>

ስህተትን በስህተት በማረም የተሄደበት ረዥም መንገድ! (ዳዊት ከበደ ወየሳ)

ማንም ሰው ስህተት ይሰራል። ነገር ግን መሳሳቱን ሲያውቅ፤ ከስህተቱ ተምሮ እና ያስቀየመውን ሰው ‘ይቅር በለኝ’ ብሎ ወደፊት ይራመዳል እንጂ፤ ስህተትን በስህተት እያረመ አይሄድም። ኢህአዴግ እና ተከታዮቹ፤ ከሚሰሩት ስህተት የበለጠ፤ ስህተትን በስህተት ለማረም የሚወስዱት እርምጃ፤ ህዝብን ለሞት እየዳረገ እና ሃገርን ቁልቁል እየናደ በመሄድ ላይ ይገኛል። በተለይም የዝቅተኝነት ስሜት ውስጥ የሚናውዝ ግለሰብ፤ ወይም “የኔ ዘር ዝቅተኛ ነው!” ብሎ የሚያስብ ባተሌ፤ ጠመንጃ እና ስልጣን በሚይዝበት ወቅት፤ እራሱን የበላይ ለማድረግ፤ በጥላቻ ህሊናው እየተመራ እጁን በንጹሃን ደም ይታጠባል። በዚህ ሁሉ ስህተት መሃል ግን… ከስህተቶች ሁሉ የበለጠው ስህተት፤ ስህተትን በስህተት ለማረም የሚደረገው ሌላ ስህተት ነው።

ስህተትን በስህተት በማረም የተሄደበት ረዥም መንገድ! (ዳዊት ከበደ ወየሳ)

 የኢህአዴግ ስህተት የሚጀምረው፤ እንደሰነፍ ተማሪ በስህተት ላይ ስህተት በመደመር ነው። ገና በጠዋቱ… የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማ ሲያዋርድ እና ሲቀይረው፤ የህዝቡን አንድነት በነገድ ዘር ሲመነዝረው፤ የኢትዮጵያዊያንን ነጻነት ዝቅ ሲያደርገው፤ የብዙ ሺህ አመት የታሪክ ባለቤትነቷን ሲያኮስሰው… ከዚያ ነው የኢህአዴግ ስህተት የሚጀምረው። ሁሉንም ዘርዝረን አንዘልቀውም። ኢህአዴጋውያን በነዚህ የስህተት መንገዶች ደጋግመው ተመላልሰውባቸዋል። የኢትዮጵያን ሰንደቅ አላማ “ጨርቅ” ብሎ የሚጀምረው ስላቅ፤ ሰንደቅ አላማው በአንዳንድ ክልሎች እንዳይውለበለብ ጭምር የራሱን አስተዋጽኦ አድርጎ አልፏል። በተለይ በሱማልያ እና በኦሮሚያ የኢትዮጵያ ሰንደቅ አላማ ከተሰቀለበት እንዲወርድ ብቻ ሳይሆን እንዲዋረድ ሲደረግ የታሪክ ምስክር ሆነን አይተን አዝነናል።

ኢትዮጵያ ታላቅ ታሪክ ያላት አገር ሆና ሳለ፤ ታሪኳን በሚያኮስስ ሁኔታ፤ የኢትዮጵያን ታሪክ የመቶ እና የሁለት መቶ አመት ታሪክ አድርገው ይመነዝሩታል። ሺህ አመታት ወደኋላ ቆጥረን ስለአክሱም እና ዛጉዌ ስርወ መንግስት ማውራት ስንጀምር፤ የአክሱም እና የንግሥተ ሳባን ታሪክ የትግራይ ህዝብ ታሪክ ብቻ በማድረግ፤ “የአክሱም ሃውልት ለወላይታው ምኑ ነው?” ሲሉ ሟቹ ጠቅላይ ሚንስትር አቶ መለስ ዜናዊ ጭምር ይሳለቁብናል። ጎበዝ የጋራ ታሪክ ብቻ ሳይሆን፤ የጋራ አገር እንዳይኖረን ለብዙ አመታት ብዙ ስራ ተሰርቷል። 

