>

በዶ/ር አብይ ላይ የሰነቅነዉ ተስፋ፤ «የተማረ ይግደለኝ» (ሃራ አብዲ)

በዶክተር አብይ ላይ የሰነቅነው ተስፋ፣ እምነት እንድናሳድርበት ያገዙን እውነቶች፣እንዲሁም፤ ተስፋዉን ወደ ድል ለመቀየር ማድረግ የሚገቡን፤ ከብዙ በጥቂት።
ተስፋ፣ ንድፈ-ሃሳብ (concepet) በመሆኑ፣በሚታይ፤ በሚዳሰስና በሚጨበጥ ተግባር እስካልተለወጠ ድረስ፤ አንጀት አያነሳም። እስከዚያው ድረስ ግን ልብ ያሞቃል። ነግሆን በጉጉት እንድንጠብቅ የማድረግ አቅም አለዉ። ተስፋ። አንዳንዱ ተስፋ በህይወታችን በጎ እንዲሆንልን ከመመኘት የግል የነፍሳችን መቃተት የሚወለድ ነዉ።ከዚህ የላቀዉ ደግሞ በቅዱስ መጽሀፍ የተጻፈዉ ታላቅ ተስፋ ነዉ። ተስፋ፤ ፍቅርና እምነት በሰዉ ልጆች ህይወት ያላቸዉን ስፍራ የምንገነዘብበት። ለዛሬዉ ብዙም ወደዚህኛዉ ተስፋ አልዘልቅም።
ሌላዉ ተስፋ ደግሞ በብዙ ትግል፤ በብዙ እምባ፣በብዙ ግፍና ሰቆቃ ዉስጥ ታልፎ በህዝባችን ምናብ ዉስጥ ነፍስ የዘራዉና በማቆጥቆጥ ላይ ያለዉ የኢትዮጵያ ትንሳኤ ተስፋ ነዉ።ሀገራችን ኢትዮጵያና ህዝባችን ፣ላለፉት ሃያ ሰባት አመታት በግፈኞች እጅ አይሆኑ ሆነዋል።ከምድራችን በፈለቁ፣ሆኖም ኢትዮጵያን እንደሀገራቸዉ፣ ህዝብዋን እንደህዝባቸዉ በማያዩ የዘመናችን እንግዴ ልጆች፣ ህልቆ መሳፍርት የሌላቸዉ ንጹሃን ዜጎቻችን በጠራራ ጸሀይ በጭካኔ ተገድለዉ፤ታስረዉ፤ በእስር ቤት በእሳት ጋይተዉ፤ አንዳንዶች እርቃናቸዉን ተገርፈዉ፣ ያም አልበቃ ሲል በጠባቂዎቻቸዉ እጅ ህይወታቸዉ አልፎአል ( አርማዬ ዋቄና ሌሎችም ሲጠቀሱ ይኖራሉ!!)የእነዚህ ዉድ ወንድሞችና እህቶቻችን ደምና፣ የወላጆቻቸዉ እምባ ዛሬ ተስፋ ለምናደርበት ቀን አድርሰዉናል።
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር በመሆን በነገዉ እለት ቃለ-መሃላ የሚፈጽመዉ ዶ/ር አብይ አህመድ አሊ እና እርሱን ለዚህ ታላቅ ክብር፤ ያበቃዉ ትግል ፣የብዙዎች ጣምራ ፍልምያ ዉጤት ነዉ።
የህዝባቸዉን ሰቆቃ የተገነዘቡ ብቻም ሳይሆን ከዚህ ህዝብ ጋር ከመቆም ዉጭ ለእኛም ሆነ ለሀገራችን ምርጫ የለም ብለዉ ቆርጠዉ በተነሱ የህዝብ ልጆች ምክንያት፣ የምስራች! ሀገራችን የሚማርክ ተስፋ ጸንሳለች። የተስፋ ብልጭታ እንደንጋት ኮከብ ጉሙን ሰንጥቃ ወጥታለች።ይህችን የንጋት ኮከብ ከአድማስ ባሻገር አንጋጠን በማየት ላይ ነን።( We are watching…the world is watching…the enemy is watching…and we are watching carefully!!)በእንባ ጎርፍና በደም ጅረት የተገኘ ተስፋ ስለሆነም እምነታችን በከንቱ አይደለም።

