>
5:13 pm - Sunday April 19, 8826

አብይ፤ በቃል የቆሰለ በቃል ይድናል? [መስፍን ነጋሽ - ዋዜማ ራዲዮ]

በድጋሚ ለማስታወስ፤ ኢትዮጵያን በተመለከተ ለአዲሱ ጠ/ሚ የምነግረው አዲስ ምኞትም ሆነ አዲስ ጥያቄ የለኝም።
ይህን ስንል ግን በአብይ አህመድ አሊ(3አ) እጅ የገባውን ሥልጣን ማጣጣሌ አይደለም። አብይ ከጠ/ሚ መቀመጫ የሚመነጭ ሕጋዊና ልማዳዊ ሥልጣኖች ይኖሩታል። እርግጥ እነዚህን ሥልጣኖች በነጻነት የሚጠቀምበት አቅምና እድል ይኑረው አይኑረው አሁን ላይ እርግጠኛ ሆነን መናገር አንችልም። ለማንኛውም ግን፣ አብይ በዘመኑ አነስተኛም ይሁን ትልቅ ለውጥ የሚያመጣ ከሆነ ሁለት ነገሮች ወሳኝ ሚና ይኖራቸዋል። እነርሱም የድጋፍ መሠረቱን ማስፋት እና በጎ ቃላትን ማብሰር ናቸው። እነዚህን ሳይይዝ የሚያደርገው ነገር አይኖርም።

በቃል የቆሰለችው አገር

ኢትዮጵያችን በድርጊት ብቻ ሳይሆን በቃልም የቆሰለች አገር ናት። የቃል ቁስሉ ወደ አካላዊ/ተግባራዊ ቁስል እንዳይለወጥ የምንሰጋበት ብዙ ጉዳዮች አሉ። በቃል የመጣ ቁስል ህክምናው የሚጀምረው በቃል ነው። አብይ ይህን ህክምና ለመጀመር ይችላል። ይቺ አገር የፖሊሲ ብቻ ሳይሆን የፖለቲካ ቋንቋ ለውጥም ያስፈልጋታል። አብይ ሊያደርገው ይችላል ብዬ በተሻለ ተስፋ የምናገረው ነገር ካለ በዚህ በኩል ሊያመጣ የሚችለውን ተጽእኖ ነው።

አብይን ጨምሮ የለማ ቡድን ከብሔርና ከክልል አጥራቸው አልፈው ዝነኛና በተወሰን መልኩም ተቀባይ ያደረጋቸው ነገር በመሠረቱ ንግግራቸው ነው፤ ቃላቸው ነው። ንግግራቸው ደግሞ ከአስተሳሰባቸው የመነጨ እንደሆነ የሚያምኑ ብዙ ዜጎች አሉ፤ ወይም ማመን ይፈልጋሉ። ለማ የመናገር ብቻ ሳይሆን በቀላሉ የመታመን ጸጋ ያለው አይነት ሰው ይመስላል። አብይ ከአንጀቱም ይናገር ከአንገቱ፣ ጥሩ የመናገር ችሎታና ተፈጥሮ አለው። ከኀማደ ቀጥሎ መምጣቱ ደሞ የበለጠ እንዲጎላ ሊያደርገው ይችላል። የለማ ቡድን የትርክትና የቋንቋ ለውጥ እንደሚያስፈልግ ማመኑን የሚያረጋግጡ በርካታ ክስተቶችን አስቀድሞ አይተናል፤ ለምሳሌ የክልሉ ቴሌቪዥን እና የኦሕዴድ የፌስቡክ እንቅስቃሴ ሊጠቀስ ይችላል።

