>

ከእንግዲህ ኢትዮጵያችንን በብሄርና ሃይማኖት አግላይነት ስሟን የሚያነሳ የተረገመ ይሁን! ያን ሩጫ ጨርሰናል! (ያሬድ ጥበቡ)

ከእፎይታ ምሽትና መኝታ በኋላ ስለአቢይና የመመረጡ ትርጉም ብዙ አውጠነጠንኩ ። በአቢይ ምርጫ አንዱ ከኢትዮጵያ ጫንቃ ላይ የተነሳው ቀንበር፣ ኦሮሞ በመሆናችን፣ ሙስሊም በመሆናችን እኩል አንታይም የሚለው ትርክት ነው ። ይህ ትርክት እውነትም ሆነ ምናባዊ፣ ዛሬ በአቢይ ምርጫ የተነሳ መፍትሄ አግኝቷል። ይህ ትልቅ ክንዋኔ ነው። ዴሞክራሲያዊ የሚባሉ ብዙ የምእራብ ሃገሮች እንኳ ሊያደርጉት የማይችሉትን ነው ኢትዮጵያችን ባለፉት ስድት ዓመታት ያደረገቸው። (በምእራብ ሃገሮች  ዛሬም ካቶሊክ ወይም  ፕሮቴስታንት መሆን እንኳንስ ለከፍተኛው ሥልጣን ለፓርላማ አባልነት እንኳ ጋሬጣ ይሆናል) ። በመጀመሪያ ወላይታና ፔንጤ፣ አሁን ደግሞ ኦሮሞና ሙስሊም ለታላቁ ወንበር በማጨት ትልቅ ክንዋኔ አድርገናል ። ዶክተር አቢይ ፔንጤ መሆኑን ሰምቻለሁ፣ ሆኖም ከአጋሮ ኦሮሞ ሙስሊሞች የተወለደ መሆኑ የኢትዮጵያውያን ሁሉ አለቃ ከመሆን አላስቆመውም። ስለሆነም፣ በኢትዮጵያችን ሙስሊምነትም ሆነ ኦሮሞነት፣ ጴንጤነትም ሆነ ወላይታነት ሳያግደን አንድን ኢትዮጵያዊ በዜግነቱ ማክበር የምንችል የመከባበር ሃገር መሆናችንን ነው ለዓለሙ ያስመሰከርነው። በዚህ ፍፃሜያችን ልንኮራ ይገባናል። ከእንግዲህ ኢትዮጵያችንን በብሄርና ሃይማኖት አግላይነት ስሟን የሚያነሳ የተረገመ ይሁን። ያን ሩጫ ጨርሰናል።
ሁለተኛው የአቢይ ምርጫ አንድምታ ላለፉት 27 ዓመታት የቆየው የህወሓት የበላይነት የሚያከትምበት ታሪካዊ ምእራፍ ላይ መድረሳችን ነው። ህወሓት እንኳንስ ኢትዮጵያን ትግራይን መምራት የሚያስችለው ውስጣዊ ቁመና፣ አንድነትና የሞራል ብቃት እንደሚጎድለው አሳይቷል። በመለስ እረፍት ወቅት መለስ ብቻውን ሳይሆን ህወሓትን ይዞ ነው የሞተው ብዬ ሳውጅ የገላመጡኝ ብዙዎች ኮፍያቸውን ሊያነሱልኝ ይገባል። የህወሓትን መዳከም በማወጅ ብቻ ነበር የቀሩትን የኢህአዴግ አባላት ለለውጥ ማነሳሳት ይቻል የነበረው። የጥገናው አብዮት ፍሬ አፍርቶ ይሄው ዛሬ የኦህዴድና የቄሮ አመፅ የፈጠረው አዲሱ አመራር ሥልጣን የሚረከብበት ቅፅበት ላይ ደርሰናል። በዚህም የህወሓት የበላይነት ማክተሚያ ዋዜማ ላይ እንገኛለን። ከሰሞኑ ዶር አቢይ የደህንነቱንና የመከላከያውን መረቦች ከህወሓት የበላይነት ሲረከብ፣ እኛ የማህበራዊ ሚዲያ ፊታውራሪዎችም ወያኔ ወያኔ እያልን መጮሁን እናቆማለን። ይህም ትልቅ ለውጥ ይሆናል።
