>

ክፍት ደብዳቤ:  “ህገ-ወጥ፥ ፀረ-ህዝብ እና ሕሊና-ቢስ አለመሆናችሁን አረጋግጡልን” (ስዩም ተሾመ)

፡-ኢፊዲሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት
ጉዳዩ፡- የአስቸኳይ ግዜ አዋጅን ውድቅ ስለማድረግ 

የተከበራችሁ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት። በሕገ መንግስቱ አንቀፅ 54(4) መሰረት እናንተ የመላው የኢትዮጲያ ሕዝብ ተወካዮች እንደሆናችሁ ይደነግጋል። በመሆኑም ተገዢነታችሁም፤ ሀ) ለሕገ መንግስቱ፣ ለ) ለሕዝቡ እና ሐ) ለሕሊናቸ ብቻ እንደሆነ ተደንግጓል። የሚኒስትሮች ምክር ቤት የካቲት 09/2010 ያወጀው የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ግን ሀ) ሕገ መንግስቱን ይጥሳል፣ ለ) የዜጎችን ዴሞክራሲያዊ መብትና ነፃነት ይገፍፋል። ምክንያቱም፣

  • ሀ) የአስቸኳይ ግዜ አዋጁ በአንቀፅ 93 ንዕስ አንቀፅ 1(ሀ) መሰረት ሕገ-መንግስታዊ ስርዓቱን አደጋ ላይ የሚጥል ሁኔታ በሌለበት የታወጀ ስለሆነ ሕገ-መንግስቱን ራሱ ይጥሳል። ስለዚህ እንደ ሕዝብ ተወካይ ተገዢነታችሁ ለሕገ መንግስቱ ከሆነ ይህን የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ውድቅ ታደርጉት ዘንድ በአክብሮት እንጠይቃለን።
  • ለ) የአስቸኳይ ግዜ አዋጁ ዓላማ የሀገርን ሉዓላዊነት ወይም የሕዝብን ሰላምና ደህንነት ማስከበር አይደለም። ከዚያ ይልቅ፣ የአዋጁ መሰረታዊ ዓላማ በተለይ የኦሮሞ እና አማራ ሕዝቦች ያነሱትን የእኩልነት እና ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ጥያቄ በኃይል በማፈንና በጉልበት በማዳፈን የህወሓትን የበላይነትና ኪራይ ሰብሳቢነት ማስቀጠል ነው። ስለዚህ እንደ ሕዝብ ተወካይ ተገዢነታችሁ ለሕዝቡ ከሆነ ይህን የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ውድቅ ታደርጉት ዘንድ በአክብሮት እንጠይቃለን።
  • ሐ) ከላይ በተጠቀሰው መሰረት የአስቸኳይ ግዜ አዋጁ ሕገ መንግስታዊ ስርዓቱን አደጋ ላይ ይጥሳል። አዋጁ በእናንተ በኩል ፀድቆ ተግባራዊ ከተደረገ እንደ እኔ ባሉ ዜጎች ላይ አሰቃቂ በደልና ግፍ፣ መከራና ስቃይ፣ እስራትና እንግልት፣ ሞትና የአካል ጉዳት ያስከትላል። ስለዚህ እንደ ሕዝብ ተወካይ ተገዢነታችሁ ለሕሊናችሁ ከሆነ ይህን የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ውድቅ ታደርጉት ዘንድ በአክብሮት እንጠይቃለን። 

የተከበራችሁ የኢፊዲሪ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት!

በሕገ መንግስቱ መሰረት አንቀፅ 54(4) መሰረት ተገዢነታችሁ ለሕገ መንግስቱ፣ ለሕዝቡ እና ለሕሊናችሁ ብቻ እንደሆነ ተደንግጓል። ከዚህ በተጨማሪ፣ በአንቀፅ 54(5) መሰረት ለሕገ መንግስቱ፣ ለሕዝቡ እና ለሕሊናችሁ ተገዢ በመሆን ይህን የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ውድቅ በማድረጋችሁ አትከሰሱም ወይም አስተዳደራዊ እርምጃ አይወሰድባችሁም። ነገር ግን፣ እናንተ ይህን አዋጅ ካፀደቃችሁት ግን ንፁሃን ዜጎች ይከሰሳሉ፣ ይታሰራሉ፣ ይሰቃያሉ፣ ይገደላሉ፣… ወዘተ።

በዚህ መሰረት፣ የአስቸኳይ ግዜ አዋጁን ውድቅ በማድረግ ተገዢነታችሁ፤ ለሕገ መንግስቱ፥ ለሕዝቡና ለሕሊናችሁ እንደሆነ ታሳውቃላችሁ። ይህን አዋጅ ካፀደቃችሁትን ግን በእርግጥ ተገዢነታችሁ ለህወሓትና ለህወሓት ብቻ እንደሆነ ለመላው የኢትዮጲያ ሕዝብ ታረጋግጣላችሁ። ስለዚህ ይህን አዋጅ ውድቅ በማድረግ፣ ህገ-ወጥ፥ ፀረ-ህዝብ እና ሕሊና-ቢስ አለመሆናችሁን ታረጋግጡልን ዘንድ በመላው የኢትዮጲያ ህዝብ ስም እንጠይቃለን፡፡

Filed in: Amharic