>
5:13 pm - Wednesday April 19, 7809

የራምሴ ጩኸት የወለዳቸው የምድራችን ድንቅ መሪዎች (ኪዳን ሰው)

ራምሴ በዘመነ ፈርዖን እስራኤላዊያን በብርቱ የባርነት ቀንበር ስር ወድቀው የሚጮሁባት የግብፅ ግዛት የሆነች ስፍራ ነበረች። በዚች የመከራ ቦታ የአይሁድ ህዝብ ለ430 ዓመታት በቀንና ሌሊት ርህራሄ በጎደለው የፈርዖን ወታደሮች ጀርባቸው በጅራፍ እየተገረፈ ጡብ በመስራት፣ ፒራሚዶችን በመገንባት የተሰቃዩባት የመከራ ቦታ ናት። የእነዚህ ህዝቦች የዘመናት ጩኸት በፈጣሪ ጆሮ መሰማቱ ታዳጊ እንዲላክላቸው ዋና ምክንያት ነበር። ሙሴ የተባለው የእስራኤላዊያን መሪና ታዳጊ ሆኖ ከፈጣሪ የተላከውም በዚህ ወሳኝ ወቅት ነበር። የሙሴ ወደ መሪነት መምጣት እስራኤላዊያንን ከባርነት ከማውጣቱም በላይ የፈርኦኖችን የዘመናት ተፈሪነትና ኃያልነትም ዳግም እንዳያንሰራራ አድርጎ ያዋረደ የእግዚአብሔር እጅ የተገለጠበት ሰው ጭምር ነበር።
በተመሳሳይ ሁኔታ በምድረ ኢትዮጵያ ላለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት የታየው ግፍ፣ ስቃይ፣ መክራ፣ መፈናቀል፣ እስር፣ ስደትና ግድያ ህዝቡ አምርሮ ወደ ፈጣሪው እንዲጮህ ገፊና ዋና ምክንያት ሆኖታል። ይህ የወያኔ ፈርኦናዊ ቀንበር እየከበደ በሄደ ቁጥር የህዝቡ ጩኸትም እየበረታ መጥቷል። በመሆኑም እግዚአበወሔር ትዕቢተኞችን ሊያዋርድ፣ ትሁታንንም ከፍ ከፍ ሊያደርግ፣ ህዝቡንም ከመከራ ሊያሳርፍ፣ በጎሳና በቋንቋ ተከፋፍላ ወደ መፈራረስ እየተንደረደረች ያለችውን አገራችንን ኢትዮጵያንም በአንድነቷ ጠብቆ ሊያኖር ሁለት ብላቴኖችን በኃይልና በሞገስ ቀብቶ አስነሳ።
የትግራይ የፋሽስት ቡድን ወያኔ በተንኮልና በመሰሪ ተግባሩ ሰፊውን የኦሮሞ ህዝብ ከወንድሙ ከአማራ ህዝብ ጋር ለማጨራረስ ፓሊሲ ቀርፆ ላለፉት 27 ዓመታት የጥላቻ ፓለቲካ ሲያራምድ መቆየቱና የጥፋት ሃውልትም ማቆሙ ይታወቃል። ሆኖም ግን ይህ የወያኔ የጠላትነት ግንብ፣ ህዝብን ከፋፍሎ የመግዛት ሴራ፣ አገርን የማፈራረስና ህዝብን እርስ በእርሱ የማጨራረስ አጀንዳ ትውልድ አምጦ በወለዳቸው ድንቅ ልጆቹ በአቶ ለማ መገርሳና በዶ/ር አብይ አህመድ ከመፍረሱም በላይ ፈጣሪ የህዝቡን የዘመናት ጩኸት ሰምቶ መልስ ለመመለስና የክፉዎችን የጥፋት አጀንዳ ለማፈራረስ ዶ/ር አብይ አህመድን የምድራችን ሙሴና ታዳጊ አድርጎ አስነስቷል። ሁለቱ ድንቅ መሪዎችም በሁለቱ ህዝቢች መካከል ወያኔ ገንብቶት የነበረውን የጠላትነት አጥር በማፈራረስ የአንድነትና የፍቅር መሰረት ገንብተዋል።
