሰዎቹ ስሕተታቸውን አምነው ለመታረም ፈጽሞ ዝግጁ አለመሆናቸውን ነው፡፡
የተባለው ስኬትና እመርታ…. ለሀገርና ለሕዝብ ከተመዘገበ ታዲያ ይሄንን ሁሉ ምስቅልቅል ምን ፈጠረው እነ ወያኔ??? ፦
* የተባለው እድገትና እመርታ የወያኔ የንግድ ድርጅቶችና የወያኔ አጋር ባለሀብቶች እንጅ የሀገርና የሕዝብ መሆን ባለመቻሉና ስላልሆነም አይደለም ወይ???
* ድህነቱ ሐሰተኛ አኀዞቻቹህ እንደሚገልጹት ሳይሆን ትምህርት ቤቶች በረሀብ ምክንያት እራሳቸውን ስተው በሚወድቁ ተማሪዎች እስኪሞሉ ድረስ በሀገሪቱ ያልነበረ ገጽታ እያሳየ በመባባሱ አይደለም ወይ???
* በሀገሪቱ መካከለኛ መደብ (middle-class) ጠፍቶ ሀገሪቱ የጥቂት ሀብታሞች፣ የድሆችና ከድህነት ወለል በታች የሆኑ ዜጎች ሀገር በመሆኗ አይደለም ወይ???
* ብሔረሰቦች ሐሰተኛ የሆነ የሚያፋጅ ታሪክ ተፈጥሮ እየተነዛ ጭምር አንድነታቸውንና ዝምድናቸውን የሚያፈራርስ መርዘኛ የጥላቻ ስብከት ሥልጣን ከያዛቹህ ጊዜ ጀምሮ በመንዛታቹህ አይደለም ወይ???
* በጎሳ ፌደራሊዝም (የራስ ገዝ) አሥተዳደር ሽፋን ጠባብነት በመሰበኩና በመራገቡ አይደለም ወይ???
* ሕዝቡ በምርጫ መንግሥት መለወጥ የሚችልበትን ዕድል ፈጽሞ ሊያገኝ ባለመቻሉ አይደለም ወይ???
* ሀገሪቱ የአንድ አናሣ ጎሳ ንብረት ብቻ እንድትሆን በመደረጉ ሌላው ደግሞ የበይ ተመልካች ሆኖ እንዲማቅቅ በመደረጉ አይደለም ወይ???
* ሕዝቡ በገዛ ሀገሩ መብት በማጣቱ ሦስተኛና አራተኛ ዜጋ በመደረጉ አይደለም ወይ???
* ከዚህም አልፎ በዘሩ ብቻ ለዘር ማጥፋትና ማጽዳት ጥቃት በመዳረጉና በማለቁ አይደለም ወይ???
* በከፍተኛ ብድርና እርዳታ የሚሠራው መሠረተ ልማት ሀገርና ሕዝብ ለማይወጡት ዕዳ ተዳርገው የተገኘው ገንዘብ እስከ 70% ድረስ እየተመዘበረ በቀሪው ገንዘብ የወረደ የጥራት ደረጃ ያለው ብላሽ ሥራ እየተሠራ ሀገርና ሕዝብ ለድርብርብ ኪሳራ በመዳረጋቸው አይደለም ወይ???
* የሕግ የበላይነትና ተጠያቂነት ጨርሶ ባለመኖሩ አይደለም ወይ???
* የአሥተዳደር በደል ሊገለጽ ሊነገር ከሚችለው በላይ ስለሆነ አይደለም ወይ???
* ግፉ ስላንገሸገሸውና ሊሸከመው ከሚችለው በላይ በመሆኑ አይደለም ወይ??? ወዘተረፈ.