ለአብይ፣ ማንም የማይከለክለው መሣሪያው ቃሉ ነው። ሌላውን ሥልጣን ሁሉ እፉኝቶቹ ሊቆላልፉብት ይችላሉ፤ እንደ ኀማደ ሊያንሳፍፉት ይችላሉ። እድሉን ሲያገኝ የሚናገረውን ቃል መወሰን ግን ቀላል አይሆንላቸውም።
በጠ/ሚ ቦታ የሚቀመጥ ሰው በንግግሩ ብዙ ጥፋት ሊያስከትል ይችላል። ብዙ ትርፍ የሚያስገኝ ዘር ሊዘራም ይችላል። በዚህ በኩል መለስንም ኀይለማርያምንም አለመሆን ነው። እንደቀዳሚው ሁሉን አዋቂ አለመምሰል፤ እብሪተኛ፣ ተሳዳቢ አለመሆን። እንደኋለኛው አድማጭን ቀርቶ ራስን የማያከብር መዘላበድ ውስጥ አለመግባት፣ ከደኅንነቱ አካል የሚመጣውን መረጃ ሳያላምጡ እየዋጡ መልሶ አለመትፋት ነው። ከአነጋገር ይፈረዳል፤ ከአያያዝ ይቀደዳል።
ስለ በጎ ቃላት ሳነሣ እርሱም ከልክ እንዳያልፍ መጠንቀቅ እንደሚያስፈልግ ግን መጠቆም ይኖርብኛል። ቃላት አላግባብ ሲለፉ ትርጉማቸውን ያጣሉ፣ ወይም ተቃራኒ ትርጉማቸውን ይላበሳሉ። የስብከትና የአስተማሪነት ቃና ለመሪ የተገባ አይሆንም። አብይ ጥሩ ተናጋሪ ቢሆንም በኢንተርኔት ካገኘናቸው ንግግሮቹ ውስጥ የታዘብናቸውና ጥያቄ የሚጋብዙት ይዘቶች ሊደገሙ የማይገባቸው ናቸው። ብዙ አለማብራራት የንግግር ጥበብ መጀመሪያ ነው።
ቃል ይገድላል፤ ቃል ያድናል እንዲል።

የድጋፍ መሠረት

የኢሕአዴግ መዋቅር፣ ቢሮክራሲው፣ መከላከያው እና ደኅንነቱ የአብይን መሪነት በተግባር እንዴት እንደሚቀበሉትና ምን አይነት ምላሽ እንደሚሰጡት የተረጋገጠ እውቀት የለንም። የድጋፍ መሠረቱ በዋናነት በኦህዴድ ውስጥ የተወሰነ ሆኖ ከመነሣቱ አንጻር፣ የአገር መሪ ሲሆን ይህንን የድጋፍ መሠረቱን በፍጥነትና በጥልቀት ለማስፋት እርምጃ መውሰድ ይኖርበታል። የኀማደን ሥልጣን የመሳለቂያ ተረት ካደረጉት ቁልፍ ምክንያቶች አንዱ፣ ለዋስትና የሚጠራ አንድም የድጋፍ መሠረት የሌለው መሪ መሆኑ ነበር። ሌላው ቀርቶ ራሱ የሚመራው “ንቅናቄ” ኢትዮጵያን ለመምራት የሚያስችል ወሳኝ የድጋፍ መሠረት ሊሆን የሚችል አልነበረም። አብይ በመላው ኦሮሚያና ኦሮሞዎች ዘንድ ተቀባይነት ቢኖረው እንኳን ይህ ብቻውን ኢትዮጵያን ለመምራት በቂ አይደለም።

«አብይ ቢያንስ በኢሕአዴግ መዋቅር እና በፌዴራሉ ቢሮክራሲው ውስጥ የማይናቅ ድጋፍ ሊያገኝ የሚችልበት ሰፊ እድል እንደተፈጠረለት እንመለከታለን። እድለኛ ነው። በኢሕአዴግ ምክር ቤት አገኝ የተባለው ድምጽ ለዚህ አንድ ጥሩ ጠቋሚ ነው። (መለስ ዜናዊ ይህንን የመደመጥ እድል ያገኘው በማሰር፣ በማባረር፣ በማስፈራራትና በሙስና ነበር።) አብይ በኦሮሚያና በኦህዴድ ውስጥ ቢያንስ የተደላደለ የሚመስል የድጋፍ መነሻ አለው። ለዚህ ሹመት ያበቃውም እርሱው ነው።»

በብአዴን እና በክልሉ ቢሮክራሲ አካባቢም የማይናቅ የድጋፍ መሠረት ሊያገኝ እንደሚችል ካየነው ተነሥተን ጊዜያዊ ግምት ማስቀመጥ እንችላለን። በከተሞች አካባቢ እና “በደቡብ ክልል”ም እድል ሊሰጡት የተዘጋጁ ብዙ ይመስላሉ። ይህ ሁሉ ግን ተመንዝሮ ሊያልቅ የሚችል ስለሆነ እስከመጨረሻው የሚተማመንበት ሊሆን አይችልም። ሌላው ቀርቶ በኦሮሚያ ያለው ተቀባይነትም ሊሸረሸት ይችላል። (መለስ ዜናዊ የድጋፍ መሠረት ፍለጋ ከትንሿ አድዋ/መቀሌ ተሰዶ በሚጠላት ሸገር ላይ መሽጎ እንደነበር እናስታውሳለን።)
የሕዝብ ድጋፍ የሚባለው ነገር (መጠኑ የቱንም ያህል ቢሆን) በኢሕአዴግ እና በቢሮክራሲው ውስጥ ወደሚገለጥ ተቀባይነት ካልተመነዘረ ውሎ አድሮ የወተት አርፋ ነው። ስለዚህ፣ አብይ መልካም ስሙ በወቀሳ ቅጽሎች ከመዥጎርጎሩ በፊት በሚገባ ሊሠራበት ይገባዋል። ለዚህ ደሞ ረጅም ጊዜ ላይኖር ይችላል።
ትልቁ ፈተናው የሚኖረው ሌላ ቦታ ነው፤ መከላከያና ደኅንነቱ። አብይ፣ መከላከያው እና ደኅንነቱን አባል ሆኖ የሠራበት እንደመሆኑ በቅርበት የመረዳት አቅምና እድሉ ከፍተኛ ነው። ሆኖም እነዚህ ተቋማት በወሳኝ መልኩ በሕወሓት ቁጥጥር ስር ያሉ እንደመሆናቸው፣ በጥንቃቄ ሊይዛቸው የሚገቡ ይሆናሉ። በአንድ በኩል ‘ከእኛ የወጣ ነው’ በሚል በቀና መንፈስ የሚታይበት እድል አለው። በሌላ በኩል ግን ‘ስለሚያውቀን በቀላሉ ሊያጠፋን ይችላል’ የሚል ስጋት በማንኛውም ምክንያት ሊዛመት ይችላል።

