>

የእስክንድር ሰብዕና፤ (ሞሀመድ አሊ መሀመድ)

እስክንድር ሊጠይቁት የሚመጡትን ሁሉ “አስቸገርናችሁ አይደል? የኛ ነገር ዛሬም ነገም መታሰር ሆነ” በማለት የሰው ውለታ እየከበደውና እየተቅለሰለሰ  ሲናገር ማየት ያስገርማል። ይልቁንስ እሱና ጓደኞቹ ለሀገርና ለህዝብ ለሚከፍሉት ዋጋ እኛ ምን ያህል ባለዕዳዎች መሆናችንን ማን በነገረልኝ?
እስክንድር ሁሌም ከፊቱ ላይ በማይጠፋው ፈገግታ ታጅቦ “መሐመድ ደውየልህ በሰፊው ሳንጫወት ድጋሜ ታሰርኩ; ይቅርታ ግን busy ስለነበርኩ ነው; ስለእኛ መታሰር ሲጨነቅ የነበረውን ህዝብ በየአካባቢው እየሄድን ማመስገን ነበረብን; ግን ምን አጠፋን?” ጥያቄም አለው። እኔን የገረመኝ ደግሞ ድጋሜ በመታሰሩ ሊፈጥርበት በሚችለው የስሜት ጫና ውስጥ ሆኖ ተገናኝተን ልናወራ ባለመቻላችን ራሱን ተወቃሽ ለማድረግ መሞከሩ ነው።
እስክንድር እንደተፈታ ብዙ ጉዳዮችን አንስተን ተጨዋውተን ነበር። ግን ጠያቂው ብዙ ስለነበር በሌላ ጊዜ ሰፊ ጊዜ ወስደን ለማውራት ቀጠሮ መያዝ ነበረብን። በሠዓቱ እሱ ስልክ ስላልነበረው የኔን ተውኩለት። ሆኖም ግን ከአዲስ አበባ ውጭ ብዙ ቦታዎች መሄድ ስለነበረበት እንዳሰብነው ሰፊ ጊዜ ወስደን አላወራንም።
ይሁን እንጅ በጠያቂ ብዛት በተጨናነቀበት ሠዓትም ቢሆን ከእስክንድር ጋር ስናወራ በማንም ላይ ቂም እንደማይዝና “የሥርዓቱ ባህሪ ነው” በማለት ነበር በትህትና የሚናገረው። ግን ይጠይቃል።
“እግርህ ሥር የወደቀን አውሬንኳ በጫማህ አትጨፈልቀውም። ሰብኣዊ ርህራሄህ አይፈቅድልህም። እኛኮ እግራቸው ሥር የወደቅንና ምንም ማድረግ የማንችል (helpless) ነን። በእኛ ላይ ሲፈፅሙ የነበረውን ፈርጀ-ብዙ በደልና ጭካኔያቸውን ሳስበው ይገርመኛል። ሰው እንደሰው እንዴት አይራራም? እኛ ምን በደልናቸው?”
ዛሬም ይጠይቃል; “ግን ምን አጠፋን?”
Filed in: Amharic