እምነት እንድናሳድርበት ያገዙን እዉነቶች፤

«ስልጣኔ ማለት የራስ ያልሆነን ነገር ካለመፈለግ ይጀምራል» ብሎ የሚናገርን ሰዉ ተስፋ ማድረግ ካልተቻለ ፤ማንን ማድረግ ይቻላል?
«ይህችን የመሰለች ሀገር እያለን ድሃ መሆናችን ያሳዝናል»የሚል ልባም ተስፋ ካላደረግን ማንን እናደርጋለን?
የበላዮች፣ ከታች ያሉትን የሚያዩበት መነጽር የተስተካከለ መሆን አለበት…( ቃል በቃል አይደለም)
ያለዉን የግንባር ስጋ ተስፋ ካላደረግን፣
«የኢትዮጵያ ህዝብ ሰርገኛ ነዉ…አብሮ የሚፈጭ፤ አብሮ የሚበላ…
ያለዉን የትዉልድ ድልድይ ተስፋ ካላደረግን ማንን እናደርጋለን??( ዶ/ር አብይን ያካተተዉ የቲም ለማ እምነት) ዶ/ር አብይ በንግግር ብቻ ሳይሆን ኢንሳን ያዋቀረ፤ በሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ሆኖ የሰራ፣ በኦሮምያም በምክትል ፕሬዚዳንትና በከተማና የቦታ አስተዳደር በሚኒስትርነት ሃላፊነቱን በብቃት የተወጣ ነዉ። ብቻም አይደለም! በተሰማራበት ሁሉ እዉቀቱን በስራ የተረጎመ ፣እዉቀት ያላቸዉን በሙያቸዉ ያሰማራ ፣አንባቢና አርቆ አሳቢ ነዉ። ( እረ እንኩዋን እግዚአብሄር ረድቶን ጨርቃቸዉን ቤተ- መንግስት ከሚያሰጡ እጅ ስልጣን ወጥቶ ለ እስፔስ ምርምር ሊያበቃን በሚያልም እጅ ዉስጥ ገባ.. ምን ይሳነዋል!!)
እንዳላሰለቸሁዋችሁ ተስፋ አደርጋለሁ። እርግጥ ነዉ። አንድ እንጨት አይነድ ፤አንድ ሰዉ አይፈርድ ይላሉ አበዉ።ለዚህ ነዉ ዶ/ር አብይ በቲም የመጣዉ። ቲም ለማ። የኦሮምያዉ ፕሬዚዳንት ለማ መገርሳ ራሱ ኢትዮጵያን ለመምራት ብቁ ሆኖ ሳለ፣እንደመጥምቁ ዮሀንስ «ከኔ ሁዋላ የሚመጣዉ ከኔ ይበልጣል ሲል እሱ የሊቀመንበርነቱን ወንበር ለቆ ለትግል ወንድሙ መሰላል ሆኖ በታሪካችን አይተነዉ የማናዉቀዉን ሆኖም ስንናፍቀዉ የኖርነዉን ከግል ዝናና ክብር ይልቅ ሀገርን ማስቀደምን አሳየን። ይህም የሚነግረን አብይ ነገር አለ።ቲም ለማ ይህን በማድረጉ፤ የህዝባቸዉ ልብ ተከፈተላቸዉ። የሰዉ ልብ ከስጋ ነዉ የተሰራዉ። ፍቅር እንጂ ጠብመንጃ አይከፍተዉም።ማንኛዉንም መስዋእትነት ለመክፈል በተዘጋጁ፤ለኢትዮጵያ ትንሳኤ ጥርጊያ መንገድ ለመክፈት በቁርጠኝነት በተነሱ፤ አቅሙና ችሎታዉ ባላቸዉ፣ ከግራ ፤ከቀኝ፤ ከፊት ከሁዋላ ነቅቶ በሚጠባበቅ ህዝብ በሚደገፉ አመራሮች ተዋናይነት ሀገራችን ከቀድሞ የክብር ማማዋ ላይ ብቅ ትላለች!!!!ብቁ አመራር ሊሰጥ የሚችልና «ሀገሬን፤ ኢትዮጵያን»የሚሉ መማክርት ያሉት አንድ ሰዉ፣ ለሀገር ድንቅ ሊያደርግ ይችላል።
አንድ ሰዉ ሀገር ሊያጠፋም ይችላል። መለስ እንዳጠፋዉ ሁሉ …ሂትለር እንዳጠፋዉ ሁሉ…
አንድ ሰዉ ደግሞ ሀገር ሊያድን ይችላል።ማንዴላ አንድ ሰዉ ነበር…ጋንዲ አንድ ሰዉ ነበር…ማርቲን ሉተር ኪንግ አንድ ሰዉ ነበር…እነዚህ በስንት ክፍለዘመን አንድ ጊዜ ብቻ የሚፈጠሩ ግለ -ሰቦች ከግል ጥቅማቸዉና ከንቱ ዝናቸዉ በላይ የሀገራቸዉን ነጻነትና ጥቅም በማስቀደማቸዉ ከነሱ ቀጥሎ የመጣዉ ትዉልድ ስማቸዉን እየተቀባበለ ስላከበራቸዉ፣ከሀገራቸዉ አልፎ በአለም ደረጃ ምሳሌ ሆነዋል።
እና ዶ/ር አብይ አህመድ አንድ ሰዉ ቢሆንም ተገቢዉን አመራር በመስጠት ከአዲሱ ካቢኔዉ ጋር በመሆን የሀገራችንን የሽግግር ስርአት ያደራጃል ብለን ተስፋ ብናደርግ አይበዛም። ይችላል!!
«ስልጣኔ ማለት የራስ ያልሆነን ካለመፈለግ ይጀምራል »አለ።የተማረ ይግደለኝ!! ( book smart ) የሆነ ሁሉ እንዲህ እዉቀቱን ከነፍሱ ጋራ ያዋህዳል ማለት አይቻልም።