የጋራ አገር እንዳይኖረን ለማድረግ ደግሞ፤ ስሌቱ ቀላል ነው። በዘር የተደራጁ ትናንሽ እና ትላልቅ የብሄር ድርጅቶችን ማቋቋም፤ እነሱንም እርስ በርስ እያጣሉ በስልጣን ላይ መቆየት፤ እስከመገንጠል ድረስ ያላቸውንም መብት በህገ መንግስት ላይ አስፍሮ፤ የሚገነጠሉበትን ቀን በናፍቆት መጠበቅ – የኢህአዴግ ድብቅ እውነት፣ ግልጽ ስህተት ነው። 

በመረጃ እና በምሳሌ መነጋገር ካስፈለገ፤ የኦሮሞን ህዝብ ጉዳይ እዚህ ላይ ማንሳት ይቻላል። በኢትዮጵያዊነቱ ከፍተኛ ኩራት ብቻ ሳይሆን፤ ታላቅ መስዋዕትነትን የከፈለውን የኦሮሞ ህዝብ፤ ክብር እና ዝናውን ዝቅ አድርጎ እንዲመለከት “ነፍጠኛ አማራ ሲገልህ ነበር፤ እንደሰው አያዩህም ነበር!” የሚል ስብከት በተደጋጋሚ እንዲመገብ አደረጉት። የኦሮሞ ህዝብ… የአገሪቱ ኦፊሴል ቋንቋ የሆነውን የአማርኛ ቋንቋ እንዳይጠቀም ፊደሉንም እንዳይማር አበረታተዋል፤ ተፈጻሚም አድርግዋል። በውጤቱም… ዛሬ ላይ አማርኛ የማይናገር፣ የማይሰማ፤ አማርኛ የማይጽፍ፣ የማያነብ አንድ ትውልድ አፍርተዋል። ይሄ የኦሮሞን ህዝብ ከሌላው ኢትዮጵያዊ ለመነጠል ሆን ተብሎ የተሰራ፤ የስህተቶች ሁሉ ስህተት ነው። ይሄንን መናገር የጀመርነው ዛሬ አይደለም። ደግመን ደጋግመን ላለፉት ሃያ ምናምን አመታት ተናግረነዋል፤ አሁንም እንደግመዋለን።

በመጪው ዘመን… የኦሮሞ ህዝብ በኢትዮጵያ ጉዳይ ተሳታፊ እንዳይሆን ለማድረግ፤ ከሌላው ኢትዮጵያዊ ጋር የጋራ ቋንቋ፣ የጋራ ፊደል፣ የጋራ ሰንደቅ አላማ፣ የጋራ ጀግና፣ የጋራ ታሪክ እንዳይኖረው… በውጤቱም የጋራ አገር እንዳይኖረው ከሽግግር መንግስቱ ግዜ ጀምሮ፤ ህወሃት  ሳያቋርጥ ሲሰራበት የቆየ ጉዳይ ነው። ሌላው ቀርቶ… የኦሮሞ ህዝብ ከሌላው ኢትዮጵያዊ ጋር የጋራ ሰንደቅ አላማ እንዳይኖረው፤ አባቶቻችን ለመላው ኢትዮጵያዊ የሞቱለትን አረንጓዴ፣ ቢጫ እና ቀይ ባንዲራ እንዲጠላው ለማድረግ የማያቋርጥ ኢህአዴጋዊ ፕሮፓጋንዳ ተካሂዷል። በኋላ ላይ ይህንን ስህተት ለማረም ሌላ ስህተት ተሰራ። የህዝብን እኩልነት ለማረጋገጥ በሚል፤ በሰንደቅ አላማው ላይ ባዕድ ምልክት በማድረግ፤ የአለማችን የሰይጣን አምላኪዎች የሚጠቀሙበትን የተከበበ ኮከብ አርማ በሰንደቅ አላማው ላይ አስቀመጡበት። ውጤቱ ግን ዛሬ በኦሮሚያም ሆነ በሱማሌ ወይም በአንዳንድ ክልሎች፤ እንኳንስ ኮከብ አላባው ቀርቶ የራሳቸው ባለኮከብ ባንዲራም፤ ከመንግስት መስሪያ ቤቶች በስተቀር የትም ቦታ በኩራት አይውለበለብም።