እውነታው የሚያሳየው ይሄንንና ሌሎች ተገልጸው የማያልቁ ግፎችንና ችግሮችን ከሆነ ወያኔ ስለየትኛው እመርታና እድገት ነው የሚያወራው??? ስለራሱና ስለአጋሮቹ እድገትና እመርታ ካልሆነ በስተቀር ሀገርና ሕዝብ ያሉበት ሁኔታ ዓለም ያወቀው ፀሐይ የሞቀው የአደባባይ ምሥጢር ነው፡፡
ወያኔ ሰላምና መረጋጋት በዚህች ሀገር እንዲሰፍን የሚፈልግ ቢሆን ኖሮ ቢያንስ በዚህ ሰዓት እራሱን ለውጦ አዲስ ምዕራፍ ለመጀመር ፈቃደኛ ይሆንና ተግባራዊም ያደርግ አልነበረም ወይ??? እንዲያው በከንቱ ድከሙ ቢላቹህ ነው እንጅ ወያኔ ይለወጣል የሚል እምነት የሚጣልበትና ተስፋ የሚደረግበት አገዛዝ እንዳልሆነ ከዚህ ሁሉ ምስቅልቅል በኋላ እጅግ ወደኋላ ተመልሶ ከሦስት ዓመት በፊት ከነበረበት ቦታ በመቀመጥ እንዲህ ዓይነት መግለጫ ከማውጣቱ መረዳት ትችላላቹህ፡፡ ይሄ ማለት ለኢትዮጵያ ሕዝብ እጅግ አሳዛኝና ከፍተኛ ንቀት ነው፡፡
ሕዝቡ ለውጥ ሲጠብቅ፣ ባለሀብቱ ሊሠራ ሊንቀሳቀስ የሚችልበት የተሻለ ነጻነት ሲጠብቅ፣ ወጣቱ የተሻለ ሁሉን አቀፍ ለውጥ ሲጠብቅ፣ ምሁራኑና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ተማሪዎች የተሻለ የአካዳሚክ (የምኅዳረ ትምህርት) ነጻነት ሲጠብቁ፣ የኪነጥበብ ሰዎች የተሻለ ሞያዊ ነጻነት ሲጠብቁ… ሁሉም ከዚህ በኋላ ወያኔ/ኢሕአዴግ የተሻለ ነጻነትና መብት ለመስጠት መዘጋጀቱን ያረጋግጣል ብሎ ሲጠብቅ ወያኔ/ኢሕአዴግ ግን በመግለጫው ላይ በግልጽ እንዳረጋገጠው ምንም ነገር እንዳልተፈጠረ ቆጥሮ በርካታ ርምጃዎችን ወደኋላ በመመለስ የቆየና ሕዝብን ለዐመፅ የዳረገውን ኢዲሞክራሲያዊ (ኢመስፍነ ሕዝባዊ) እና ኢሰብአዊ በሆነውና በቆየው “ልማታዊ!” በሚል ሽፋን ባስቀመጠው የአፈና አሠራሩ ባለሀብቱ ልማታዊ ባለሀብት እንዲሆን፣ ሙሁራኑ ልማታዊ ምሁራን እንዲሆኑ፣ የኪነጥበብ ሰዎች ልማታዊ የኪነት ሰዎች እንዲሆኑ ሌሎቹም ልማታዊ ምንትስ፣ ልማታዊ ቅብርጥስ በሚለው የጥርነፋ ማዕቀፍ ውስጥ በመሆን ሁሉም ከጎኑ እንዲቆም ትዕዛዝ ያዘለ ጥሪ አስተላልፏል፣ በዚህ መልኩ እንደሚንቀሳቀስም ቅንጣት እንኳ ሳያፍር ይፋ አድርጓል፣ ይህ እንዲሆን በርትቶ እንደሚሠራ ከዚህ ውጭ ምንም ዓይነት መንገድ እንደሌለ አረጋግጧል፡፡
