>

የህወሀት የበላይነት የተንሰራፋበት ምክር ቤት - አሳፋሪ ታሪክ ተመዝግቧል የሞት አዋጁም ጸድቆብናል!?! (መሳይ መኮንን)

ብዙዎቻችን ትንሽ ዕድል ሰጥተናቸዋል። ምናልባት የዘመናት ሃጢያታቸውን በዚህች ቆራጥ ውሳኔያቸው ሊያካክሱ ይችሉ ይሆን በሚል ግመል በመርፌ ቀዳዳ የመሽሎክ ዓይነት የሚመስል ተስፋ ያሳደርን ጥቂቶች አይደለንም። የትግራይ ነጻ አውጪ ግንባር በጉልበት ለመቀጠል በሚል ያወጣውን የሞት አዋጅ ፓርላማው ተባባሪ እንዳይሆን ጥረቶች ተደርገዋል። በአብዛኛው የፓርላማ አባላት ዘንድ በስልክና በአካል በመድረስ አዋጁን በማጽደቅ የታሪክ ተወቃሽ እንዳይሆኑ በሚገባ ተነግሯቸዋል። የድርጅት ማዕከላዊነትን በመስበር አዋጁን ውድቅ እንዲያደርጉት ተጎትጉተዋል።

ምንም እንኳን ከህዝብ ግፊት በተጓዳኝ የትግራይ ጀነራሎችና ደህንነቶች ማስፈራሪያ እንደነበረ ቢታወቅም በዚህ ታሪካዊ አጋጣሚ ለየትኛውም የአገዛዙ ቁንጥጫ የማይንበረከኩ ሊሆኑ ይችላሉ የሚል ግምት በግሌ ውስጤ ነበር። በመጨረሻ ግን የተጠበቀው ሆኗል። ፓርላማው ታሪክ መስራት የማይችል እንደሆነ ዳግም አስመስክሯል። የፓርላማ አባላቱ እየሰመጠ ካለው መርከብ ዘለው እንዲወርዱ የተሰጣቸውን የመጨረሻ ዕድል አልተጠቀሙበትም። አብረው መስመጥን መርጠዋል።

በእርግጥ አዋጁ በሙሉ የፓርላማ አባላት ይሁንታ የጸደቀ እንዳልሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ። ከ80 በላይ አባላት የሞት አዋጁን መቃወማቸው ይነገራል። ይሄ በራሱ የሚነገረን የድርጅት ማዕከላዊነት መሰበሩን ነው። ወይም ደግሞ በጫናና ማስፈራራት ሳይሆን በነጻነት የተካሄደ የድምጽ አሰጣጥ ተደርጎ እንዲወሰድ በትግራዩ አገዛዝ በኩል የተጻፈ ድርሰት ሊሆን ይችላል። የፓርላማውን ቁልፍልፍ አሰራርና የትግራዩ አገዛዝ የሚጎነጉነውን ሴራ በቅርበት የሚያውቁት አስምረው የሚናገሩት አዋጁ ማዕከላዊነትን በጠበቀ አካሄድ በሙሉ ድምጽ የመጽደቅ ዕድሉ ሰፊ መሆኑን ነው።

እያንዳንዱ አባል የያዘው ድምጽ የግሉ አይደለም። የወከለው ፓርቲ ነው። ፓርቲው የወሰነውን አባሉ በፓርላማ እጁን አውጥቶ እንዲጸድቅ ከማድረግ ያለፈ ምንም ስልጣን የለውም። የፓርላማ አባሉ ውክልናው ለመረጠው ህዝብ ሳይሆን ላስመረጠው ድርጅቱ ነው። ይህ የትግራዩ አገዛዝ ፓርላማውን ያዋቀረበት ውስጣዊ አሰራር ነው። ፍጹም ነጻነትን የሚነጥቅ ስታሊናዊ አሰራር ነው። ይህ አሰራር ነው ላለፉት 27 ዓመታት የትግራዩን አገዛዝ በህግ ሽፋን ሀገሪቱን እንዳሻው እንዲጫወትባት ያደረገው።

ዛሬ በሞት አዋጁ ላይ ድርጅታዊ ማዕከላዊነት እንዳልነበረ የሚያሳይ የድምጽ ውጤት ተመዝግቧል። ከ80 በላይ የሚሆኑ አዋጁን ከተቃወሙት ውሳኔው የድርጅትን መስመር ተከትሎ የተካሄደ ነው ለማለት የሚቻል አይመስለኝም። እነዚህ 80ዎቹ ለምን ተነጥለው አዋጁን ተቃወሙት? ማዕከላዊነት ተሰበረ ወይስ በሀሳብ ፍጭት፡ በነጻነት የተደረገ የድምጽ አሰጣጥ ነው የሚል ድራማ ተሰርቶ ይሆን?

ምንም ሆነ ምን አዋጁ ጸድቋል። አሳፋሪው ታሪክ ተመዝግቧል። ፓርላማው ዕድሉን አጨናግፏል። በኢትዮጵያ ታሪክ ህዝብ ላይ የታወጀን ጦርነት ያጸደቀ ፓርላማ ከሚል ጥቁር መገለጫ ጋር የሚነሳ ፓርላማ ሆኗል። ብዙ ጥያቄዎች ይነሳሉ። አዋጁን አጥብቆ ሲያወግዝ የነበረው የኦህዴድ-ለማ ቡድን ከእንግዲህ ምን ሊያደርግ ይችላል? የትግራዩን አገዛዝ ለማዳን ህዝባቸውን የካዱት እነአባዱላ ገመዳ በአሸናፊነት የኦህዴድን መሪ ይጨብጡ ይሆን? ውጭ ያሉት የኦሮሞ አክቲቪስቶች የፓርላማውን ውሳኔ እየጠበቅን ነው– ከጸደቀ መሬት አንቀጥቅጥ አድማ እንዲጠራ እንቀሰቅሳለን ያሉትን ቃላቸውን ያጥፉ ይሆን? የዛሬው የፓርላማ ውሳኔ የተበታተነውን ትግል በአንድ ቋት ውስጥ አስገብቶ ለስርነቀል ለውጥ ያነሳሳልን?

Filed in: Amharic