 ከሆነ አይቀር… የጋራ ታሪክ እንዳይኖረን ለማድረግ ኢህአዴግ የሰራቸውን አንዳንድ ስህተቶች በወፍ በረር እንቃኝ። ለምሳሌ  ኢህአዴግ አዲስ አበባ እንደገባ የዳግማዊ ምኒልክ ሃውልት እንዲፈርስ ከወሰነ በኋላ፤ በወቅቱ የኢህዴን (አሁን ብአዴን) ታጋዮች፤ “ያታገልነው የምኒልክን ሃውልት ለማፍረስ ነበር ወይ?” የሚል ሙግት በመጀመራቸውና በህዝቡ ተደጋጋሚ ጩኸት ጭምር የጋራ ሃውልታችን ሳይፈርስ ቀረ። በዚህ ሽንፈት ያፈሩት ኢህአዴጋውያን፤ ይህንን ስህተት ያረሙት በአጼ ምኒልክ ላይ የሃሰት ክሳቸውን ለማጠናከር፤ ኤኖሌ ላይ የድንጋይ ጡት በሃውልት መልክ አሰሩ። ይሄ አይናችን የሚያየው እውነት ነው።

 ይህ ብቻ አይደለም። የአድዋ በአል የጋር ትግላችን ውጤት መሆኑን ደግመን ደጋግመን ስንጽፍ እና ስናስረዳ፤ ኢህአዴግ የማያቋርጥ የማጥላላት ዘመቻውን ቀጠለበት። የአድዋ መቶኛ አመት “አዲስ አበባ ውስጥ እንዳይከበር” ሲደረግ፤ ከሃውልቱ ስር አበባ ልናስቀምጥ ወደ ስፍራው ያመራነውን የኢትዮጵያ ነጻ ፕሬስ ጋዜጠኞች በፖሊስ እና በደህንነት ኃይል ከስፍራው እንድንባረር ማድረጋቸው፤ እንደትላንት የምናስታውሰው ትዝታችን ነው። የአድዋ በአል አዲስ አበባ ውስጥ በህዝብ እንዳይከበር ቢደረግም፤ ህዝቡ እያገነገነ ሲመጣ… “የአድዋ በአል መከበር ያለበት አዲሳባ ሳይሆን አድዋ ላይ ነው!” አሉን። ይሁን ብለን የአድዋው በአል እንዴት እንደሚከበር ስንከታተል፤ በመጀመሪያ… በአድዋ ጦርነት ግዜ ከጣልያን ተማርከው የነበሩ መድፎች ወደ አድዋ፤ ትግራይ ተጭነው ይወሰዱ ጀመር።

“ኧረ በህግ አምላክ!” ብለን ስንጮህ ሰሚ አጣን።

ይሄ ትልቅ የታሪክ ቅርስ ዘረፋ፤ “ትክክል አይደለም” ብለን ስንሟገት… በኢትዮጵያ ፓርላማው መግቢያ ላይ፤ በግራ እና በቀኝ ለታሪክ እንዲቀመጡ የተደረጉ ሁለት መድፎች ተነቅለው ወደ ትግራይ አድዋ ተወሰዱ። እነዚህ መድፎች በነራስ አባተ እና ባልቻ አባ ነፍሶ ወደ ጣልያን መንደር እየተተኮሱ፤ የትግራይን ተራሮች አንቀጥቅጠዋል፣ የጠላትን ኃይል አርበድብደዋል። በነዚያ ጀግኖች መስዋዕትነት ኢትዮጵያ በነጻነት ቆይታ፤ የራሷ ፓርላማ እንዲኖራት አድርጋለች። እናም እነዚያ ሁለት መድፎች በፓርላማው መግቢያ ላይ መቀመጣቸው ትልቅ ትርጉም ይሰጥ ነበር።

