>

አንዱአለም አራጌና እስክንድር ነጋ ማዕከላዊ የሚገኘውን ታዬ ደንደአን አነጋገሩት! (ሃና ረጋሳ)

“anii nagaa isiin akkamii???”

(በጣም ደህና ነኝ)

ከቀኑ 8ሰአት ላይ ብርቱውን ሰው ታዬ ደንደአን ለመጠየቅ ሶስተኛ ፖሊስ ጣቢያ ደጃፍ ላይ ደርሰናል።
ከበር መታወቂያ መታደሱን ለሚያጣራው ፌደራል ፓስፖርቴን ሰጠሁ እና አገላብጦ ካየው በኋላ “ማንን ለመጠየቅ ነው?” ሲል ጥያቄውን አስከተለ
“አቶ ታዬ ደንደአን”
አልኩት እና በመገረም ፈገግታ ታጅቦ ለጥቂት ደቂቃ ካስተዋለኝ በኋላ ፓስፖርቴን መለሰልኝ።
ይሄን ግዜ የለም ሊሉን ነው ወይስ መጠየቅ አትችሉም ልንባል ነው ብዬ አሰብኩ እና
“ምነው ??”
ስል ጠየኩት።
“አይ ገርሞኝ ነው እዚህ የሚመጣው በሙሉ ታዬን ነው የሚለው ገርሞኝ ነው ለማንኛውም እዛ ጋር ተመዝገቢ” ሲል ወደ ውስጥ እንድዘልቅ ጠቆመኝ።
ለመመዝገብ ወረፋ እየጠበቅን ሳለ ከኛ ፊትለፊት ጀርባውን ሰቶን እየተመዘገበ የሚገኝ ጎልማሳ ጥያቄ ይጠየቃል
“ስራ ???”
“የምን ስራ እኔ ስራ የለኝም”
ይሄ ለጡረታ ያልደረሰ ሙሉ ጤነኛ ሰው እንዴት ስራ የለኝም ይላል እያልኩ ስገረም ሲመዘገብ የነበረው ሰው ጨርሶ ለመፈተሽ ወደ አንድ ፌደራል ፖሊስ ሲቀርብ በድንጋጤ ክው አልኩ።
ለካ ያንን ቅፅ ሲሞላ የነበረው ብቅርቡ ከእስር የተለቀቀው ፖለቲከኛው አንዱአለም አራጌ ነበር።
እኛም ምዝገባችንን ጨርሰን ወደ መጠየቂያ ስፍራው ስንደርስ ሌላው ብርቱው ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ እና ከዚ ቀደም የፓርላማ አባል የነበሩት አቶ ግርማ ሰይፉ እንዲሁም የታዬ ባለቤት ወ/ሮ አለም ጋር ቆመው አገኘናቸው።
የአንዱአለም እና የእስክንድር ነጋ አድናቂ ስለሆንኩ ከዚ ቀደምም በአካል አግንቼቻው ስለ ማላውቅ ደስታዬ ወደር አልነበረውም እና የአክብሮት ሰላምታዬን አቅርቤ ታዬ እስኪመጣ መጠበቂያ ስፍራው ለይ ቆመን መጠበቅ ጀመርን።
በግምት ከአምስት ደቂቃ በኋላ ሲልቨር ከለር የቱታ ኮት እና ቀይ ቲሸርት በቀይ ቱታ ሱሪ በነጠላ ጫማ ተጫምቶ በሁለት ፖሊስ ታጅቦ መዝጊው ተከፍቶ ታዬ ብቅ አለ።
ከዚ ቀደም የነበረው ፈገግታው በእጥፍ ጨምሮ
ለሁላችንም ሰላምታ አቀርበ እና እነ እስክንድር ከኛ ስለቀደሙ እነሱ እስኪያወሩት እኛ ወደ ኋላ ቀረት አልን።
እነ አንዱለም አነጋግረውት ሲጨርሱ እኛ ለማናገር ቀረብነው።
“እንዴት ነህ ታዬ እየበረታህ ነው ??”
“ደህና ነኝ ምን እሆናለሁ የለመድኩት ነው እንደውም እዚ ፀሃይ የለ አቧራ የለ ተስማምቶኛል”
“አሁንም ትቀልዳለህ አይደል ፍርድ ቤት መቼ ትቀርባለህ????”
(ለጥቂት ሰከንድ ፈገግ አለና)
“ምን ላርግ ብለሽ ነው እስካሁን አላወኩም ሃና ይልቅ አዲሱን ደሞዝ ትመርቂያለሽ እያልኩ ልደውልልሽ እያሰብኩ እንዲህ ሆነ እንግዲህ”
(አጠገቡ አብረውት የቆሙ 4የሚሆኑ ፖሊሶች ንግግራችንን እየሰሙ ፊታቸውን አንዴ ፈካ አንዴ ጨምደድ ሲያረጉ ይታየኛል)
“እኔ እምልህ በምርመራ ወቀት ድብደባ ምናምን አለ እንዴ???”
“እስካሁን ምንም የለም ምንም የደረሰብኝ ድብደባም ሆነ የተለያየ ነገር የለም”
እንዲህ እና እንዲያ እያልን ከተጨዋወትን በኋላ እንዲህ አልኩት
“ምን ይምጣልህ ምን ያስፈልግሃል???”
ለጥቂት ሰከንድ ካሰበ በኋላ
“እኔ እዚህ ምንም ችግር የለብኝም ሁሉም የትተረፈረፈ ነው ግን ከተቻለ እዚህ ላሉ ልጆች ቱታ ብታመጡ መልካም ነው”
ሁሌም የሚገርመኝ ባህሪው ታዬ በቃኝን ማወቁ እና ማግበስበስ የማይወደው ባህሪው ነው ሁሌም ለኔ ብቻ አይልም ሌሎችንም ያስባል።
የመሔጃችንን ሰአት ፌደራሎቹ በግልምጫ ሲያስታውሱን አንድ የመጨረሻ ጥያቄ በኦሮምኛ እንዲህ ስል ጠየኩት።
“ummanii hundhuu waa’ee kee yaadaa jiraa eergaa qabdhaa??”
(ህዝብ በሙሉ በመታሰርህ ተጨንቋል መልእክት አለህ ወይ ለህዝቡ???”
“ያው እኔ ምንም መልእክት የለኝም እንዴት ናችሁ እኔ በጣም ደህና ነኝ አመሰግናለሁ”
(መምህር ስዩም ለፍርድ ቤት ቀጠሮ እየተሰናዳ ስለ ነበር ማግኘት አልቻልንም)

Filed in: Amharic