>

ወያኔ እየተደናበረ ያለው በህዝባዊ አመፁ ሁለቱ የጥፋት አይኖቹ ስለወደሙበት ነው! (ግዮን ኢትዮጵያ)

ወያኔ አንድ ያላወቃት ሚስጥር ብትኖር የህዝቡን የነፃነት ጥያቄ ለማፈን ሲጀምር በቅድሚያ የሚያስረውና መደለያ ጉቦ ( እጅ መንሻ) የሚሰጠውም ለፖለቲካ አመራሮች ነበር።ይች አይነቷ የፖለቲካ ፍልስፍናው የሰራችው በ1997 እና በከፊልም በ2002 ዓ፡ም ነበር ነገር ግን በ2007 ዓ፡ም የተበላች እቁብ ሆና የነፃነት ትግሉ ወደ ህዝባዊ እንቢተኝነት ተቀየረና ትግሉ ሙሉ በሙሉ በሚባል ሁኔታ በህዝቡና በመላው አለም ተበትነው ባሉ ሀቀኛ የህዝብ ልጆች በሆኑ ጦማሪያኖች (አክቲቪስቶች) መቀጣጠል ጀመረ።በዚህ ምክንያት ወያኔ እድሜ ልክ በእስራት የፈረደባቸውን የፖለቲካ ልሂቃኖችንና ጋዜጠኞችን ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ በመፍታት ትግሉ በፖለቲካ መሪዎች እንዲመራ ፍቃዱን አሳዬ።ህዝቡም ይህ አይነቱ የወያኔ ሴራ ባይገለጥለትም እነዚህ የፖለቲካ እስረኞች ከተፈቱልኝማ እነሱ ይምሩኝ፣ብዙ ዋጋ ከፍለውልኛልና ማክበር አለብኝ አለና አጠቃላይ ህዝባዊ አቢዮቱን እርግፍ አድርጎ ጥሎ ቢያንስ ለመሪዎቼ ደህንነትና የፖለታካ መግባባት ሲል በመጠኑም ቢሆን ጋብ አለ።
ልብ በሉ ወያኔ ያልተገለጠለት እንቆቅልሽ እዚ ጋር ነው የሚጀምረው በእርግጥ ይህ እንደሚሆንም ስለሚያውቅ በጥናት የተደረገ የእስረኞች መፍታት ፕሮግራም ጭምር ነድፎም ሊሆን ቢችልም ያልታዬው አደጋ ግን አሁን በማያዳግም ሁኔታ ከፊቱ እየገሰገሰለት መምጣቱ ነው እሱም ከዚህ በኋላ ህዝቡ ያለመሪ ትግሉን ማቀጣጠል ስለሚፈልግ እነዚህ በየጊዜው በዎያኔ እየተያዙ ወደ ወህኔ ቤት ሊወረወሩ በሚችሉ መሪዎቹ ላይ እንብዛም አላፊነት መስጠቱን ጥሎ በራሱ ትግሉን ካቀጣጠለ በኋላና ለድል ከበቃ በኋላ የመሪነት ድርሻውን ለእነዚሁ ብዙ ዋጋ ሲከፍሉለት ለኖሩት ልጆቹ አሳልፎ ሊሰጥ የሚችል መሆኑን አለመገንዘቡን ነው።
አንድ ነገር ትዝ ያለኝ የዛሬ ሁለት ዓመት በህርዳር ላይ ህዝቡ የሰላማዊ ጥሪ ዘመቻ ሲያደርግ ሰመያዊ ፖርቲ እኔ ሰላማዊ ሰልፉን ልጥራው የሚል አቋም ያዘ ለመጥራትም ቆረጠ፣መግለጫ ሁሉ አወጣ በዚህ ጊዜ ህዝቡና አክቲቪስቱ እኔን ጨምሮ ለሰመያዊ ፖርቲ የአርፋችሁ ተቀመጡ፣ትግሉ የህዝብ ነውና ትግሉን እንዳታስቀለብሱት ከምታደርጉት የሰላማዊ ሰልፍ ጥሪ ተቆጠቡ በሚል ጮኸ፣ሁላችንም በዚሁ ጉዳይ ላይ ተረባርበን ሰመያዊ ፖርቲም የህዝብን ቃል አክብሮ ተቀመጠ ሰላማዊ ሰልፉም ተካሄደ የሰው ሂዎት ሁሉ እስከመጥፋት ደረሰ።