በወቅቱ ስለነዚህ መድፎች በተደጋጋሚ ጥያቄ ስናቀርብ፤ “መቶኛው አመት ትግራይ አድዋ ላይ ከተከበረ በኋላ ይመለሳሉ” አሉን። እነዚያ ታሪካዊ መድፎች ግን ዛሬም ድረስ የት እንዳሉ ሳይታወቅ የጋራ ታሪካችንን በጋራ አጠፉት። ብዙ ማለት ይቻላል። በዳግማዊ ምኒልክ ቤተ መንግስት ውስጥ የነበሩ ሰነዶች ተመዝብረው አልቀዋል። የምኒልክን የወርቅ ማንኪያዎች ፒያሳ በሚገኙ ወርቅ ቤቶች የሸጡ፤ የምኒልክን ሽጉጥ ጭምር ታጥቆ መጠጥ ቤት ሲዞር የነበረ ሃለፎም የሚባል ወጠጤ ታጋይ እና ሌሎችንም ታሪኮች አገር ቤት በነበርንበት ወቅት በየጋዜጦቻችን ላይ ስንዘግብ የነበረ እውነት ስለሆነ፤ እዚህ ላይ በድጋሚ መዘርዘሩ ይበልጥ ለመናደድ ካልሆነ በስተቀር፤ ብዙም ጥቅም ላይሰጥ ይችል ይሆናል። እነዚህ ሁሉ ታሪክን የማጥፋት ስህተቶች ግን፤ ተጠራቅመው ተጠራቅመው… ሊታረሙ የሚሞከሩት በሌላ ስህተት መንገድ መሆኑ ይበልጥ ያናድዳል።

እነዚህንና ሌሎች ታሪኮችን ለማጥፋት ሲባል፤ በወመዘክር የሚገኙ የታሪክ ሰነዶች ጭምር በኪሎ እንዲሸጡ የተወሰኑት ከቅርብ አመታት በፊት ነው። ኢትዮጵያ ታሪኳን እንኳን የሚነግርላት ምሁር እንዳይኖር፤ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ይሰጥ የነበረው የ”ኢትዮጵያ ታሪክ ዲፓርትመንት” በትዕዛዝ እንዲዘጋ የተደረገውም ከጥቂት አመታት በፊት ነው። ተጭነው ሊወሰዱ ከማይችሉት፤ የፋሲል ግንብ እና ላሊበላ በስተቀር፤ በእጃቸው የገቡ የታሪክ ቅርሶች ብዙዎቹ የሉም። ሌላው ቀርቶ አዲስ አበባ ሙዚየም ውስጥ የነበረውና በመስታወት ውስጥ ሆኖ ለህዝብ ይታይ የነበረው የቀዳማዊ ኃይለሥላሴ የጣት ቀለበት ጭምር ደብዛው ጠፍቷል። 