ጥሩ የተናገረ ሁሉ ጥሩ ይሰራል ማለትም ደግሞ አይቻልም። ሆኖም የሰዉ ልጅ ሌሎችን ወደ ራሱ አለም የሚያስገባበት ሁለት መስኮቶች አሉ ብዬ በግሌ አምናለሁ። አንደኛዉ ንግግር ፤ ሁለተኛዉ ምግባር ነዉ።የዶ/ር አብይን ንግግሮች የሰማንና በነዚያ ንግግሮች ዉስጥ የስብእናዉን ሸማ (fabric) በአንደኛዉ መስኮት ዘልቀን ለተመለከትን የተናገረዉን በገቢር ያዉላል የሚያስብሉ መተማመኛዎች መዘን ማዉጣት እንችላለን።በሁለተኛዉ መስኮት ቀረብ ብለን ለማየት ታላቁ ቤተ-መንግስት ገብቶ ስራ እስኪጀምር መጠበቅ ይኖራል።

ዶ/ር አብይ ስልጣኑን ካደላደለ በሁዋላ ቃሉን ካጠፈስ? ብዬ ማሰላሰል አሁን አልፈልግም። (I know..)

ተስፋዉን ወደ ድል ለመቀየር ማድረግ የሚገቡን፤ ከብዙ በጥቂት።

ዶ/ር አብይ መልካም ቢያስብና መልካም ቢናገርም ወያኔዎች አያሰሩት ይሆናል ለሚባለዉ ምን ማድረግ እንችላለን? ። ወያኔ ዶ/ር አብይንም ሆነ ቲም ለማን ለመጉዳት ከፈለገ፤በዘረፈዉ ንብረት፤ በአባላቱ ነፍስና የእነሱ በሆነዉ ሁሉ ላይ የሚመጣዉን መአት መቀበል ፈልጎአል ማለት ነዉ።
አንድ አይን ያለዉ ሰዉ ባፈር አይጫወትም የሚባለዉን ብሂል ልብ ይሉአል።
ለማንኛዉም ቲም ለማ፣ ከግራ ከቀኝ፣ ከሁዋላ፣ ከፊት፣ ለዶክተሩ ቦዲ ጋርድ አሰናድቶአል ብለን እናምናለን።
-ወያኔ በቀጥታ ከሚያዝዋቸዉ ጦራቸዉ ላይ አንስቶ በአልባሌ ቦታዎች ያስቀመጣቸዉ ከፍተኛ የጦር መኮንኖች የኦሮሞ፣ የአማራ፣ የደቡብ፣የጋምቤላ፣ የአፋርና የሌሎችም ብሄረሰብ ተወላጆች ፣በተጠንቀቅ ዘብ ይቁሙ። ወደፊተኛዉ መስመር የሚመጡበት ጊዜዉ አሁን ነዉ።
የዋሆች አይደለንም!! ወያኔዎች ባገኙት ቀዳዳ ሁሉ ተጠቅመዉ የዶ/ር አብይን ተልእኮ ለማደናቀፍ ሌት ከቀን መጣራቸዉ ለአፍታም ሊዘነጋ አይገባም!!ስለዚህ በሚገባቸዉ ቁዋንቁዋ መንገር ተገቢ ይሆናል።