በከንቱ የምንቃዥና በሌለ ተስፋ ተስፈኛ የሆንን ሁሉ እንግዲህ ተስፋ እንቁረጥ!!! የነ ዐቢይ ባዶ ስብከት ዳቦና ሰላም የሚሆንህ ከመሰለህ ይህ ቅዠትህ ከንቱ መሆኑን ነገ የምታየው ይሆናል፡፡ በዐቢይ ባዶ ስብከቶች እየተሸነገሉ መጨቆን፣ መረገጥም፣ መመዝበር…. ለውጥ ነው ካላልክ በስተቀር አንድም የሚለወጥ ተጨባጭ ነገር እንደማይኖር ስነግርህ በከፍተኛ ሐዘን ነው፡፡ ይህ መጨረሻ ላይ የወጣው የወያኔ መግለጫ ያረጋገጠው ሀቅ ይሄንን ነው፡፡
በተለያየ ጊዜ በተደጋጋሚ “ወያኔ መቸም ቢሆን የመለወጥ ተስፋ፣ ብቃት፣ ፍላጎትና ዕድል የለውም!” የምላቹህ ከመሬት ተነሥቸ አይደለም፡፡ ወያኔ በሀገሪቱና በሕዝቧ ላይ የፈጸመው ለከት የለሽ ክህደት፣ አረመኔያዊ ግፍና ዝርፊያ ምዝበራ የአገዛዝ ዘመኑን በብሔራዊ እርቅ ወይም በፍትሐዊና ተአማኒ ምርጫ ሰላማዊ በሆነ መንገድ ሥልጣን በማስረከብ እንዲቋጭ ፈጽሞ እንደማይፈቅድለት ወይም ዕድል እንደማይሰጠው ስለሚያውቅ ከዚህም የተነሣ በነዚህ መንገዶች ሥልጣን መልቀቅን ፈጽሞ እንደማይፈቅድ ጠንቅቄ ስለማውቅ ነው፡፡ ይሄንንም በተደጋጋሚ አሳስቤያለሁ፡፡ ማሰብ የሚችል ጭንቅላት ያለው ሁሉ ይሄንን ጠንቅቆ ይረዳል፡፡
ይህ የወያኔ መግለጫ “ቢበርም ፍየል ነው!” ካለ በኋላ ዞር ይልና ደግሞ የአዞ እንባውን እያነባ ሕዝብን ለመደለል “ሕዝባዊው ዐመፅ የተፈጠረው ሙስና በመንሰራፋቱ፣ ሥልጣንን አላግባብ መጠቀምና ብልሹ አሥተዳደር በመስፋፋቱ… ነው!” በማለት ከላይ የዘረዘረውን የልማትና ዲሞክራሲ ስኬትና እመርታ መልሶ ይቃረናል፡፡ ይሄ መጨረሻ ላይ ሕዝብን ለዐመፅ የዳረገው ለዐሥርት ዓመታት የተንሰራፋው ስር የሰደደ እጅግ አሳሳቢና ተስፋ አስቆራጭ ችግር ከነበረና ካለ ታዲያ መቸ የትና እንዴትስ ነው ዲሞክራሲ (መስፍነ ሕዝብ) የሰፈነው??? ፣ ተመዘገበ የተባለው ሁሉን አቀፍ ዕድገትና እመርታስ ሊመዘገብ የቻለው???