በዚህ ሰላማዊ ሰልፍ ወቅት ሰመያዊ ፖርቲ ሰልፉን ጠርቶት ቢሆን ኖሮ የፖርታው አባላትና አመራሮች በጅምላ ወደ ወህኔ ቤት ይወረወሩና ትግሉን የመሪ አልባነት ካባ በማልበስ የተጀመረውን ህዝባዊ አመፅ አፈር ድሜ ወያኔ ያስገባው ነበር። ተወደደም ተጠላም አሁን የነፃነት ትግሉ ህዝባዊ መሰረት ስለያዘ ማንኛውም ምድራዊና ሰመያዊ ሃይል አያስቆመውም።ይልቁንም ወያኔ የሚያስራቸው የፖለቲካ መሪዎችና ታዋቂ ጋዜጠኞች ለህዝባዊ ትግሉ እንደ ገፊ ምክንያት ስለሚጠቅሙ በራሳቸው አቀጣጣይ አብሪ ጥይቶች ይሆናሉ እንጅ የሚከሽፉ አርቴፊሻል ጥይቶች አይሆኑም።
ከዚህ በኋላ ህዝብ ማድረግ አለበት ብዬ የማምነውና እኔም ልከተለው የምደፍረው የፖለቲካ ፍልስፍና ወያኔ ከእስር የፈታቸው ወንድሞቻችን እስካሁን የበኩላቸውን አላፊነት ተወጥተዋልና የነፃነት ትግሉን ራሱ ህዝቡ በመሰለው መልክ እንዲያደርገው አላፊነቱን ለባለ ድርሻው ሰፊው ህዝብ ሰጥተው እነሱ ግን አልፎ አልፎ ከህዝብ ፖለቲካዊ ድጋፍና የማማከር አገልግሎት እንዲሰጡ በክብር ከተጠዬቁ ይመልሳሉ እንጅ ወያኔ የህዝብ መሪዎችን በፈለገው ጊዜ እያሰረና እየፈታ ህዝባዊ የነፃነት ትግሉን እንዲያዳፍነው መፍቀድ የለባቸውም።
በጣም የገረመኝ አንድ ነገር አስቸኳይ አዋጁን አስመልክቶ የተከበሩ የመኢአድ ፕሬዜዳንት #አቶ_ማሙሸት_አማረ ለሕብር ሬዲዮ በሰጡት ቃለ መጠይቅ ወያኔ ከዚህ በኋላ ያስረኛል ብለህ ትገምታለሆይ ሲባሉ ይህ ጥያቄ የሚያሻማ ጥያቄ እንዳልሆነና ወያኔ ህዝብን በማዘናጋት ድጋሜ ሊያስራቸው እንደሚችል ተናግረው ነበር።እኔ #ነብዩ ፖለቲከኛ እያልኩ የምጠራው ማሙሸት አማራ የተናገረው ካፉ ጠብ ብሎ ሳይደርቅ ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ እነ እስክንድር፣እነ አንዱአለም፣እነ ተመስገንና ሌልች ከ10 በላይ ታስረው የተፈቱ የነበሩ ፖለቲከኞችና ጋዜጠኞች አረንጓዴ፣ቢጫ ቀይ ሰንደቅ አላማ ለብሳችኋል ተብለው ሲታሰሩ ሌሎች ደግሞ እነ ጋሻው መርሻ እና ሌሎች ከ10 በላይ ወጣቶች ባህር ዳር ላይ የአማራ ፖርቲ ልታቋቁሙ ነበር በሚል ስበብ ተይዘው ወደ ወህኔ ቤት ተወርውረዋል።
“ዘጠኝ ገዝቶ ዘጠኝ መሸጥ ትርፉ ዘጥ ዘጥ ነው። “ያሉት አበው እንደዚህ አይነቱን ውሃ ቅዳ ውሃ መልስ የፖለቲካ ቁማሩን አይነት ነው።ከዚህ በኋላ አዋጭ የሆነው ትግል የኢትዮጵያ ህዝብ ህዝባዊ አመፁን ምንም መሪ ሳያስፈልገው ማቀጣጠል ሲኖርበትና ሲኖርበት ብቻ ነው።ከዚህ በኋላ እኛም ለአፍታም አንተኛ ወያኔም ከተኛበት የዛፍ ላይ እንቅልፍ ለደቂቃ እንኳን አያንቀላፋም።ይህ ሁሉ ሆኖ እንኳን ወያኔም ከሚያንቀላፋበት የዛፍ ላይ እንቅልፍ ላይ መውደቁና ተኮታኩቶ መሞቱ አይቀርም እኛና ህዘባችንም በቅርብ ጊዜ ውስጥ የነፃነት ደጃፋችንን መርገጣችን ሳይታለም የተፈታ ሀቅ ነው።
Filed in: Amharic