ጎበዝ እነዚህን የምናወራው… ጥቂት ጸሃይ የሞቃቸው ጉዳዮች በመሆናቸው እንጂ፤ ውስጥ ውስጡን እኛ የማናውቃቸው እጅግ የበዙ እና የገዘፉ ነውሮች ሊኖሩ እንደሚችሉ ለመገመት ከባድ ሆኖብን አይደለም። ለምሳሌ ያህል… የኤርትራ መገንጠል ከመታወጁ እና ከታወጀ በኋላ በግልጽ ትዕዛዝ፤ በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ውስጥ መኮንን አዳራሽ ውስጥ የነበሩ ከኤርትራ ጋር ተዛማጅነት ያላቸው ታሪኮች በሙሉ ተሰብስበው ወደ አስመራ እንዲወሰዱ ተደርጓል። ይሄ እኛ የምናውቀው እና በወቅቱ፤ በልጅ አንደበታችን “ኧረ በህግ አምላክ!” እያልን የጮህንበት ጉዳይ ነው። ከዚያ በፊት እና በኋላ፤ በሌላ ቦታና ስፍራ ከዚህ የበለጠ ተደርጎ ሊሆን እንደሚችል ታሳቢ ማድረግ ያስፈልጋል። በነገራችን ላይ በመጨረሻው የኢትዮጵያ እና ኤርትራ ጦርነት ወቅት ጉዳዩ በአለም አቀፍ ፍርድ ቤት ሲታይ፤ ኢትዮጵያ ላይ የቀረቡት ሰነዶች ምንጭ፤ በፍቅራቸው ግዜ ከኢትዮጵያ ተጭነው የተወሰዱ ሰነዶች መሆናቸውን… በኤርትራ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ውስጥ ይሰራ የነበረ አምዶም የሚባል ሰው በስደት ዘመናችን በዝርዝር ነግሮን፤ ይበልጥ እንድንቆጭ ያደረገበት አጋጣሚ ተፈጥሮ ነበር።

ኢህአዴግ የታሪክ ሰነዳችንን ብቻ ሳይሆን፤ በቀይ ባህር በኩል የነበረንን የአሰብ ወደብ በር ጭምር አሳልፎ ሰጥቷል። ያን ያህል ዋጋ ያለው የባህር በር በምርቃት መልክ ሰጥቶ፤ ለባድመ ጦርነት ግን ሰባ ሺህ ኢትዮጵያውያንን በጦርነት ማግዷል። በዚህ እና በሌላ ሌላም ተግባሩ ምክንያት፤ ከኤርትራ ህዝብ ጭምር አቆራርጦናል። የተቀረውንም የኢትዮጵያ ህዝብ እርስ በርሱ ለማቆራረጥ ብርቱ ስራ እየሰራ ይገኛል – ኢህአዴግ። ይሄንን እኩይ እቅድ ለማስፈጸም ደግሞ… እታች ድረስ ወርዶ የዘር ፖለቲካን እንደአረም እርሻ በህዝቡ መሃል መዝራቱን ቀጥሎበታል። እራሱ ያመጣው የዘር ፖለቲካ መልሶ እየፈጀውም ቢሆን፤ ዛሬም ድረስ እነዚህ ሁሉ ስህተቶች የሚያርመው ሌላ ስህተት በመስራት እንጂ ካለፈው በመማር አይደለም። የዘር ፖለቲካው ወርዶ ወርዶ የስፖርት ቡድኖችን ጭምር እያዳረሰ ነው። ስፖርት ለሰላም እና ለወዳጅነት መሆኑ ቀርቶ፤ ህዝብን በአንድ ሊያሰባስብ በሚችል ስፖርት መሃል የዘር መርዝ ረጭቶ፤ ደም ሲያቃባን ከማየት በላይ የሚያሳዝን እና የሚያሳፍር ነገር የለም። ይህ ሁሉ የስህተት መንገድ እና ጉዞ እየተሄደ ያለው ደግሞ በኢህአዴግ እና በደጋፊዎቹ አማካኝነት መሆኑን ለአንድ አፍታም ቢሆን ልንዘነጋው አይገባም።