መግለጫው የጠቀሳቸው ችግሮች መፈጸማቸውን ይገልጽና ሲያበቃ “ለዚህም ኃላፊነት እንወስዳለን!” በማለት ያላግጥና ወያኔ በየጊዜው መግለጫ ባወጣ ቁጥር ሕዝብን ሸንግሎና አታሎ ለማለፍ ሲያደርገው የቆየውን ጥረት እዚህም ላይ ይደግመዋል፡፡
ነገር ግን በየጊዜው በሚያወጣቸው መግለጫዎቹ ላይ “ኃላፊነትን እንወስዳለን!” የሚለው ቃል ለማለት ያህል ብቻ የሚባሉ መሆናቸውን የሚያረጋግጠው ችግሮች ሳይቀረፉ ከዕለት ወደ ዕለት እየተባባሱና እየተወሳሰቡ መምጣታቸውና “ኃላፊነትን እንወስዳለን!” እንደተባለው ሁሉ ኃላፊነቱን የወሰዱ ሰዎች ሕጋዊ እርምጃ ሲወሰድባቸውና ችግሮቹም ሲቀረፉ አለመታየቱን ባስተዋልን ጊዜ ነው፡፡
አገዛዙ አለብኝ ያለውን ችግር መፍታት የሚፈልገው ችግሩን በፈጠሩት ሰዎቹ ነው፡፡ ለነገሩ አገዛዙ ያለ እነኝህ ተጠያቂ ሰዎች ባዶ ነው፡፡ አገዛዙ የተሞላው ይህ አሁን በሀገራችን የታየውን ቀውስ በፈጠሩና ኃላፊነቱን ሊወስዱ በሚገባቸው ሰዎች ነው፡፡ እነሱ የሉም ወይም በእነሱ ላይ እሮምጃ ተወሰደ ማለት አገዛዙ የለም ማለት ነው፡፡ ለዚህ ነው ወያኔ በየጊዜው “ኃላፊነቱን እንወስዳለን!” እየተባለ ኃላፊነቱን ከወሰዱ ወይም ሊወስዱ ከሚገባቸው ከፍተኛ ባለሥልጣናት እስከ ዝቅተኛው ድረስ ሕጋዊ ርምጃ ሲወሰድ የማናየውና መውሰድም የማይፈለገው፡፡
በመሆኑም በዚህ ምክንያት አገዛዙ ተጠያቂነትንና የሕግ የበላይነትን ማረጋገጥ አልቻለም፡፡ እስካልቻለ ጊዜ ድረስም ሀገራችን የገጠማትን ችግርና ፈተና ለመፍታት ፈጽሞ አይችልም ወይም ብቃት የለውም ማለት ነው፡፡ የማይችል ከሆነም ሥልጣኑን ለሕዝብ እንዲያስረክብ የኢትዮጵያ ሕዝብ ጫናና ግፊት ማሳደር ወይም ሁሉንም አማራጮች ተጠቅሞ ማስወገዱ አማራጭ የሌለው ጉዳይ ነው ማለት ነው!!!
ወያኔ ግን ተገቢነት ያለውን እርምጃ ወስዶ የሀገሪቱንና የሕዝቧን ችግር ከመፍታት ይልቅ የኢትዮጵያ ሕዝብ ጥያቄ የአቶ ኃይለማርያም ከሥልጣን መወገድ ወይም የጠ/ሚ ለውጥ እንደሆነና እሱንም በማድረጉ ሰላም እንደሰፈነ፣ የሕዝቡ ጥያቄ እንደተመለሰ አስመስሎ በዓለም አቀፍ የብዙኃን መገናኛ እንዲነዛ በማድረግ የኢትዮጵያን ሕዝብ የለውጥ ጥያቄን አዳፍኖ ለማስቀረት ከፍተኛ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡
የተሿሚው ጠ/ሚ ጽሑፍም ወያኔ ሊደርሳቸው የሚፈልጋቸውን አካላት በሙሉ በማታለል ጥቅሙን ሊያስጠብቅ በሚችልበት አቀራረብ መድረስ የቻለበትና በሚገባ ተቀምሮ የተዘጋጀ ሸፍጠኛ ጽሑፍ ነው፡፡ ከመጀመሪያው ቃል እስከ ምስጋናው ቃል ሰውየው የተናገረው እያንዳንዱ ቃል ለፖለቲካ ትርፍ ታስቦበት የተነገረ ነው፡፡
