>
5:13 pm - Friday April 19, 3686

የወቅታዊ  ተግባራዊ ትግል (ወተት) መልዕክት: በግልጽ ጦርነት ውስጥ ካልሆን በህቡዕ ጦርነት እንሳተፍ! (ዶ/ር ታደሰ ብሩ)

(ክፍል 2)
እያንዳንዱ ነፃነት ናፋቂ ኢትዮጵያዊ ሊሳተፍባቸው ከሚችሉ የህቡዕ ጦርነት ስልቶች ውስጥ አሻጥር፣ የስነ-ልቦና ጦርነት፣ የኢኮኖሚ ጦርነት፣ እና ኢህአዴግን እርስበርሱ ማናከስ የተባሉት ለአብነት እንደማቀርብ ቃል ገብቼ የመጀመሪያው ክፍል አሻጥር በክፍል 1  አቅርቤዓለሁ፤ ይህ ክፍል 2  ደግሞ በስነልቦና ጦርነት ላይ ያተኩራል።
ለ. የስነ-ልቦና ጦርነት  –  ትላልቅ ጦርነቶች የሚካሄዱት በሰዎች ጭንቅላት ውስጥ ነው። ማንኛውንም ፍልሚያ ለማሸነፍ አንተ በተረጋጋ የአዕምሮ ሁኔታ ላይ መገኘት ይኖርብሃል፤ መረጋጋትህ ሁኔታዎችን በቁጥጥር ስር ያደረግሀቸው መምሰል አለበት፤ በአንፃሩ ተፋላሚህ ደግሞ መዋከብና መደንገጥ ይኖርበታል። የጠላትህ መዋከብ የህቡዕ ጦርነት ግብ ነው። አምባገነን ሥርዓትን ማሸነፍ የሚቻለው የሥርዓቱ አራማጆች ወደ እብደት የተጠጋ የስነልቦና ቀውስ ውስጥ ሲገቡ ነው፤ ያኔ ውሳኔዎቻቸው ሁሉ የጭንቀት ይሆንና በስህተት ላይ ስህተት ይጨምራሉ፤ ከጭንቀት ብዛት የራሳቸውን ወዳጆች ሳይቀር ያጠፋሉ።
የስነልቦና ጦርነት በተለያዩ መንገዶች ሥራ ላይ ማዋል ይቻላል። በጦርነቶች ውስጥ ፉከራ፣ ሽለላ፣ ቀረርቶ፣ ሰልፍ የሚደረገው ወዳጅን ለማጀገንና ጠላትን ለማሸማቀቅ ነው። ከዚህ በተጨማሪ በሬድዮ፣ በቴሌቪዥን፣ በበራሪ ወረቀቶች፣ ከሰው ወደሰው በሚተላለፊ ወሬዎችና አሉባልታዎች አማካይነት በሚላኩ መረጃዎችና ማሳሳቻዎች አማካይነት ከፍተኛ የመረጃ ጦርነት (Information warafre) ይካሄዳል። [ወደፊት የመረጃ ጦርነትን ለብቻው እናየው ይሆናል]
በዚህ ጽሁፍ ላተኩር የፈለግሁት በቀላሉ ተግባራዊ ልናደርጋቸው የምንችላቸው “ማግለል”፣ “ማድነቅ” እና “ማብራራት” ብዬ የጠራኋቸው ሶስት የስነልቦና ጦርነት ስልቶችን ነው።
ማግለል –  የህወሓት፣ የብአዴን፣ የኦህዴድና የደህዴግ እንዲሁ የአጋር ድርጅቶች ቀንደኛ አባላትን፤ ግፈኛ የፌደራል ፓሊስ አባላትን፣ በየመንደሩ እያነፈነፉ ያሉት ጆሮ ጠቢዎችን፣ ጭንቅላት የለሽ ፓሊሶችን፣ ፍርደ ገምድል ዳኞችን፣ ሀሰተኛ አቃቢያነ ህግ፣ ካድሬ መምህራንን፣ የመንደር ለፍላፊ ካድሬዎችን ማግለል፣ መጠየፍ፣ ማራቅ፣ መናቅ፣ ማዋረድ በቀላሉ ተግባራዊ ሊደረግ የሚችል ከፍተኛ ውጤት ሊያመጣ የሚችል ተግባር ነው። በተለይ ጆሮ ጠቢዎችንና ገራፊዎችን ማጋለጥ፣ ፎቶግራፎቻቸውን በማኅበራዊ ሚዲያ መበተን፤ በእነሱ ላይ ማፌዝ፤ ድንቁርናቸውን፣ ሆዳምነታቸውንና ዘረኝነታቸውን የሚገልፁ የቅሌት ስሞችን ማውጣት እና ማሰራጨት ወደ እብደት ሊመራቸው ይችላል። ማግለልን ተግባራዊ ለማድረግ “ጨዋ” ለመሆን መሞከር አያስፈልግም። ማንኛውም ዜጋ ከውሸታም፣ ሆዳምና ደንቆሮ ጋር አብሬ አለመዋል መብቱ ነው። ከትንሽ ሰው ጋር መዋል ያሳንሳል፤ በዛሬዋ የኢትዮጵያ ተጨባጭ ሁኔታ የህወሓት አገልጋይ መሆንን ያህል ትንሽነት የለም። ከዚህ አንፃር ሲታይ የህወሓት ሰዎችን ማግለል መብት ብቻ  ሳይሆን ብልህነትም ነው።
ማድነቅን  –  ለነፃነት ሲሉ ዋጋ የከፈሉ እና እየከፈሉ ያሉ ዜጎችን ማድነቅ፤ አርዓያነታቸውን ማጉላት፤ ማበረታታት፤ ሁለተናዊ ድጋፍ መስጠት። ከታጋዮች መካከል ጀግኖችን ማውጣት። በእስር ላይ የሚገኙ የህሊና እስረኞችን መዘከር፤ ማወደስ፤ ማበረታታት፤ ቤተሰቦታቸውን መደገፍ። በትጥቅ ትግል የተሰለፉ ወገኖችን መደገፍና ማበረታት፤ የሕዝባዊ አመጽ ጀግኖችን ማውጣት። በትጥቅ ባልተደገፈ ሕዝባዊ እምቢተኝነት ሥርዓቱን እየተገዳደሩ ያሉ ወገኞችንም መደገፍ፣ ማበረታት፤ የሕዝባዊ እምቢተኝነት ጀግኖችን ማውጣት።
ማብራራት – የሥርዓቱ አገልጋዮች አድርባይነት ከዚያም አልፎ ወንጀለኝነት በማስረጃዎች አስደግፎ ይፋ ማድረግ። ስለ ሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች፤ ሰለ ሀብት ዘረፋ፣ ስለ ሙስናን፣ ስለ መሬት ቅርምት፣ የባለስልጣኖች ሀብት ማሸሽን በሀሪቱ ከተንሰራፋው እና እያደገ ከመጣው ድህነት ጋር እያነፃፀሩ ማቅረብ። አስከፊ ስለሆነው የእስረኞች አያያዝ በሀቅ ላይ የተመሰረቱ ጽሁፎችን በጋዜጦች፣ ሬድዮና ቴሌቪዥኖች መሰል መገናኛ ብዙሀን እንዲሰራጭ ማድረግ። ሥርዓት በያዘ ጨዋ ሙግትና ተጨባጭ ማስረጃዎች ሥርዓቱን እርቃኑን ማስቀረት።
Filed in: Amharic