የኢትዮጵያ እና የአፍሪካ የስፖርት አባት ተብለው በመልካም ስም የሚሞገሱት አቶ ይድነቃቸው ተሰማ፤ በዘር እና በብሄር ላይ የተመሰረተን የስፖርት ክለብ  ህዝብን በህዝብ ላይ የሚያነሳሳ መርዝ መሆኑን ይገልጹ ነበር፤ በኢትዮጵያም ሆነ በአለም አቀፍ ደረጃ አገር ወይም ክለብን እንጂ የዘር ፖለቲካን መሰረት ያደረገ የስፖርት ክለብ ተቀባይነት እንዳይኖረው አድርገዋል። በህይወት ዘመናቸው  ወቅት፤ በኤርትራ ውስጥ በዘር ተደራጅተው የነበሩትን የሃማሴን እና አካለጉዛይን እግር ኳስ ቡድን ስሙንም አቋሙንም እንዲያስተካክል አድርገዋል። እነዚህ የእግር ኳስ ቡድኖች ተቋቁመው የነበሩት በጣልያኖች አማካኝነት ነበር። ጣልያን ይህን ያደረግገው በ“ከፋፍለህ ግዛው!” ጨዋታ ህግ መሰረት፤ ሁለቱ ትላልቅ የኤርትራ ብሄሮች ይበልጥ እንዲራራቁና እንዲጣሉ በማድረግ፤ ጣልያኖቹም መልሰውም አስታራቂ በመሆን የስልጣናቸው እድሜ እንዲረዝምላቸው የነደፉት እቅድ ነው።

እናም አቶ ይድነቃቸው ተሰማ እንዲህ አይነቱን በዘር ላይ የተመሰረተ የስፖርት እንቅስቃሴ እንዲፈርስ ካደረጉ ብዙ አመታት ተቆጥረዋል። ከብዙ አመታት በኋላ ግን ኢህአዴግ የጣልያኖቹን ናሙና በመከተል፤ በብሔር ላይ ያተኮረ የእግር ኳስ ቡድኖች ፈጥሮ የርስ በርስ ግጭቱ ይበልጥ እንዲፋፋም በማድረግ ላይ ነው። እነዚህ ሁሉ ስህተቶች የሚታረሙት ደግሞ ሌላ ስህተት በመስራት ስለሆነ፤ የሌላው ብሄር ተወላጆች ትግራይ ላይ ሄደው ሲጫወቱ ይደበደባሉ፤  የትግራይ ቡድን ተጫዋቾች ወደሌላ ክልል ሲሄዱ ደግሞ በፌዴራል ፖሊስ ታጅበው፤ የተቃወማቸው ህዝብ ሲቀጠቀጥና ሲገደል አብረን እያየን፤ የአይን ምስክርም እየሆንን ነው። እንግዲህ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የብሄር ፖለቲካ እታች ድረስ ወርዶ የስፖርት ቤተሰቡን የመከፋፈል ሚና፤ በጉልህ እየተጫወተ ነው።

ዛሬ ኢትዮጵያ ውስጥ የሚነሳ ማንኝውም ችግር መሰረቱ የኢህአዴግ አስተዳደር ለመሆኑ እሩቅ መሄድ አያስፈልግም። እያንዳንዱ ተፈጠረ የሚባለውን ችግር እና መነሻቸውን ወደኋላ መለስ ብለን ካጤንን፤ ያለምንም ጥርጥር የኢህአዴግ እጅ እንዳለበት ማረጋገጥ እንችላለን። በኢትዮጵያ ውስጥ የእስር፣ የአፈና፣ የማሰቃያ እና የመግደያ መዋቅሮችን አደራጅቶ የሚንቀሳቀስ ድርጅት ነው – ኢህአዴግ። የኢትዮጵያ ነጻ-ፕሬስ ጋዜጠኞች እንዲሰደዱ፤ የፖለቲካ ድርጅቶች እንዲሽመደመዱ፤ የሲቪክ ማህበራት እንዲፈርሱ እና የህዝብ ሃብቶች እንዲወረሱ ያደረገ ድርጅት ነው – ኢህአዴግ። በአገሪቱ ውስጥ በሚገኙ እንደባንክ፣ ቴሌ እና አየር መንገድ የመሳሰሉ መስሪያ ቤቶች ውስጥ ያለምንም ይሉኝታ፤ የራሱን ሰዎች በማስቀመጥ በሚሊዮን የሚቆጠር ዶላር እንዲመዘበር የሚያደርግ ድርጅት ነው – ኢህአዴግ። የፖሊስ፣ የደህንነት እና የመከላከያ ኃይሎችን የሚቆጣጠር፤ እንደሜጋ አይነት ግዙፍ የንግድ ድርጅቶችን በማቋቋም የሚሊዮን እና የቢሊዮን ብር ስልቻዎችን በየፈርጁ የሚቆጣጥር ድርጅት ነው – ኢህአዴግ።