በጽሑፉ ሆን ተብሎ የተቃውሞ እንቅስቃሴው ተዋናይ የሆኑ አካላትን ማለትም ተቃዋሚ ፓርቲዎችን (ቡድኖችን) ፣ ዳያስፖራውን (ግዩራኑን)፣ ወጣቱን… አገዛዙ እንደጠላት ሳይሆን እንደ ሀገር ወዳድ ተቆርቋሪ ዜጎችና አጋር የመፍትሔ አካላት አድርጎ እንደሚያይና አብሮ ለመሥራትም “ጽኑ ፍላጎት አለው!” ብሎ አስመስሎ በመናገር የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የሕዝባዊ ትግሉ ተዋንያን ሰላማዊ የችግር መፍቻ መንገድ ወይም አማራጭ አጥተን ተገደን ወደ ዐመፅ ያመራን ሳይሆን አጉራዘለል፣ ተራ በጥባጭ፣ ነውጥ ናፋቂ ስለሆንን ብቻ ሀገር እየበጠበጥን ያለን አስመስሎ በማቅረብ በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለማስወገዝ፣ ለሕዝባዊ ትግሉ ድጋፍ እንዲነፍግ ለማድረግ ባሴረና በተሰላ አቀራረብ በሚገባ ታስቦበት የተዘጋጀ ጽሑፍ ነው በዐቢይ በኩል እንዲቀርብ የተደረገው፡፡ በሚያሳዝን ሁኔታ ይሄ ሸፍጥ ሊገባው የሚችለው በጣም ጥቂቱ ነው፡፡
እውነታው ግን ማንም እንደሚያውቀው ወያኔ “በኢሕአዴግ መቃብር ላይ…!” እያለ ለአንዲት ደቂቃም እንኳ ቢሆን የሕዝባዊውን ዐመፅ ተዋንያንንም ሆነ ተቃዋሚዎችን እንደ ሀገር ወዳድ ዜጎችና የመፍትሔ አካላት አጋሮች አድርጎ ፈጽሞ ተመልክቶና አቅርቦ የማያውቅ መሆኑ ነው፡፡ ቀንደኛ ጠላት አድርጎ ነው ሲያሳድና ያለፍርድ በግፍ ሲያስር ሲያሰቃይ አፍኖ ሲገድል ሲያጠፋ የኖረው፡፡ ዐቢይ ከዚህ በኋላ አገዛዙ እንዲህ ዓይነት ዕይታ ይኖረዋልና ብሎ “አብረን እንሠራለን፣ የመፍትሔ አካል እንድትሆኑም እንፈልጋለን!” በማለት ጥሪ ቢያቀርብ ወይም ቢናገር የተናገረው እውነት መሆኑ ወደፊት የሚታይ ሆኖ አነጋገሩ እንደአነጋገር ትክክል በሆነ ነበር፡፡ የተባለው ግን እንደዚያ አይደለም አገዛዙ ከበፊቱም እንዲህ ዓይነት ቀና አመለካከት ያለው እንደሆነ አደርጎ ነው የተናገረው፡፡
ይሄም የተደረገው ሆን ተብሎ እላይ ለገለጽኩት ሸፍጥ ነው፡፡ በዚህም ዐቢይ ሰው ተስፋ እንዳደረገው ዓይነት ሰው ሳይሆን ምን ያህል ከሕዝብ ፍላጎትና ጥቅም ተፃራሪና መሰሪ መሆኑን ማየት ይቻላል፡፡ ዓለም አቀፍ የብዙኃን መገናኛዎችም ከቀረበው ንግግር እየጠቀሱ ከተናገሩት መረዳት እንደሚቻለው ወያኔ ያሰበው ሸፍጥ የተሳካለት መሆኑን ነው ዘገባዎቹ ያረጋገጡት፡፡
ከወያኔ ሸፍጠኛ አቀራረብ በተጨማሪ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እንዲህ ዓይነት የተዛባ ድምዳሜ እንዲይዝ ዘወትር የወያኔ መጠቀሚያ የሆኑ ነፈዝ የተቃዋሚ ፓርቲ አመራር ተብየዎች፣ በወያኔ ተወርሰው ወያኔን እያገለገሉ ያሉት የመኢአድና የሰማያዊ ኃላፊዎች፣ በተቃዋሚ ስም የሚንቀሳቀሱ ሌሎች የወያኔ ቅጥረኞች፣ ከሀገር