>
5:14 pm - Monday April 20, 8409

በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስም በሀገርና በሕዝብ ላይ የሚደርሰው በደል ይቁም! (ከሰማያዊ ፓርቲ የተሰጠ መግለጫ)

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በመላ ሀገሪቱ የተፈጠረው ፖለቲካዊ ችግር ስር እየሰደደ መሄዱ የማያሳስበው አንድ ዜጋ አይኖርም፡፡ ላለፉት 27 ዓመታት ሲከማቹ የመጡ በርካታ ኢህአዴግ ሰራሽ ችግሮች ዛሬ ላይ ሕዝባዊ ቁጣን በማስነሳት ሰላምና መረጋጋታችን ብርቱ ፈተና ላይ ወድቋል፡፡ ገዢው ፓርቲ ይህንን እንደሰደድ እሳት የሚቀጣጠል ችግር የሕዝብን ድምፅ በማድመጥ ተገቢውን ምላሽ ከመስጠትና አገራዊ መግባባትን ከመፍጠር ይልቅ ሀገሪቱን እንደገና ለአስቸኳይ ጊዤ አዋጅ ዳርጓታል፡፡
ባለፈው የካቲት 23/2010 ዓ.ም የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት አፀደቀው የተባለውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ዜና ከመነሻው የሚኒስትሮች ም/ቤት አዋጁን ይፋ ባደረገበት ወቅት ሰማያዊ ፓርቲ(ሰማያዊ) አግባብነት የሌለውና አሁን የተፈጠረውን ችግር ይበልጥ ከማባባስ በዘለለ አንዳችም ፋይዳ እንደማይሰጥ ጋዜጣዊ መግለጫ መስጠቱ ይታወቃል፡፡
አዋጁ በሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት ለመጽደቅ በቀረበበት ወቅት በርካታ የምክር ቤት አባላት ሀገሪቱ ያለችበትን ወቅታዊ ሁኔታ ከግምት ውስጥ በማስገባት እንዲሁም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሊከሰቱ የሚችሉ የሰብዓዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ጥሰት፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ቀውሶችን በመስጋት በገሃድ መቃወማቸውን ተገንዝበናል፣ ይህ በአጨቃጫቂና በአወዛጋቢ ክስተቶች ታጅቦ በም/ቤቱ ፀድቋል የተባለው አዋጅ የመፅደቅ ሁኔታ እንድንጠራጠረው አድርጎናል፡፡ ግልፅነትና ተዓማኒነት የጎደለው ስለመሆኑም የም/ቤቱ አፈ-ጉባኤ በኢቢሲ ቀርበው የገለፁት የቁጥር ማሻሻያ ለዚህ በዋቢነት ሊጠቀስ የሚችል ነው፡፡
በአጠቃላይ ፓርቲያችን ሰማያዊ በተደጋጋሚ በመግለጫዎቹ ሲገልፀው የነበረውን አገራዊ መግባባት ላይ የሚደረስበትን ምቹ ሁኔታ እንዲፈጠር ዛሬም ጥያቄውን የሚያቀርብ ሲሆን ከዚህ በታች
በተጠቀሱት ጉዳዮች ላይ ያለውን አቋም ለመግለፅ ይገደዳል፡፡
1.ገዢው ቡድን ለሕዝብ ጥያቄ ተገቢውን መልስ እስካልሰጠና እገዛበታለሁ እያለ ነጋ ጠባ ለሚደሰኩርለት ሕገ መንግስት እስካልተገዛ ድረስ ዜጎች አደባባይ በመውጣት በሰላማዊ መንገድ ጥያቄያቸውን ከማቅረብ እንደማይቆጠቡ ከአዋጁ መፅደቅ ማግስት ጀምሮ በተግባር እያሳየ ነው፡፡ ይህንንም ተከትሎ የሰብዓዊ መብት ተሟጋችና ጦማሪ ስዩም ተሾመ እንዲሁም በተለያዩ የኦሮሚያ አካባቢዎች በሚገኙ የተዋረድ መዋቅሮች ላይ ሕዝብን የሚያገለግሉ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ላይ እየተወሰደ ያለው የአሥራት እርምጃ ፍፁም አግባብነት የሌለው መሆኑን ሰማያዊ ፓርቲ(ሰማያዊ) በአፅንኦት ይገልፃል፡፡