የኢህአዴግን ግፍ እና በደል ዘርዝረን ለመጨረስ መሞከር፤ የሰማይ ላይ ከዋክብትን ሲቆጥሩ ውሎ እንደማደር የሚቆጠር ነው። ይህም ሆኖ ይህን መስማት የማይፈልጉ ጆሮዎች አሉ። እነዚህ ሰዎች ሁሌም “ልማት ላይ ነን!” የሚል አደንቋሪ ከበሮ ይደልቃሉ። እርግጥ ነው- እየተሰራ ያለው ልማት መሬት ላይ እስከሆነ ድረስ የትም አይሄድብንም። ነገር ግን አገር እና ትውልድ እየተለያዩ፤ ኢትዮጵያን ያህል ትልቅ አገር አደጋ ውስጥ እየገባች መሆኑን የሚያዩበት ህሊናቸው ታሟል። የኢትዮጵያ ህዝብ እና አንድነቷ፤ እነሱ ከሚሉት ልማት በላይ መሆኑን ዘንግተውታል። የዚህ ህዝብ አንድነት ካልተጠበቀ፤ ኢህአዴግም ስህተትን በስህተት እያረመ መሄድ ላይ ከዘለቀ፤ ሁላችንም ተያይዘን እንወድቃለን እንጂ ማንም አሸናፊ ሊሆን አይችልም። እኛ ስለሰብአዊ መብት አጠባበቅ፣ ስለፖለቲካው ምህዳር መጥበብ፣ ስለሙስናው፣ ስለዘረኝነቱ፣ ስለፍትህ ማጣት ስናወራ… ኢህአዴግ “እሱን ትታቹህ ልማቱን ብቻ እዩልን” ይለናል። አገር ያህል ትልቅ ነገር እየፈረሰ ስለመንገድ እና ህንጻ መብዛት ማውጋት ከቅንጦትም በላይ ቅብጠት ሆኖብን፤ ዛሬም “ኧረ የሰሚ ያለህ!” ማለታችን አልቀረም።

ይሄን ስንል አንድ የሱማሌዎች ተረት ታወሰን። ቀበሮ አንድ ዋሻ ውስጥ ቤት ነበረው። ቤቱ ቀዳዳው ከመብዛቱ የተነሳ መግቢያ እና መውጫው አይታወቅም። አንድ ቀን ቀበሮ ጥንቸልን በእንግድነት ቤቱ ጋበዛት። ጥንቸል የዋሻው ቤት ውስጥ እንደገባች የቀዳዳውን ብዛት አይታ፤ ቤቱንም በንቀት እያየች… “ምንድነው ይሄ ሁሉ ቀዳዳ?” አለችው።