ጥላቻ ከምድሪቷ ላይ ሊሻር፣ ዘረኝነት ዳግም የምድራችን በሽታ ላይሆን፣ በጠላትነት መተያየት ቀርቶ በፍቅር ልንኖር፣ ፍትህ በምድሪቷ ሊሰፍን፣ ነፃነትና እኩልነት እውን ሊሆን፣ ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል ሊረጋገጥ፣ ኢትዮጵያም እንደ አገር ከተደቀነባት የመበታተን አደጋ ተርፋ ኃያልና የበለፀገች አገር ልትሆን እግዚአብሔር የምድሪቷ ታዳጊ አድርጎ ዶ/ር አብይ አህመድን አስነስቷል። ይህ እውነት ያልገባቸው ሰዎች ይህን የፈጣሪ ጣልቃ ገብነት የወያኔ የተቀነባበረ ሴራ አድርገው ያዩታል። እውነታው ግን ወያኔ እንዲህ ያለ የአንድነት፣ የፍቅር፣ የእኩልነትና የነፃነት ሰባኪና መሪ ወደ ስልጣን እንዳይመጣ ተግታ ስትታገል መቆየቷና በሽንፈት መረታቷ ነው።
ዶ/ር አብይ አህመድ ለዚች ቀን፣ ለዚህ ትውልድ፣ ለዚች አገር ታዳጊና ጠባቂ ሆኖ መፈጠሩ እንቆቅልሽ የሚሆነው ለወያኔና ለመሰሎቹ ብቻ ነው። ለእኛ ግን ከፈጣሪ የተላከ ታዳጊ ነው፣ የወያኔን የዘመናት ክህደት፣ አገር የማውደምና ህዝብ የማሰቃየት ስራ በቃ ሊል እንደ ዳዊት ከወንድሞቹ ተመርጦ ለንግስና የተቀባ መሪ ነው። አስጨናቂውን ጎልያድ (ወያኔን) ከህዝቡ ፊት ሊያዋርድና ህዝቡንም ከመከራ ሊያሳርፍ የተነሳ የምድራችን ሙሴ ስለሆነ ከነቀፋና ከትችት ተቆጥበን እግዚአብሔር የሚሰራውን ድንቅና ታምር ብናይ እንዴት መልካም ይሆናል።
በአጠቃላይ ዶ/ር አብይ አህመድ የምድራችን የራምሴ ጭንቀት የወለደው እውነተኛ መሪ ከመሆኑም በላይ የምድራችንን ፈርዖኖች የጭቆና ዘመን በቃ ለማለትም አቅም፣ ድፍረት፣ እውቀት፣ ወኔ፣ ድፍረት፣ ሞገስና መለኮታዊ ድጋፍ ያለው ሰው ነው። የተበላሸውን ለማስተካከል፣ የጠፋውን ፍቅር ለመመለስ፣ ትውልዱ የሚናፍቀውን ፍትህ፣ ነፃነት፣ እኩልነትና ፍትሃዊ የሃብት ተጠቃሚነት ለማስፈን የትኛውም የወያኔ የክፋትና የማስፈራሪያ ክንድ የማያንበረክከው በፈጣሪው ታምኖ ህዝቡን ወደ ተስፋይቱ ምድር የሚያደርስ የምድራችን መሪ ነው። በመሆኑም አቶ ለማ መገርሳና ዶ/ር አብይ አህመድ የምድራችን የራምሴ ጩኸት፣ የፍትህ እጦት፣ የነፃነት እጦት፣ የእኩልነት እጦት፣ የፍቅር እጦት፣ የአንድነትና የመረጋጋት እጦት የወለዳቸው የዘመናችን ድንቅ የፍቅር፣ የአንድነትና የኢትዮጵያዊነት ሰባኪና መሪዎች ናቸው።
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ ፣ ዳርቻዋንም ያስፋልን!!
ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!!
Filed in: Amharic