>

ትግላችን ከግለሰብ ሳይሆን ከአብዮታዊ ዲሞክራሲ ነው! (ኪዳኔ አሚን)

በኢህአዴግ ኣባል ድርጅቶች ለሊቀመንበርነት በተደረገው ውድድር ህወሓት 2 ሲያገኝ ኦህዴድ 108 ድምፅ ማግኘቱ የሚያሳየን አንድ ነገር አለ። ኦህዴድ ለህወሓትና ለድህዴን ዘርሮ አብላጫ ድምፅ ማግኘቱ በኢህአዴግ ውስጥ ትንሽ ተስፋ ያለው እሱ ብቻ መሆኑን ያሳያል። ህወሓት 2 ድምፅ ማግኘቱ ደግሞ በራሱ አባላት እንኳ ምን ያህል የተተፋ ድርጅት መሆኑ አጋጣሚው ግልፅ አድርጓል። አንዳንድ ሰዎች ህወሓት በትግራይ ድጋፍ ያለው ድርጅት ይመስላቸዋል። በክልላችን እውነተኛ የምርጫ ሂደት ተደርጎ ሓቀኛ ምርጫ ቢደረግ ህወሓት አሁን ከገኘው ድምፅ በላይ አያገኝም። ህወሓት በህዝቡም በራሱ አባላትም የተናቀና የተጠላ ድርጅት ነው። የህወሓት ምርኩዝ ጠበንጃ ብቻ ነው። ህወሓት በአደባባይ ውርደት ተከናንቦ በዝረራ መሸነፉ ትንሽ ተስፋ የነበራቸው ደጋፊዎቹ ስለሚያሳዝን እኛ( በትግራይ የስርአት ለውጥ ለማምጣት እየተታገልን ያለን) የምናደርገው ትግል እየሰፋና ስር እየሰደደ እንደሚሄድ ነባራዊ ሁኔታው ያረጋግጣልም ያሳያልም።
.
ዶክተር አብይ አህመድ አሊ 108 ድምፅ አገኘ ማለት ግን የኦሮሞ ህዝብ ፍላጎት ያሳያል ማለት አይደለም። አብይ የሚመራው ድርጅት አምባገነኑ ኢህአዴግ እስከሆነና መስመሩም አብዮታዊ ዲሞክራሲ እስከሆነ ድረስ የኦሮሞ ህዝብ ጥያቄ አይመለስም። የኦሮሞ ህዝብ ጥያቄ እውነተኛ ፍትህ፣ እውነተኛ ነፃነትና ዲሞክራሲ እንጂ የኦሮሞ ጨቋኝ ስልጣን ላይ ለማውጣት አይደለም። የኢትዮጵያ ህዝብ ጥያቄም ስር ነቀል የስርአት ለውጥ ነው። ስለሆነም የአብይ ውጤት ለጊዜው ለኦዴድ ደጋፊዎች የሚሰጠው ጊዝያዊ ተስፋ ካልሆነ በቀር በኢትዮጵያ የሚመልሰው ጥያቄ ስለሌለ የሚያመጣው ለውጥም የለም።
.
ኢህእዴግን የምንቃወም ሰዎች ደግሞ ጠባችን ከኢህአዴግ ሰዎች ሳይሆን ከሚከተሉት ርእዮተ-ዓለም ነው። አብዮታዊ ዲሞክራሲ ከሀገርና ከህዝብ በፊት ለመሪ ድርጅት ቅድሚያ የሚስጥ፤ በዲሞክራሲያዊ ማእከላዊነት ከላይ ወደታች ሀሳቡን የሚጭን፤ የይስሙላ ምርጫ የሚያደርግ፤ በመንግስትና በገዢ ድርጅት ያለው ድንበር የሚያፈርስ፤ ፖለቲካል-ኢኮኖሚው በድርጅት ካምፓኒዎች በሞኖፖል ይዞ ፍትሃዊ የገበያ ውድድርን የሚያጠፋ ርእዮተ አለም ነው። ስለዚህ ትግላችን ከአብይ መሀመድ ሳይሆን ከኢህአዴግ ርእዮተ ዓለም ነው። አብይ አህመድ የሚከተለው መስመር አብዮታዊ ዲሞክራሲ እስከሆነ ድረስ ትግላችን የአብይ መስመር ለመቀየር ያነጣጠረ ነው። ዶ.ር አብይ አህመድ በእህአዴግ እንጂ በህዝብ አልተመረጠም። ኦህዴድ ሆነ ሁሉም የኢህአዴግ ድርጅቶች በፍትሃዊና በነፃ ምርጫ አልተመረጡም። ስለሆነም ትግላችን በኢትዮጵያ እውነተኛ የህዝብ ምርጫ እንዲደረግ ስርነቀል የስርዓት ለውጥ ማካሄድ ነው።

Filed in: Amharic