ቀበሮም ፈጠን ብሎ፤ “አንቺ አንድ በር ነው ያለሽ። ጠላት ቢመጣብሽ ከመበላት በቀር ምንም ማምለጫ የለሽም። እኔ ጋር ግን ብዙ ቀዳዳ አለኝ። ጠላት በዚህኛው በር ቢመጣ በዚህኛው ወጥቼ አመልጣለሁ፤ በዚህኛው ቢመጣ በዚኛው…” እያለ ስህተቱን በውሸት ሸፍኖ ጥንቸልን ሊያሳምናት ሞከረ። እናም መልካም አስተዳደር መፍጠር እና ሰላም ማስፈን የተሳነው ኢህአዴግ መሰረታዊ ስህተቶቹን ለመሸፋፈን ሲል፤ ስለጠላት እና ስለልማት ብዙ ሊያወራልን ይሞክራል። በዚህ መሃል የህዝብ ብሶት ታላቅ ንቅናቄ ፈጥሮ፤ ህዝባዊ ትግሉ ሊቀለበስ የማይችልበት ደረጃ ላይ ደርሷል። እዚህ ደረጃም ላይ ተደርሶ፤ ኢህአዴግ እንደህጻን ልጅ ሊደልለን እና በተራ ውሸት ሊያታልለን መሞከሩን አላቋረጠም። 

በአጠቃላይ የኢህአዴግ መንገዶች፤ ከአፈና ወደ አፈና… ከሞት ወደ ሌላ ሞት የሚያሸጋግሩ፤ ህዝብ እና አኩሪ ታሪኩ የሚገናኙበትን ድልድዮች የሚሰባብሩ፤ ትውልድ እና አገርን በጠመንጃ አፈሙዝ የሚያሸብሩ ናቸው። ታላላቅ የአለማችን መሪዎች ካለፉት መሪዎቻቸው ስህተት በመማር፤ የቀደመውን ጥፋት መልሰው አይደግሙትም። በኢትዮጵያ የበቀሉት መሪዎች ግን እንኳንስ ካለፈው ስህተት ሊማሩ ቀርቶ፤ ቀደም ሲል የነበሩትን መሪዎች ያንቋሽሻሉ። ሌላው ቀርቶ የቀደሙት መሪዎች ያልፈጸሙትን ስህተት እነዚህ እንደአዲስ ይፈጥሩልናል። እራሳቸው ስህተት ሰርተው፤ ለስህተቱ እርማት ማድረግ የሚችሉ የመፍትሄው አካል እነሱ ብቻ እንደሆኑ ይሰብካሉ። የፈጠሩትን ስህተት ግን ሊያርሙት ቀርቶ፤ ስህተታቸውን በሌላ ስህተት ይተኩታል። ይሄ ሳያቋርጥ የሚቀጥል የአገራችን እውነታ እና የኢህአዴግ በሽታ ሆኗል።

 መቼ እንደሚቆም ባናውቀውም… ኢህአዴግ እንደዱርዬ ልጅ መስረቅ እና ማጭበርበርን እንደሙያ ተያይዞታል። በዚህ የስህተት መንገድ የሚመላለሱ ብዙ ሰዎችም አሉ። እኛ ግን ትላንት ያልነውን ዛሬም እንደግመዋለን… “ስህተትን በስህተት ማረም አይቻልም። የስህተት መንገድ ስህተት፤ መጨረሻውም ውድቀት ነው!” እንላለን። ይህ መልዕክታችን ታዲያ ለዛሬ ብቻ ሳይሆን፤ ለነገም …ከነገም ወዲያ ለሚመጣው ትውልድ ጭምር ይሁን!

በዚህ ሁሉ መሃል ግን… በተለይ የኦሮሞ ህዝብ ከሌላው ኢትዮጵያዊ ጋር ሊኖረው የሚገባውን የጋራ ታሪክ፣ የጋራ ጀግና፣ የጋራ ቋንቋ፣ የጋራ ፊደል እያጣን መሆኑ እያሳዘነን፤ ነገና ከዚያ ወዲያም የጋራ አገር እንዳይኖረን እየተሄደበት ያለው የስህተት መንገድ ትክክል እንዳልሆነ ስናስብ፤ ይህንን ትልቅ ስህተት ለማረም የሚወሰደውን ቀጣይ የስህተት እርምጃ ስናስብ… ልባችን በጥልቅ ሃዘን ውስጥ ወደ ታች ስንጥቅ ይልብናል። ቸር ያሰማን!!

Filed in: Amharic