የዶክተር አቢይ ጠቅላይ ሚኒስትር መሆን ሶስተኛው አንድምታ፣ የዚያ ትውልድ (የ60ዎቹ) ፀሃይ መጥለቋንና፣ አዲሱ ትውልድ ለመረከብ ዝግጁ መሆኑን ማብሰሩ ነው። ይህ በሰላም መከናወኑ ራሱ ትልቅ ፍፃሜ ነው። ዴሞክራሲያዊ ነን በሚሉ የምእራብ ሃገሮች የጃጁ የ80 ዓመት አዛውንትና ባልቴቶች ሥልጣኑን ለ50 ዓመታት የሙጥኝ ብለው ከሚንገታገቱበት ሥርአት (እን ጆን ምኬይንን ማየት ነው) ፣ የኛ የኢትዮጵያውያኑ የተሻለ መስሎ ይሰማኛል። ሆኖም ከዚያ ትውልድ አባላት የሚገኘው ትምህርትና ልምድ ትልቅ በመሆኑ፣ አዲሱ የነአቢይ ትውልድ ቀጣይ የሆነ መስተጋብርና ግንኙነቶች የሚቀጥሉበትን መረቦች መወጠር ይኖርበታል። በተለይ ሃገራችን ካጠላባት አፍቃሪ ፈረንጅ የባርነት አደጋ አዲሱን ትውልድ ለመታደግና ኢትዮጵያዊ እሴቶቻችንን ፈልፍሎ ለማግኘት፣ ብሎም በሚዲያው፣ በፊልሙ፣ በሥነፅሁፉ፣ በሥነልቦናው ባለፉት 27 ዓመታት  የተስፋፋውን የባህል ወረራ ለማስቆም በአስረካቢውና ተረካቢው ትውልዶች መሃል በመከባበር ላይ የተመሠረተ ውይይትና መድረክ ያስፈልጋል።
የዶክተር አቢይ መመረጥ አራተኛው አንድምታ ባለፉት 27 ዓመታት ከሃገራቸው የተሰደዱና በደርጉ ዘመን ተሰደው ሃገራቸው መመለስ ያልቻሉ ልጆቿ መመለስ የሚችሉበት ሁኔታ መፈጠር ነው። እነዚህ ስደተኞች ውስጥ፣ ታላለቅ ምሁራን፣ በተለያዩ መስኮች ልምድ ያካበቱ ፕሮፌሽናልስ፣ የገንዘብ አቅም ያላቸው ወይም የፈረንጅ ባለሃብቶችን ይዘው መግባት የሚችሉ ዜጎች ይገኛሉ። በተለይ ሃገራችን አሁን ለምትገኝበት የኢኮኖሚና ፋይናነስ ቀውስ መፍትሄ መሆን የሚችሉ ሃይሎች ስለሆኑ፣ በተለይ በኦሮሞና አማራ ስደተኞች ላይ ተጥሎ የነበረው የእድሜልክ ስደተኝነት ተነስቶ ሃገራቸው እንዲገቡ መደረግ የሁለቱን ክልሎች አቅም መገንባት ላይ የሚጫወተው ሚና የትዬለሌ ነው። ይህ እውን እንዲሆን ግን የደህንቱና ፀጥታው መረብና አሠራር ከህወሓት የበላይነት መፅዳት ወሳኝ ነው።
ከዚሁ የስደተኞች ወደሃገራቸው መመለስ ጋር ተያይዞም በስደት ካሉት የፖለቲካ ሃይሎች ጋር ለመነጋገር ኦህዴድ አድርጎት የነበረው ውሳኔ በአፋጣኝ ተግባራዊ መደረግ የሚችልበትና፣ አሁን ዶክተር አቢይ ጠቅላይ ሚኒስትር መደረጉ ካልቀረ፣ ያንን የኦህዴድ ውሳኔ የመንግስት ጭምር አድርጎ፣ በአመፅ እንፋለማለን የሚሉትንም ሃይሎች ያካተተ ሃገራዊ ምክክር የሚጀመርበት እድል ተፈጥሯል። ለዚህም እንዲረዳ፣ በመንግስት በኩል ብቻ ሳይሆን፣ እንደ ግንቦት 7 አይነት ሃይሎች የአመፅ ጥሪያቸውን አቁመው ወደፊት ለሚመሠረተው ሃገራዊ ምክክር ፈቃደኛ መሆናቸውን ምልክት ማሳየት ይኖርባቸዋል ። ይህን ማድረግ አቅቷቸው ግን በለመዱት ባዶ የአመፅ ጥሪ ከገፉበት፣ የሚከስሙበት አደጋ (ፖለቲካሊ ኢሬለቫንት የሚሆኑበት) ሊመጣ እንደሚችል የአቢይ መመረጥ ሊያነቃቸው ይገባል።
Filed in: Amharic