ውስጥና ውጭ ያሉ አክቲቪስት (ስሉጥ) ነን ጋዜጠኛ (ዘጋቢ) ነን ፖለቲከኛ (እምነተ አሥተዳደራውያን) ነን የሚሉ  ደነዝ ግለሰቦች፣ ሆዳቸውን አምላኪ ጥቅማቸውን አሳዳጅ የሆኑ ታዋቂ ሰዎችና የእነዚህ ሁሉ ተከታይ ደጋፊዎቻቸው በብዙኃን መገናኛዎች ለዶ/ር ዐቢይ ሲሰጡት የሰነበቱት የጋለ ድጋፍ ላቅ ያለ አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡
ወያኔ በዐቢይ በኩል ሕዝብን በማታለል የግዛት ዘመኑን ለማራዘም ጥረት እያደረገ የሚገኘው ሕዝቡ “በዚህ አጋጣሚ ቀስ ብለን ወያኔን የምንገላገልበት ክፍተት ይፈጠር ይሆናል ዕድል እናገኝ ይሆናል!” በሚል ተስፋ አውቆ ይታለልልኛል በሚል ብልጠት ነው፡፡ ፍላጎቱም መቶ በመቶ ተሳክቶለታል እነ ኢሳትና ኦኤምኤን እንኳን አልቀሩም እነሱ ተጃጅለው ሕዝብ እንዲጃጃሉ ሲያደርጉለት፡፡
ዓለም አቀፍ የብዙኃን መገናኛዎችም ሆኑ ምዕራባውያኑ የኢትዮጵያ ሕዝብ ጥያቄ ወይም ችግር ምን እንደሆነ ጠንቅቀው ያውቃሉ፡፡ እውነቱን እያወቁ እንዳላወቁ ሆነው ከወያኔ ጎን መቆማቸው የሚያሳየው ወያኔ በደንብ ማስመሰል እስከቻለበትና ሁኔታው ከቁጥጥሩ ውጭ እስካልወጣበት ጊዜ ድረስ ምንጊዜም ከጎኑ መሆናቸውን ነው የሚያሳየው፡፡ ምክንያቱም የኢትዮጵያ ሕዝብ ከአገልጋያቸው ከወያኔ ስለማይበልጥባቸውና ጥቅማቸውን ማስጠበቅ ስለሚፈልጉ ነው ከወያኔ ጋር በመመሳጠር ይሄንን ደባ በመፈጸም የሕዝብ ጥያቄ እንዲዳፈንና ወያኔ እንዲተርፍ ጥረት እያደረጉ የሚገኙት፡፡
እንደምናየው ከሆነ በዚህ አዝማሚያ ከሁለት ሳምንት በኋላ በአሜሪካ መንግሥት ምክር ቤት ለማጽደቅ ወይም ለመጣል ድምፅ እንዲሰጥበት የተቀጠረውና የግፈኛው የወያኔ አገዛዝን ባለሥልጣናትን የመዘዋወር ነጻነትን የሚገድበው፣ የዘረፉትን የሕዝብ ሀብት የየግል ሒሳብ እንዳይንቀሳቀስ የሚያግደው፣ ለፍርድ እንዲቀርቡ የሚጠይቀው የHR. 128 የውሳኔ ሐሳብም የመጽደቁ ነገር እጅግ አጠራጣሪ ይመስለኛል፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆይ! እንግዲህ ቁማራቸው እንደምታየው የዚህን ያህል በነፍሳችን እንደተጫወቱብን እያየህ ነው፡፡ የሚያዋጣህ ነገር ቢኖር ከላይ እንደጠቆምኩት የተከፈለው መሥዋዕትነት ተከፍሎ ስር ነቀል የሆነ ለውጥ እንዲመጣ መነሣት ብቻ ነውና ጊዜ ሳታባክን ተነሥ!!!
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!! ሞት ለሸፍጠኞች!!! ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!
ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው
Filed in: Amharic