ODF : ለአንድ አማራ አስተባባሪ ግብረ ኃይል
የአማራ ወገኖቻችን “አንድ አማራ” በሚል ስም መደራጀት አገር ዉስጥ በሕዝባችን መካከል የተጀመረዉን አብሮ መቆም የበለጠ ለማጠናከር ብሎም “ትግልህ ትግሌ”፣ “ደምህ ደሜ”፣ “ድልህ ድሌ”፣ የተባባለዉ የአማራ እና የኦሮሞ ሕዝብ በዘላቂነት አብሮ እንዲቆምና የጋራ አገሩን በጠንካራ ዲሞክራሲያዊ መሠረት ላይ እንደ አዲስ ለመገንባት እንዲችል ያደርገዋል። የአማራን መደራጀት አስፈላጊነት እንደ የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ግንባር የፀና አቋም ወስደን በተለያዩ መድረኮች ስንገልፅ የቆየነዉም የሁለቱ ሕዝብ በተደራጀ መልክ አብሮ መቆምና ለሌሎችም የአገራችን ብሔር-ብሔረሰቦች አብሮነት ምሣሌ ሆኖ መገኘት ለጊዜያዊ የፖለቲካ ትርፍ ሣይሆን ዘላቂ ለሆነ የአገር ህልዉና እጅግ በጣም አስፈላጊ መሆኑን ስለምናምን ነዉ።የአማራ ወገኖቻችንን “አንድ አማራ” በሚል ስም መደራጀት ከልብ የምንደግፈዉ ለተባበረ ህዝባዊ ትግል ከሚፈለገዉ ግብ መድረስ ከሚያደርገው አስተዋጽኦ አንፃር ብቻም ሳይሆን ድርጅቱ ተጠናክሮና በሁሉም መስክ ጎልብቶ ለዚህ ተሟጋች ላጣ ህዝብ ድምፅና ጋሻ እንደሚሆን በመተማመን ነው። ጠቅለል ባለ አገላለፅ በአማራነት መደራጀታችሁ የተያያዝነዉን ትግል በድል ለመደምደም ብሎም ለወደፊቱ የአገር ግንባታ ጥረታችን ዘርፈ-ብዙ ጠቀሜታ እንደሚኖረዉ እርግጠኞች ነን፡፡
በዚህም መሠረት በመሥራች ስብሰባችሁ ላይ እንድንገኝ ያደረጋችሁልንን ጥሪ በደስታ መቀበላችንንና ተወካዮቻችንን የምንልክ መሆናችንን እየገለፅን ጅምራችሁ ዉጤታማ እንዲሆን ለማድረግ የድርጅታችን ትብብር እንደማይለያችሁ እናረጋግጣለን።
የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ግንባር #ODF