>
5:13 pm - Sunday April 18, 5875

እንኳን ደስ አለን! (ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ) 

እንኳን ደስ አለን፡፡ ቢያንስ በሁለት ምክንያት ደስ ሊለን ይገባል፡፡ ዶ.ር አብይ በመመረጣቸውና በተመረጡበት መንገድ ደስ ሊለን ይገባል፡፡ 
ዶ.ር አብይ በመመረጣቸው ደስ ሊለን ይገባል፡፡ ሲናገሩ አድምጠናቸዋል፤ ንግግር የትእቢት፣ የማናለብኝነትና የጉልበት ፍሬ ሳትሆን፣ የእውቀትና የስነምግባር ፍሬ መሆንዋን ከእሳቸው አድምጠናል፡፡ ከእንግዲህ በየቲቪው መስኮት በአሸባሪነት የሚፈርጁን፣ በቀይ መስመር የሚያስፈራሩን፣ አግአዚና ፌደራል የሚልኩብን መሪ ሳይሆን፣ ስለማወቅና ማንበብ ጥቅም፣ ስለመከባበርና ተደምሮ ጠንካራ ሀገር ስለመገንባት የሚነግሩን መሪ ያገኘን ይመስለኛል፡፡ ከእንግዲህ የጠቅላይ ሚንስትራችን ፊት ቲቪያችንን የሚያስዘጋን አይመስለኝም፡፡ እስካሁን በተናገሩትና በሰሩት ከተወዳዳሪዎች እጅግ ልቀው የተገኙ፣ ሲናገሩ አድማጭን የሚስቡ፣ ፈገግታቸው ስሜትን የሚያፍታታ ከነፍጥ ይልቅ ለእውቀት፣ ከማስፈራራት ይልቅ ለምክር የቀረቡ ወጣት ሰው ናቸው፡፡ ከዚህ በመነሳት፣ ከአሁን በኋላም በትልቅ ችግር ውስጥ ባለችው፣ ትልቅ ሀገር፣ ትልቅ ቢሮ ውስጥ ቢያንስ በቅንነት የአቅማቸውንና የሀገራቸውን አቅም የህል ያበረክታሉ ብዬ አምናለሁ፡፡
ዶ.ር አብይ ከመመረጣቸው በላይ፣ ለኢትዮጵያ ህዝብ ትልቁ ተስፋ የተመረጡበት መንገድ ነው፡፡ እሳቸው ለ180 የኢህአዴግ አባላት በስልክና በሻይ ቡና በተላለፈ ማሳሰቢያ፤ ያለልዩነት በሙሉ ድምጽ አልተመረጡም፡፡ እሳቸው የተመረጡት ለህዝቦች መብትና ጥያቄ መመለስ የቀረበውን፣ የክልላቸውን ህዝብ ጥያቄ ጥያቄያቸው አድርገው፣ ከሁለት አመት በላይ ነግሶ ያለውን የህዝብ አመጽ ተከትለው ኢህአዴግን ፈትነው፣ አኦሄዲድና ብአዲን ጋር አሸንፈው በመውጣት ነው፡፡ ከእንግዲህ በኢህአዴግ ውስጥ ዲሞክራሲያዊ አሰራር ተመልሶ ፌዝና ለበጣ ለመሆን ተአምር ያስፈልጋል፡፡ በተለይ በጠመንጃ ስልጣን መያዝና ማስተዳደርን ዋና አማራጭ አድርጎ የሚያየው ‹‹ያ ትውልድ›› እንደነለማና አብይ ያሉ በህሊናቸው ከጠመንጃና እስርቤት ይልቅ እውቀትና መነጋገርን የያዙ ወጣት መሪዎች በየድርጅቱና የፖለቲካ ፓርቲው ስለሚተኩ (ይህ የግድ ነው) ዲሞክራሲው እየዳበረ የመሄድ ተስፋው ትልቅ ነውና ስለተስፋው መደሰት አይበዛም፡፡
ከሁሉም በላይ ለተገኘው የዲሞክራሲ ጭላንጭል በዋናነት መመስገን ያለባቸው እንደ ድርጅት ኦሄዲድና ብአዲን፣ እንደ ህዝብ ደግሞ የኦሮሞና የአማራ ህዝቦች ናቸው፡፡ የህዝብን ጥያቄ ይዞ የተነሳው አመጽ፣ በተለይ በሁለቱ ክልሎች መካከል የተደረገው የህዝብ ለህዝብ ምክክር፣ ኢትዮጵያዊነትን ከተቀበረበት አዋራውን እፍፍ ብሎ ያስነሳና ለሌሎች የኢትዮጵያ ህዝቦችም መንገድ የቀደደ ነው፡፡
ጅምሩ ለፍሬ በቅቶ፣ . . . እየተገላመጡ የማይናገሩባት፣ በተናገሩት ለእስር የማይዳረጉባት ፣ በዲሞክራሲ የበለጸገች ሀገር ለልጆቻችን ለማውረስ እንደምንበቃ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡
Filed in: Amharic