-የኢትዮጵያ ህዝብ የትግራይ የዉስጥ ቅኝ አገዛዝ በቃ ብሎአል።ከእንግዲህ የትግራይ ወያኔዎች ለራሳቸዉና ለሚወክሉት ህዝብ ደህንነት ሲሉ መራራ ሽንፈታቸዉን መጎንጨት አለባቸዉ። ካለበለዚያ……
-መላዉ ህዝባችን የህዝባዊ እምቢተኝነት ትግሉን አቀነባብሮ ያፋፍማል። የትጥቅ ትግሉ ይሰፋል!!
-በወያኔ ነፍሰ-ገዳዮች ላይ እርምጃ መዉሰድ ተጠናክሮ ይቀጥላል።
-በዝርፍያ ያካበቱዋቸዉ ንብረቶች የጥቃት ኢላማ ይደረጋሉ።
-በመከላከያ፣በፖሊስ፣በደህንነት፣በስለላ መዋቅር ዉስጥ የሚሰሩ ጀግኖች ወገኖቻችን በየመስካቸዉ የወያኔን እድሜ ለማሳጠር ሌት ከቀን ይተጋሉ።
-ቄሮ ፤ ፋኖ፣ዘርማ ፣ከኦሮምያና ከአማራ ክልል አልፎ ከሌሎች ኢትዮጵያዊ ወገኖች ጋር ትግሉን በማስተሳሰር ሀገራዊ መልክ ያስይዛሉ።
-ለዶ/ር አብይ መመረጥ ከፍተኛ ድርሻ ያበረከቱት የገዱ ብአዴንና የደቡብ ኢትዮጵያ ወንድሞችና እህቶቻችን ታሪካዊ ሀቀኛነትና ወገናዊነታቸዉ ምንጊዜም ሲታወስ የሚኖር ነዉ።( በነገራችን ላይ አማራ ክልል፤ ደቡብ ክልል ምናምን ፣እያለ ወያኔ ባጠረዉ የእሾህ አጥር ላይ እሳት የምንለቅበት ቀን ሩቅ አይሆንም። አንዳች ይከልላቸዉ! ሀገራቸዉ ደደቢት እነሱ ደደቦች)
-በዉስጥም በዉጭም የምትንቀሳቀሱ ተቃዋሚዎ ፓርቲዎች ልዩነታችሁን አቻችሉና የኢትዮጵያን የሽግግር ዘመን አቃርቡ።በአንድነት ሆነን የወያኔን አረመኔያዊ አገዛዝ ዶጋ አመድ እናደርጋለን።
ለማንኛዉም ፣በተስፋ የምንጠብቀዉን ለመስማት ከሃያ አራት ሰአታት ያነሰ ጊዜ ነዉ የቀረን!!
« ናና አርሂቡ ናና፣ አብይ እተዉ ሴና»!!!!!
ነጻነትዋና አንድነትዋ ተጠብቆ ኢትዮጵያ በክብር ለዘላለም ትኑር!!!

Filed in: Amharic