>

ኃይሌ ሆይ! ሜዳሊያ ብቻ ሳይሆን ዝምታም ወርቅ ነው። (ሳምሶን አስፋው)

ኃይሌ ገብረሥላሴን ባስበው ባስበው አልገባ አለኝ፦ ምን አጥቶ ነው ? ምን ፈልጎ ነው? ወይም ምን አልፈልጎ ነው?ከህዝብ ጋር የሚያጣለውን ነገር እየተናገረ ለዘመናት በእግሩ ሮጦ የገነባውን ክብርና ዝና፤ በ5 ደቂቃ ንግግር በተደጋጋሚ አፈር የሚያስገባበት ምክንያት ምን እንደሆነ በፍጹም ሊገባኝ አልቻለም።

ሃብት ፈልጎ ነው እንዳልል ለራሱ ቀርቶ ለዘር ማንዘሩ የሚበቃው በአንጡራ እግሮቹ ያፈራው አንጡራ ሃብትና ንብረት አለው፡፤ ክብርና ዝና ፈልጎ እንዳልል፤ እንደሱ ክብርና ዝና ያላቸው ሰዎች እንኳን በኢትዮጵያ በዓለማችንም ላይ በጣት የሚቆጠሩ ናቸው። ሥልጣን ፈልጎ ነው እንዳልል፤ በፖለቲካው መስመር ላይ የለም ፡፡ በሙስና ብላክ ሜል ተደርጎ ነው እንዳይባል፤ ራሱ ጉቦ ሰጭ መሆኑን እንጂ ተቀባይ ሲሆን አልሰማንም። ለሃብቱ የወያኔን ዋስትና ፈልጎ ነው እንዳይባል’ እንደሱ ብዙ ገንዘብ አፍሰው ስራ የሚሰሩ ባለሃብት አትሌቶች ምነው ትንፍሽ አይሉ?

ታዲያ ምንድነው ምክንያቱ? እንቆቅልሽ አይደለም ትላላችሁ?

መካሪ ወይ አማካሪ የለውምን የሚለው የጋዜጠኛ ሲሳይ አጌና ጥያቄ የብዙዎቻችን ጥያቄ ይመስለኛል።

አብዛኛው የዘመኑ ተቃዋሚ በዘር ፖለቲካ ፍቅር ተለክፎ ባንዲራችንን ችላ ባለበት ከ15 እና 20 አመት በፊት ፤
ዘር compulsory ኢትዮጵያዊነት ግን optinal በነበረበት በዚያ ዘመን፤ ኃይሌ ከአንዱ አለም ጥግ ሌላው አለም ጥግ ብቻውን ሮጦ የተረሳቺውን ባንዲራ ከፍ አድርጎ አውለበለበ።

የደበዘዘውን ኢትዮጵያዊነት አድምቆ በኢትዮጵያዊ ልብ ውስጥ የክብር ኃውልት ተከለ፡፤ (በተለይ በ 2000 የሲዲኒ ኦሎምፒክ በ10 000 ሜትር ሩጫ ፍጻሜ ከኬኒያዊው ፓውሎ ቴርጋት ጋር ያደረገው የመጨረሻ ትንንቅ አውስትራሊያ ለነበረው ኢትዮጵያዊ ልዩ ትዝታ ነበረው)።

ታዲያ “ሰው ማለት፤ ሰው የሚሆን ሰው ሰው የጠፋለት” እንዲሉ ኢትዮጵያ አስታዋሽ ልጅ ባጣችበት ወቅት አለሁልሽ ያላት ይሄ ሰው፦ ዛሬ በተገላቢጦሽ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ልጅቿዋ፤ ከስህተታቸው ተምረው፤ አንድ ሆነው፤ አለንልሽ ኢትዮጵያ ሲሏት፤ ለ27 አመታት ያደከማት “ወያኔ” የተሰኘ ነቀርሳ መሆኑን አውቀው፟›- መድሃኒቱን ፍለጋ ዳር እስከዳር በተነሱበት በዚህ ወቅት የክፉ ቀን ልጅዋ የነበረው ኃይሌ ገብረሥላሴ ከነቀርሳው ከወያኔ ወግኖ ስቃይዋን የሚራዝም አቋም የያዘበት ምክንያት ባስበው ባስበው አልገባ ብሎኛል።

ሮጦ ባሸነፈ ቁጥር መሸለሚያ ማማው ላይ ቆሞ ሰንደቅ ዓላማችን በብሄራዊ መዝሙር ታጅባ ከፍ ከፍ ስትል ያነባላት ያቺ ኢትዮጵያ ዛሬ 100 ሚሊዮን ልጆቿ የሚያለቅሱባት ኢትዮጵያ አይደለች ይሆን? በሷ አልደራደርም ያለን የትኛዋን ኢትዮጵያ ይሆን?

እግሮቹ የሃገር መኩሪያ አንደበቱ የሃገር ማፈሪያ ሆነብን። እግሩን ነጥለን አናከብር ነገር ቸገረን እኮ…በለፈለፉ በአፍ ይጠፉ…ይሏል ይህ ነው። ኃይሌ ሆይ! ሜዳሊያ ብቻ ሳይሆን ዝምታም ወርቅ ነው ።

Filed in: Amharic