«የትሕነግ (ህወሓት) የፕሮፓጋንዳ መዋቅር በአብይ ላይ ያደረገውን ዘመቻ ከግምት ካስገባን፣ አብይ መከላከያ እና ደኅንነቱን በከፍተኛ ጥንቃቄ መያዝ እንደሚኖርበት መገንዘብ አያስቸግረንም። ሰዎቹ ኀማደን የማይጎዳ እንስሳ አድርገው ስለቆጠሩት ሊጎዱት አልፈለጉም፣ አልሞከሩም። አብይን በተለየ ዐይን እንደሚያዩት የሚያጠራጥር አይሆንም። አንዳንዶቹ ጀነራሎች የአብይን መመረጥ ተከትሎ ተናገሩት የሚባለው ነገር አስገራሚም አስፈሪም ነው።»

ለማጠቃለል፣ አብይ በዘመነ ሥልጣኑ ሊፈጽማቸው የሚችሉትን ነገሮች ከሚወስኑት በርካታ ሁኔታዎች ሁለቱ እዚህ የጠቀስኳቸው ናቸው፤ የሚያንጽ ቃል እና የድጋፍ መሠረትን ማስፋትና መጠበቅ።
በቀረውስ፣ ይህን ለመጻፍ የተነሣሁት አብይ ትልቅ ለውጥ ሊያመጣ ይችላል ከሚል እምነት ተነስቼ አይደልም። ምናልባት ጥቂት ለውጥ ያስተዋውቅ ይሆናል ከሚል ብቻ ነው። በዚህ ጥቂት ከማይባሉ ጓደኞቼ ጋራ የተለየ አቋም ወስጃለሁ። ጨለምተኛ ከመሆን አይደለም። ራስን ከብስጭት የመከላከያ ስልት ተደርጎ ቢቆጠርብኝ ቅር አይለኝም። በኢህአዴግ ሺህ ጊዜ የተበደልን እና የተካድን ሰዎችና ትውልዶች፣ የአብይን መምጣት በሞቀ ጭብጨባ ባንቀበል ልንወቀስ አይገባም። ተስፋና እምነታችንን በስስት እንጠብቃታለን። ሆኖም፣ ተስፋቸው የለመለመላቸው ወገኖቼ ተስፋቸው እንዲሠምር ምኞቴ ነው።
በበኩሌ፣ ኢሕአዴግ ከልቡ ስለመለወጡ ቀርቶ ለመለወጥ ስለመዘጋጀቱ የሚጠቁም አስረጅ ፍለጋ ብባዝንም እስካሁን አላገኘሁም። ይሁንና ኢሕአዴግ/ድርጅቱ እና ነጠላ አባላቱ አንድና ያው ናቸው ብዬ አላምንም። ተቋሙን መቀየር ያቃታቸው፣ ራሳቸው ግን የተቀየሩ ሰዎች ሊኖሩ አይችሉም ብዬ አልነሣም። የለማ ቡድን እዚህ የሚካተት ይሆን? እነለማ በኦሮሚያ፣ አብይ በፌዴራል ደረጃ የዚህ አካል መሆናቸውን የሚያሳዩበት ዕድል እነሆ ከፊታቸው ቆሟል። ጥያቄው ያለው በተግባር ከመሞከራቸው ላይ ነው። እናያለን።
አስቀድሜ እንዳልኩት ለአዲሱ ጠ/ሚ የምነግረው አዲስ ምኞትም ሆነ ጥያቄ የለኝም።

Filed in: Amharic