>

የዕውቁ አዝማሪ ሐሰን አማኑ ግጥሞች ስለ ዐጼ ቴዎድሮስ፤ (ውብሸት ሙላት)

ለዛሬ ደግሞ የመይሳውን ልጅ በሐሰን አማኑ ግጥሞች እናወድሳለን!!! ስለ ሐስን አማኑ አንስተን ከዚያ ወደ ዐጼ ቴዎድሮስ!
ሐሰን አማኑ ወሎዬ ናቸው፡፡ ማየት የተሳናቸውም ናቸው፡፡ ስለእሳቸው የተጻፉ መረጃ እስካሁን አላገኘሁም፤ ከግጥሞቻቸው በስተቀር፡፡ ከግጥሞቻቸው በመነሳት ምናልባትም የአዝማሪነት ሕይወታቸው በዐጼ ቴዎድሮስ ጊዜ የጀምረ  ይመስላል፡፡ በእርግጠኝነት የሚታወቀው ግን በዐጼ ዮሐንስ፣በንጉሥ ሚካኤል፣በዐጼ ምኒልክም  ዘመን የነበሩ፣በቤተ መንግሥትም ዘንድ የተወደዱ መሆናቸው ነው፡፡እስከ ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ዘመን ድረስም  እንደነበሩ ይነገራል፡፡ በአድዋ ጦርነትም ጊዜ አብረው ዘምተዋል፡፡ (ከጉዞ አድዋ ተጓዦ መካከልም አንድኛው የዚህ ዓመት ጀግናው እኒሁ ሐሰን አማኑ መሆናቸውን መግለጹን በቴሌቪዥን ዐይተናል!)
ሐሰን አማኑ  በመሳፍንቱም፣ በነገሥታቱም እጅግ የታወቁ እና የተከበሩ አዝማሪ ነበሩ፡፡ በዋናነት የንጉሥ ሚካኤል አዝማሪ ቢሆኑም በዐጼ ዮሐንስም በዐጼ ምኒልክም ዘንድ እንዲሁ ተወዳጅ ነበሩ፡፡ እንደ ሌሎች አዝማሪዎች ሁሉ ሐሰን አማኑም በሰላሙ ጊዜ ያዝናናሉ፤በጦርነትም ጊዜ ያበረታታሉ፣የጀግንነት ሥራ የፈጸሙትንም ያሞግሳሉ፣በሞት ጊዜም ያጽናናሉ፡፡
በመጽሐፍ ውስጥ ከተገኙት ብቻ እንኳን ብንወስድ ሐሰን አማኑ ስለ ብዙ ጀግኖች ውዳሴ አቅርበዋል፡፡  ስለ ዐጼ ቴዎድሮስ፣ ዐጼ ዮሐንስ፣ዐጼ ምኒልክ፣ ራስ ዳርጌ፣ልዑል ራስ መኮንን፣ራስ ተሰማ፣ደጃዝማች ባልቻ፣ፊታውራሪ ገበየሁ፣ፊታውራሪ ገበየሁ፣ራስ ጎበና፣ንጉሥ ሚካኤል በጣም ጥቂቶቹ ናቸው፡፡
ሐሰን አማኑ ሌላውን ለማዝናናት በራሰቸውም ላይ ቢሆን ይቀልዳሉ፡፡  በዚህ አኳኋን ካቀረቧቸው አዝናኝ ጨዋታዎች መካከል የሚከተለው ድርጊታቸው አስረጂ ነው፡፡
በአንድ ወቅት እንዲህ ይሆናል፡፡ በወሎው ባለ አልጋ፣በመሐመድ አሊ (የኋላው ንጉሥ ሚካኤል) እና በዛን ጊዜው ንጉሥ ምኒልክ መካከል ጦርነት ይነሳል፡፡ ምክንያቱ ደግሞ የወረኢሉ መቃጠል ነው፡፡ ወረኢሉን ንጉሥ ሚካኤል ያቃጥሏታል፡፡ ምኒልክም እነ ደጃች ውቤን ይልካሉ፡፡ ዉጊያም ይጀመርና የንጉሥ ሚካኤል ወታደሮች ወደ ደሴ አቅራቢያ ያፈገፍጋሉ፡፡
እነደጃች ውቤም አገር አማን ብለው ይቶ መድኀኒ አለም በሚባል  አካባቢ (ከደሴ በስተምእራብ በግምት 10 ኪ.ሜ.) ላይ ፈረሶቻውን አሳርፈው እረፍት ያደርጋሉ፡፡ በዚህን ጊዜ የንጉሥ ሚካኤል ሰዎች ይደርሱና ሁሉንም ይማርኳቸዋል፡፡  ምርኮኞቹም ተይዘው ወደ ደሴ እየሄዱ ሳለ ገራዶን ጨርሰው ጉዳሞ የሚባል ወደሩጋ መገንጠያ ላይ ሲደርሱ ሐሰን አማኑ እየተመሩ መንገድ ላይ ነበሩ እና የትርምስምሱን ምንነት መሪያቸውን ሲጠይቁ የሆነውን ሁሉ ይሰማሉ፡፡
በዚህን ጊዜ ከተማረኩት መካከል አንዱን እንዲሰጣቸው ይጠይቃሉ፡፡ ኋላ ደሴ ላይ ንጉሥ ሚካኤል ሰዎቻቸውን ግብር እያበሉ ሳለ ሐሰን አማኑ እንዲህ በማለት እየፎከሩ ምርኮኛውን አስረከቡ አሉ፡-
“እውሩ ሁሉ ሲል ደንበር ደንበር፣
ሐሰን አማኑ ጉዳሞ ገዳይ ከሩጋ ድንበር፡፡”
ሐሰን አማኑ ስለ ዐጼ ቴዎድሮስ ከገጠሟቸው ውስጥ የሚከተሉትን እናገኛለን፡፡
“መቼ ሞተና መቼ ተረሳ፣
መቅደላ ያለው የቋራው ካሳ፡፡
የቋራው ካሳ ልበልኽ አንዴ፣
የለኽም ዘመድ ያለጎራዴ፡፡
አንሡ ካላችሁ እናንሳ ወንድ፣
የቋራው ካሳ አባ ሞገድ፡፡”
(ግጥሞቻቸውን ወስደው የጻፉ ሰዎች እንኳን ስለ ሐሰን አማኑ ማንነት አንድ መስመር ጽሑፍም ቢሆን አልተቸሯቸውም፡፡ ሐሰን አማኑንም አንረሳቸውም!!! )
ማጣቀሻ፡-
ጎበዜ ጣፈጠ፣አባ ጤና ኢያሱ፣Addis Ababa/Paris,1996.
ብላቴን ጌታ ማኅተመ ሥላሴ ወልደ መስቀል፣ዝክረ ነገር፣አዲስ አበባ፣1962፡፡
Fitz-Hardinge Berkley, The Campaign of Adowa and the Rise of Menelik, London 1902.
#Yared Shumete
#Nafkot Yosef
#Hassen Amanu
Filed in: Amharic