>

ለአድዋ ትርጉም ፍለጋ! (ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ)

አሁን ከመሸ በፌስ ቡክ የውስጥ መስመር፣ ‹‹ጋሼ ምነው ዝም አልክ? በእለተ አድዋ ምንድነው የሚሰማህ? ለመሆኑ አድዋ ለአንተ ምንድነው?›› የሚል መልእክት ከአመታት በፊት ተማሪዬ ከነበረች፣ ሳራ የምትባል ሰው ደረሰኝ፡፡ . . . ምንም ለማለት ምንም ፍላጎት አልነበረኝም፡፡  የተማሪን ጥያቄ አልመልስም አይባልም፡፡
አውቃለሁ! አድዋ ነጻነት ነው! ባንዲራም፣ ክብርም፣ የሰው መሆን አዋጅም ነው – ሰርተፊኬት! ይህ ሁሉ ግን አድዋን በደምና በህይወት ለሰሯት አባቶቻችን ነው፤ አልፎም ለመላው የጥቁር ዘር፡፡ ይህ ትውልድ አድዋን ነጻነት፣ ባንዲራ፣ ክብርና ሰው የመሆን አዋጅ ብሎ ሊፈታው አይችልም፡፡ የአድዋን ድል ታላቅነት ሊያስብ አደባባይ በወጣበት፣ እንደራሴዎቹ ተሰብስበው በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መብቱን የሚገፉት ትውልድ አድዋን ነጻነት ብሎ ሊበይን ይችላል? የአድዋ ጀግኖች ያጌጡበትን የድል አርማ – ቀይ፣ ቢጫ፣ አረንጓዴ ሰንደቅ፣ ድላቸውን ለማክበር በወጣበት አደባባይ እንኳን፣ እንዳይጠቀምበት በፖሊስ የተከለከለ ትውልድ አድዋ ለመያ አርማዬ – መመኪያ ሰንደቅአላማዬ ነው ሊል ይችላል? ሀገር ማንም የሚደፍራት ባለቤት አልባ ግጦሽ ሆና (በደቡብ ሱዳን ታጣቂዎች በጋምቤላ የደረሰውን ያስታውሷል) የተመለከተ ትውልድ፣ አድዋ የሀገር ድንበር መከበር ነው ሊል ይችላል? በቋንቋው እየተሰፈረ በተበጀለት ክልልና በጠባብ ጎሳዊ ኮረጆ ውስጥ ትልቁን ሰብአዊ ክብሩንና ማንነቱን ጠቅልሎ ለማስገባት፣ ትዳሩን፣ ጉርብትናውን፣ እድሩን . . .  . እያፈረሰ፣ ከሩብ ምእተአመት በላይ እየተጋጋጠ ማንነቱን እየከረከመ ያለ ትውልድ፣ አድዋን የህብረትና የአንድነት ምልክት አድርጎ ሊተረጉመው ይችላል?  . . . በፍጹም!
ሳራ፣ ለዚህ ትውልድ አድዋ ሊኖረው የሚችለው ፍቺ አንድ ብቻ ነው፤ ጀግኖች አባቶቹ አድዋ ላይ ያሰረጹትን ፍቺ መመለስ! አድዋን የነጻነት ባንዲራም፣ ክብር፣ የሰው መሆን አዋጅ ማድረግ፡፡ ይህ ደግሞ ትግል ይፈልጋል፡፡ እና ሳራ፣ በዚህ ዘመንና ትውልድ የአድዋ ፍቺ ትግል ነው – ጀግኖች አባቶቻችን በአድዋ የቋጠሩልንን ልእልና ከተበተነበት ሰብስቦ፣ ለትውልድ እንዲተላለፍ የሚደረግ ትግል ነው – የአድዋ ፍቺ፡፡ ያንን ፍቺ እውን ካደረግን ልጆቻችን፣ ‹‹አድዋ ነጻነት ነው! ባንዲራም፣ ክብርም፣ የሰው መሆን አዋጅም ነው – ሰርተፊኬት!›› ብለውን እየዘመሩ ያከብሩታል፡፡
Filed in: Amharic