>
5:13 pm - Friday April 19, 7771

ስብሰባው እስኪያልቅ! (ደረጄ ደስታ)

እንደኛ እንደ ተራ ዜጎች፣ የተቃዋሚ መሪዎችም፣ አክቲቪስቶች፣ የሃይማኖትና የማህበራት መሪዎች በሙሉ ቁጭ ብለው ሰበር ጠቅላይ ሚኒስትር እየተጠባበቁ ይመስላል። መንግሥቶቹም እሚደግፉትን እኛም እምንቃወመውን ይህን ጠቅላይ ሚኒስትር በጉጉት እየተጠባበቅን እምንገኝ መስለናል። ሰዎቹም ይህን ያህል አምጠውና ልብ ሰቅለው እሚወልዱት ሰው “ውይ ለዚቹ ነው እንዴ…” ተብለው መሳቂያ ሊሆኑ መቻላቸው እንደሚያስጨንቃቸው አንስተውም። ችግሩ እኛ የደግፈነውን ሰው ካመጡብን ነው። ያው ኢህአዴግነቱ መቸም ያው ኢህአዴግ ነው ቢሆንም የኛው ኢህአዴግ ነው ልንል ይሆን? ወይስ የተመረጠልን ወይም የተመረጠብን ይህ ሰው እኔን የመረጠኝ ህዝቡ እንጂ ኢህአዴግ አይደለም ይለናል። ስላልሆነም ድርጅቱ ህዝቡን እንጂ ህዝቡ ድርጅቱን እንዲከተለው አልፈቅድም ይል ይሆን? አሁን አብይ ወይም ለማ ቢመረጡ በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ሥልጣን ከህወሓቱ ኢህአዴግ ወደ ኦህዴዱ ኢህአዴግ በሰላማዊ መንገድ ተሸጋገረ እንባል ይሆን? አብይና ለማስ ቢሆኑ በሉ እንግዲህ ኮማንድ ፖስቱም አመጹም ያውላችሁ አሁን መሪዎች ስለሆናችሁ እንደፍርጥርጣችሁ አድርጉት ቢባሉ ምኑን ከምን ያደርጉታል? እኛስ በእንዴት ያለ ምላስ እንቀበላቸዋለን?… ያሁኑን አሻንጉሊት ለየት እሚያደርገው ኦሮምኛ ተናጋሪ መሆኑ ነው …ድሮም ህዝቡን ሲያታልሉ ነው እንጂ ….እያልን ልቀንጥል ይሆን? ለመሆኑ ሊባሉ እሚችሉት ነገር ይታየናል? ፍጹም ሊሆን እማይችል ነው ብለን ለማጣጣል ሳይሆን ኢአህዴጎቹ መቸም ደመቀና ሽጉጤን እንኳን ለጠቅላይ ሚኒስትርነት፣ በቁመናቸው ሰዎች ናቸው ብለው ሰው ፊት እንደማያቀርቧቸው እናምናለን። ደብረጽዮንንም ቢሆን መቸም እነሱም ሲጀመር ከሰው አልቆጠሩትም፣ ሽኩቻ የበዛበትን የህወሓት ሥልጣንን ምንም ሊያደርገው ስለማይችል እኛ እስከምንስማማ እሱ ይዞልን ይቆይ የተባለ አደራ ጠበቂ መሆኑን እናውቃለን። አድርባይ እንጂ ሰው ከማይወጣለት ኢህአዴግ ግን እሚመረጥ ይጠፋል ብለን አንጃጃልም። እንዲያውም ሰበር ዜናቸው እንደሱ ያለ ነገር ሊሆን ይችላል። ከጥሩ አድርባዮች መካከል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ እነ ወርቅነህ ገበየሁም ታሳቢ ሊሆኑ እማይችሉበት ምክንያት የለም።
ወርነቅነህም ሆነ ጨርቅነህ ቢመረጥ ግን ከህወሃት ራስ እሚወርድ አንድም ሰው አይኖርም። ምክያቱም ሁሉንም ነገር ከራስ ጀምሮ ቢመለከቱት ጥሩ ነው። ከዚህ ሁሉ ግን ራስ ወያኔን ማየት ብቻ ሳይሆን እኛንስ የሚመሩን ተቃዋሚ ራሶች የት አሉ ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው።  ከኛ ጋር ቁጭብለው ኢህአዴግቹ ማንንም የዝንጀሮ ቆንጆ ሲያማርጡ፣ ያ ቢሆን ይህ ቢሆን …እሚል ትንተና ሲሰጡም ሆነ ሲያደምጡ መኖር ጥሩ ራስነት አይደለም። ራስንም ማየት አንዳንዴ ደግ ነገር ነው። ደክመዋል ወድቀዋል የተባሉት ራሳችን ላይ እየተመላለሱ ሲጠጋገኑ ማየት ራስ እሚያዞር ነገር ነው። የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ አልቆላቸዋል ማለቱም ስትራቴጂ አይደለም። አዎ ሰዎቹ አርጅተውም ጃጅተውም ያልቃሉ። ዝምብሎ እድሜ ልክ ፣  “የጊዜ ጉዳይ ነው” እያሉ ማዝገም ሰበር እውቀት አይደለም። ይታወቃል ነገሮች በጊዜያቸው እንደሚፈጸሙ ግልጽ ነው። በፖለቲካ አግባብ ግን የነገሮችን ጊዜ እሚያሳጥሩትና እሚያረዝሙት ሰዎች ናቸው። ዋናው ስጋት ከሚገባው በላይ ቆይተዋል ብቻ ሳይሆን አሁንም ሊቆዩ ይችላሉ እሚለው ነው። ከእነዚህ ጋር አንዷም ቀን የዘለዓለም ስቃይ ናት። አንዳንዴማ ሲያስቡት አርጅተው እንኳ እሚሞቱ አይመስሉም። አስተውላችሁ ከሆነ ከመለስ ሞት ሌላ አንዳቸው እንኳ ሲሞቱ አንመለከትም። ምክንያቱም ሰዎቹ ራሳቸው በሽታ ሳይሆኑ አይቀሩም። በሽታ ደግሞ ይገድላል እንጂ አይሞትም። መድሃኒት እስኪገኝለት ድረስ!! ስለዚህ እንዲህ አገሩን ከሞላው ተቃዋሚ ዶክተር ይህን በሽታ እሚገድል መድሃኒት እሚያውቅ አንድ ዶክተር እንዴት ይጠፋል ብሎ መጫወቱ አይከፋም። ሰዎቹ ስብሰባቸውን እስኪጨርሱ ድረስ ከገዛ ሀሳብ ጋር መጫወት ይጠቅማል! ከዚያ በኋላማ አጀንዳ ስለሚወረወርልን ቢዚ ነን።
Filed in: Amharic