2.ሥርዓቱ ስር የሰደደ የሙስና ደዌ የተጠናወተው መሆኑን ራሱ ገዢው ፓርቲም አምኖ የተቀበለው ጉዳይ ነው፡፡ በተለይም የመሬት ፖሊሲው ለሙሰኞች ባመቻቸው መንገድ በመላ ሀገሪቱ የተቀራመቱትን ተገቢ ያልሆነ ይዞታ በሕጋዊ መንገድ ወደ ሕዝብ ንብረትነት መመለሱ ያንገበገባቸው የሥርዓቱ ጋሻ ጃግሬዎች በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ  በማሳበብ ኮማንድ ፖስቱ እንዲቆጣጠረው ማድረግ በብርቱ ያሳዝናል፡፡ በሌላ በኩል የኢትዮጵያ ሕዝብ ከጥንት ጀምሮ የአካባቢውን ሰላምና ፀጥታ ለመጠበቅ የሀገሪቱ የሕግ አግባብ በሚፈቅደው መሠረት መሣሪያ መያዝን የተለማመዱ እና በተለይም በጠረፍ አካባቢዎች የመከላከያ ሰራዊት በሌለበት ሁኔታ ድንበር የመጠበቅ ግዴታ እንዳለበት ማንም ሳይናገረው የሚያውቀው ሀቅ ነው፡፡ ለዚህም ማሳያ የጋምቤላ ሕፃናት በደቡብ ሱዳን የሙርሌ ጎሳዎች ታፍነው ሲወሰዱ የነዋሪው ትጥቅ አልባ መሆን የፈጠረው ክፍተት እንደሆነ ሊታመን ይገባል፡፡ ከዚህ አንፃር ከሕዝብ ጋር ለዘመናት የቆዩ ትጥቆችን በጉልበት ለማስፈታት መንግስት እያደረገው ያለውን ተግባር ከውጭ ወራሪ ኃይል እና ጥቃት ከመከላከል አንፃር ፓርቲያችን በብርቱ ይቃወማል፡፡
3.ከሦስት ቀናት በፊት የሀገሪቱ የመከላከያ ሠራዊት በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሽፋን በኦሮሚያ ክልል በቦረና ዞን በሞያሌ ከተማ ያጠፋው የንፁሐን ዜጎች ሕይወት በይቅርታ የሚታለፍ ብቻ ሳይሆን ይህ ኢ-ሰብዓዊ የሆነ የግድያ ወንጀል እንዲፈፀም ትህዛዝ ያስተላለፉ አዛዦችና ታዘው ግድያውን የፈፀሙ  የሠራዊት አባላት ለሕዝብ ግልፅ በሆነ መንገድ በፍርድ ተጠያቂ እንዲሆኑ አጥብቀን እንጠይቃለን፡፡
4.ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ስትራቴጂክ ቦታ ላይ የምትገኝ መሆኑ እሙን ነው፡፡ ይሄንንም ተንተርሶ ባሳለፍነው ሳምንት የአሜሪካ፣ የሩሲያ፣ እንዲሁም የተባበሩት አረብ ኤሚሬት የውጭ ግንኙነት ኃላፊዎች በሀገራች መዲና አዲስ አበባ ተገኝተው ያደረጉት ውይይት ከመንግስት መገናኛዎች ተከታትለናል፡፡ በነበራቸው ቆይታም የኢትዮጵያን ጉዳይ የገዢው ፓርቲ ጉዳይ ብቻ አድርገው ተነጋግረው ማለፋቸው በእጅጉ አሳዝኖናል፡፡
ኢትዮጵያ ያለችበትን ስጋት ኃላፊነት ከማይሰማው ገዢው ፓርቲ ይልቅ በጥልቀት የኢትዮጵያን ሕዝብ ያሳስበዋል፣ ገዢው ቡድን ለዘመናት በኢትዮጵያውያን ጫንቃ ላይ ያሳረፈውን የመከራ መርህ በቃኝ ወደሚልበት ምዕራፍ መሸጋገሩን የእነዚህ ሀገሮች ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች የሀገራችንን ሁኔታ አለመረዳት አሊያም በኢትዮጵያ ሕዝብ የነፃነትና የፍትህ ጥያቄ ላይ ውኃ እንደመቸለስ መሆኑን ያሳያል፡፡
ሰማያዊ ፓርቲ(ሰማያዊ) የኢትዮጵያ ጉዳይ የሚፈታው በኢትዮጵያ ሕዝብ መካከል በሚደረግ ግልፅነት በሰፈነበት ሰላማዊ ውይይት ብቻ እንደሆነ ያምናል፡፡ የኃያላኖች ከዚህ ቀደም ጣልቃ ገብነት በሀገራችን ላይ ጥሎ ያለፈውን አሻራ ፈፅሞ አይዘነጋም፣ ተጨማሪም ጠባሳ እንዲጣልበት አይፈልግም፡፡
ሰማያዊ ፓርቲ (ሰማያዊ) ማንኛውም በኢትዮጵያ ሰላም እንዲሰፍን የሚፈልግ አካ የሚያደርገውን አስተዋጽኦና ድጋፍ በእጅጉ የሚያከብርና የሚያደንቅ ቢሆንም በውስጥ ጉዳያችን የሚደረግ ጣልቃ ገብነትን ግን በፍፁም አይቀበልም፡፡
በመጨረሻም የአገራችንን ውስብስብ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና፣ ማህበራዊ ችግሮችን ለመፍታት ያለው ብቸኛ አማራጭ አገራዊ መግባባት መፍጠርና በጠረጴዛ ዙሪያ መወያየት መሆኑን ሰማያዊ ፓርቲ(ሰማያዊ) በጥልቅ ያምናል፡፡ ገዢው ቡድንም የጠብመንጃ ቃታ ከመሳብና በጦር ኃይል ዜጎችን ከማስፈራራት ተቆጥቦ ከሕዝብ ጋር እርቅ ቢያወርድ እንደሚበጀው አጥብቀን መግለፅ እንሻለን፡፡
ኢትዮጵያ በክብርና በነፃነት ለዘላለም ፀንታ ትኑር!
መጋቢት 4 ቀን 2010 ዓ.ም
አዲስ አበባ
Filed in: Amharic